Saturday, 21 October 2023 20:26

ከመኪና አስመጪነት እስከ ሪል እስቴት አልሚነት

Written by  ከእዝራ እጅጉ
Rate this item
(1 Vote)

 “በጥራት ጉዳይ ድርድር የለም”  አቶ ዮናስ ካሣ፤

        የንግድ ስራ ፈጣሪው አቶ ዮናስ ካሣ፤ የቢዝነስ ሥራን ከአባቱ እንደተማረ ይናገራል፡፡ አባቱ አቶ ካሣ አበበ በንግዱ ዘርፍ ላይ ትልቅ አሻራ ያኖሩ የቢዝነስ ሰው ነበሩ፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ አባቱ የሚሰሩትን በቀርበት እየተመለከተ ያደገው ዮናስ፤ በ18 ዓመት ዕድሜው ነበር ወደ ንግድ ሥራ የገባው፡፡ ለ22 ዓመታት ገደማም እንደ አሉሚኒየምና ብረታ ብረት የመሳሰሉ የግንባታ ግብአቶችን በማስመጣት ሥራ ላይ ተሰማርቶ ቆይቷል፡፡ አባቱ አቶ ካሣ፤ እርሻና ትራንስፖርትን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ሰርተዋል፡፡ ጣሊያን ሀገር ድረስ እየሄዱ የተለያዩ  የመኪና መለዋወጫ ክፍሎችን ያስመጡ ነበር፡፡
 አቶ ካሣ ለዓመታት ሰርተው በህመም ሳቢያ ሥራውን ሲያቆሙት፣ ዮናስና ቤተሰቡ ቢዝነሱን በመረከብ የአባታቸውን ሌጋሲ ማስቀጠል ችለዋል፡፡ ዮናስ ገና በ18 ዓመቱ መኪና እያስመጡ በመሸጥ ሥራ ላይ በነበረበት ወቅት፣ በሌሎችም ዘርፎች በሥፋት መንቀሳቀስ እንዳለበት ያስብ ነበር፡፡ ለዚህም ነው የአሉሚኒየም እቃዎችን የማስመጣት ስራ ውስጥ የገባው፡፡ በዚህ የቢዝነስ ተሞክሮው ታዲያ በአገሪቱ ያለው የግንባታ እቃዎች አቅርቦት ምን እንደሚመስል በቅጡ መገንዘቡን ይገልጻል፡፡

 


ዮናስ፤ በቢዝነስ አለም ውስጥ ማግኘት እንዳለ ሁሉ መክሰርም እንደሚያጋጥም ከአባቱ ትምህርት ቀስሟል፡፡ በአንድ ወቅት ከፍተኛ ኪሳራ የደረሰባቸው አባቱ፤ በእንዴት ያለ ጽናትና ጥበብ ከዚያ ኪሳራ እንደወጡ ያስታወሳል፡፡ ለብዙዎችም ተምሳሌት እንደሚሆን ያምናል፡፡ ያኔ በቢዝነሳቸው ላይ የገጠማቸውን ተግዳሮት በጽናት ተቋቁመው፣ ነገም ሌላ ቀን ነው በሚል እሳቤ፣ ንግዳቸውንም  ቤተሰባቸውንም መታደግ ችለዋል፡፡ ‹‹ያኔ አባቴ ከፍተኛ ብስጭት ውስጥ ቢገባ ኖሮ፣ ነገሮች ተባብሰው ዳግም ቢዝነሱ ህይወት ሊያገኝ አይችልም ነበር፡፡ እኛም እርሱ ከደረሰበት ፈተና ትምህርት ቀስመን ቢዝነሱን ለማስቀጠል ችለናል›› ሲል ዮናስ ያንን ፈታኝ ጊዜ  ያስታውሰዋል፡፡ አቶ ካሳ አበበ፣ ከ10 ዓመት በፊት ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ ወዳጆቻቸው በትጋታቸው፣ ሥራ ወዳድነታቸውና ቁርጠኝነታቸው ያስታውሷቸዋል፡፡


ለበርካታ ዓመታት በአስመጪነትና ላኪነት ሥራ ላይ የቆየው ዮናስ ካሣ፤ የረዥም ጊዜ ህልምና ዕቅዱ ወደነበረው የሪል እስቴት ዘርፍ ለመግባት መወሰኑን ይገልጻል፡፡ ከ20 ዓመት በፊት በእንግሊዝ  ሀገር የአይቲ ትምህርቱን በሚከታተልበት ወቅት፣ ሀገሩ ገብቶ በዚህ ዘርፍ ላይ የመሰማራት ትልቅ ህልም እንደነበረው ያስታውሳል፡፡ ሪል እስቴት፤ ገና ብዙ ያልተሰራበት ዘርፍ መሆኑን ዮናስ ይናገራል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገራችን የመኖሪያ ቤት ችግር አንገብጋቢ ቢሆንም፣ በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት ቁጥር ግን እጅግ አናሳ ነው፡፡ ከ5 አመት በፊት ኮስሞፖሊታን ሪል እስቴትን የጀመረው ዮናስ፤ ወደ ሥራው ከመግባቱ 2 ዓመት በፊት ዝርዝር ንድፉን  አውጥቶ እንደነበር ይናገራል፡፡ አሁን ደግሞ በቴክኖሎጂና በኢነርጂ ዘረፍ ላይ ለመሰማራት እቅድ አውጥቷል፡፡ ይህም እውን እንደሚሆን ቅንጣ ጥርጣሬ የለውም፡፡


