Saturday, 28 October 2023 19:54

“አባት ዐልባ ህልሞች” መጽሐፍ ነገ ይመረቃል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 የጋዜጠኛና ደራሲ ማስረሻ ማሞ “አባት ዐልባ ህልሞች” መፅሐፍ ነገ ጥቅምት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ ከአዲሱ ገበያ ከፍ ብሎ ባለውና ፅዮን ሆቴል አጠገብ በሚገኘው ስቴይ ኢዚ ሆቴል አዳራሽ ይመረቃል።
መፅሐፉ በዋናነት የራስን እወነት ፊትለፊት በድፍረት ለመጋፈጥ ሲባል የተፃፈ ነው የተባለ ሲሆን ስነ-ልቦናዊ ህመምን፣ አካላዊ ቁስልን፣ ስሜታዊ ሲቃንና ማህበራዊ ሰቆቃን አደባባይ ማሳጣትን የፈውስ ሂደት አድጎ የሚያሳይ ነው ተብሏል።

መፅሐፉ ህይወት እንደወረደ የተንከኮለኮለበት ነው የተባለ ሲሆን፣ በአንድ ዓመት ከስድስት ወሯ እናቷ የሞተችባት፣ በ3 ዓመቷ አባቷ ጥሏት  የጠፋ፣ በአምስት ዓመቷ አያቷን በሞት የተነጠቀች፣ በአደራ የተቀበሉ ዘመዶቿ የቤት አገልጋይ ያደረጓት፣ በእህቷ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ብዝበዛ የተደረገባትና ልጅ በወለደችላቸው ወንዶች ምንም አይነት እገዛ ስላልተደረገላት የቀጨኔ እናት ህይወት ዙሪያ በዋናነት የሚያተኩር ሲሆን የባለጅን ማንነት፣ ወግና ልማድ የሚያሳይ የህይወት መስታዎት ነውም ተብሏል። በመፅሀፉ ምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ በርካታ ገጣሚያን፣ የስነ-ፅሁፍ ሰዎች ጋዜጠኞችና ተጋባዥ እንግዶች ይገኛሉም ተብሏል።


“አባት ዐልባ ህልሞች” መፅሐፍ በ340 ገጽ ተቀንብቦ በ700 ብር ለገበያ መቅረቡም ታውቋል። ደራሲና ጋዜጠኛ ማስረሻ ማሞ የአዲስ ነገር ጋዜጣ መስራች፣ አዘጋጅና አምደኛ የነበረ ሲሆን ኢሳት ቴሌቪዥን ከውጪ ሀገር ይተላለፉ በነበረ ጊዜ “ኢሳት ማማ” የተሰኘ ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢም ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ጋዜጠኛና ደራሲ ማስረሻ ማሞ እ.ኤ.አ በ2013  ዓ.ም በአምስተርዳም ከተማ ተጋባዥ እንግዳ በመሆን ከ70 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች የተተረጎመውን “The Diary of Anne Frank” የተሰኘውን መፅሐፍ በፃፈችው አና ፍራክና ቤተሰቦቿ መኖሪያ ቤት ውስጥ ለአንድ ዓመት በተጋባዥ ጸሀፊነት መኖሩን ያገኘናቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።

Read 1213 times