Friday, 20 October 2023 00:00

የአርትስ ቴሌቪዥን “በህግ አምላክ” ድራማ ምዕራፍ ሁለት ሊጀመር ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

“ሚዮዚክ ሪቮሊዩሽን” የተሰኘ አዲስ የተሰጥኦ ውድድር በቅርብ ይጀምራል

         አፍሪካን ሬነስንስ ቴሌቪዥን ሰርቪስ (አርትስ) “በህግ አምላክ” የተሰኘውንና በአርቲስት ሰለሞን አለሙ ፈለቀ እየተዘጋጀ የሚቀርበውን ምዕራፍ ሁለት ተከታታይ ድራማውን በቅርቡ እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡ ቴሌቪዥን ጣቢያው ይህን ያበሰረው ሀሙስ ምሽት ጥቅም 8 ቀን 2016 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል የተከታታይ ድራማው ፕሮዲዩሰር፣ ተዋንያኑ እና የፕሮዳክሽን ቡድኑ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና በርካታ የኪነጥበቡ ማህበረሰብ በታደሙበት ነው፡፡ ቴሌቪዥን ጣቢያው “በህግ አምላክ” ተከታታይ ድራማው ካነሳው ሀሳብ ከተዋንያን መረጣ ከፕሮዳሽን ጥራትና ከመሳሰሉት አንፃር ሲገመገም ተወዳጅና በርካታ ተመልካችን ያፈራ ስለመሆኑ የጣቢያው ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ዳንኤል በማብሰሪያ ስነስርዓቱ ላይ ተናግረዋል፡፡

በተያያዘ ዜና አርትስ ቴሌቪዥን ከንጉስ ኢንተርቴይንመንት ጋር በመተባበር “ሚዩዚክ ሪቮሊዩሽን የተሰኘ የሙዚቃ የባለተሰጥኦዎች ውድድር በቅርቡ እንደሚጀምር ያበሰረ ሲሆን በዚህም አሸናፊዎችን መኪና ከመሸለም ጀምሮ አልበም ፕሮዲዩስ እስከማድረግ የሚዘልቅ ስራ በመስራት ለዘርፉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ለማድረግ መዘጋጀቱን አብስሯል፡፡ በዚህ አይዶል ላይ ሙዚቀኞቹ ክብረት ዘኪዩስ፣ ኤንዲ ቤተ ዜማና ሮቤል መሃሪ በዳኝነት እንደሚቀጥሉ ተገልጿል፡፡ በዕለቱ የ”በህግ አምላክ” አዘጋጅና ፕሮዲዩር አርቲስት ሰለሞን አለሙ ፈለቀ ተዋናያኑ አበበ ባልቻ፣ ሚካኤል ታምሬና ሌሎቹም የተገኙ ሲሆን ሰለሞን ቦጋለን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ከያኒያን በእለቱ ከተከታታይ ድራማው አንዱ ክፍል ለእይታ ከቀረበ በኋላ የማብሰሪያ ስነስርዓቱ በዕለት ግብዣ ተጠናቅቋል፡፡

Read 1333 times