ባለፈው ቅዳሜ፣ ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም፣ ቦሌ ጃፓን ኤምባሲ አካባቢ ለምርቃት የበቃውን ባለ 11 ፎቅ የኮስሞፖሊታን አፓርታማ፣ ብዙዎች አድናቆት ቸረውታል፡፡ አፓርታማውን በጥራት ሰርቶ ለማጠናቀቅ  ግን  ብዙ ትጋቶችን፣ ብዙ እንቅልፍ አልባ ሌሊቶችን ብዙ መስዋዕትነትን መጠየቁን ዮናስ ያስረዳል፡፡   
“ሥራው ከባድ ነው፤ አንዳንዴ ሌሊት ሁሉ ያባንንሀል፤ የሆነ ነገር ሳይሰራ የቀረ ይመስልሃል፡፡ እኔ ጥራት ላይ በመደራደር አላምንም፡፡ የቱንም ያህል ዋጋ ተከፍሎም ቢሆን ጥራትን በማምጣት አምናለሁ፡፡ የተበላሸ ነገር ፈጽሞ እንደማልቀበል እኔ ዘንድ የሚሰሩ ሰዎች ጠንቅቀው ያውቃሉ፤” ሲል የሥራውን ፈታኝነት ያስታውሳል፡፡  
 የኮስሞፖሊታንን የውስጥ ዲዛይን ያወጣው ራሱ መሆኑን የሚናገረው ዮናስ፤ እንዲህ አይነት ስራዎችን ሲሰራም ከፍተኛ እርካታ እንደሚሰማው ይገልጻል፡፡ በየጊዜው ራሱን ከአዳዲስ እውቀቶች ጋር በማስተዋወቅ በግንባታ ዘርፉ አዲስ እይታ ይዞ ለመምጣት ሁሌም ይታትራል፡፡ በተለምዶ ከስህተት የጸዳ ስራ ወይም ፈረንጆቹ “ፐርፌክሽኒስት” የሚሉት አሰራር ዮናስ ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ በዚህ መንገድ መሄድ ለስኬት ያደርሳል ብሎ ስለሚያምንም ሁሌም ይመራበታል፡፡ አንዳንድ ባለሙያዎች፤ ”እዚህች ጋር የሰራሃት ትፍረስ“ የሚል አስተያየት ሲሰጣቸው  ደንግጠው በዚያው ሊቀሩ ሁሉ የችላሉ፡፡ ዮናስ ግን ደንግጠው ከሚቀሩ ይልቅ  ከስህተታቸው ተምረው የተሻለ ባለሙያ ቢሆኑ ያተርፋሉ ይላል፡፡ በተለይ የቤት ማጠናቀቂያ ግንባታ ወይም ፊኒሺንግ ላይ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ታግሶ መስራትን ሊለማመዱ ይገባል ሲልም ይመክራል፡፡ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የችሎታ ችግር የለባቸውም፣ ነገር  ግን ታግሶ በጥራት የመስራት ዲሲፕሊን ያስፈልጋቸዋል ብሏል - ወጣቱ ሥራ ፈጣሪ፡፡

 
“አንዳንዶቹ እኛ ጋ  ሰርተው አዲስ  እውቀት ሲቀስሙ መጨረሻ ላይ እኛን ያመሰግኑናል፡፡ ይህም እኛን ያስደስተናል፤” ይላል፤ዮናስ፡፡
የኮስሞፖሊታን መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ዮናስ፤ የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ ካስመረቀው አፓርታማ ባሻገር ቦሌ ኦሎምፒያ ባለ 17 ፎቅ ህንጻ እንዲሁም ፒያሳ ካቴድራል ተጨማሪ ቤቶችን ጀምሯል፡፡ ዮናስና የአመራር ቡድኑ ኮስሞፖሊታንን በመገንባት ባገኙት ልምድ፣ በ3 ዓመት ውስጥ የኦሎምፒያውን ሪል እስቴትና የፒያሳውን ለገበያ ማዕከል የሚውል ህንፃ ለማጠናቀቅ አቅደዋል፡፡ የኦሎምፒያው ግንባታ በአሁኑ ወቅት 2ኛ ፎቅ ላይ የደረሰ ሲሆን፤ ስራውም በፍጥነት እየተከናወነ እንደሚገኝ ዮናስ ነግሮናል፡፡ ፒያሳ የሚገኘው ደግሞ ለገበያ ማእከልና ለሱቆች የታለመ ባለ 16 ፎቅ ሲሆን፤ የዲዛይን ስራው ተጠናቅቆ በቅርቡ ግንባታው ይጀመራል፡፡የሪል እስቴት ሥራውን በፍቅር እንደሚወደው የሚገልጸው ዮናስ፤ በዚህም የተነሳ አንድ ግንባታ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከአጠገቡ እንደማይለይ ይናገራል፡፡ በሳምንት 3 ጊዜ የግንባታ ሳይቱ ድረስ በመሄድ ጉብኝት ያደርጋል፡፡ “… እኛ ሳይት ለጉብኝት በምንሄድበት ሰአት ምንድን ነው ያልተሰራው ብለን እንከን ነው የምንፈልገው፡፡ ጥሩ አድርጎ መስራትማ የባለሙያዎቹ ግዴታ ነው፡፡ እያንዳንዱ ነገር መታየት አለበት፡፡ ዝርዝር የሆነ ነገር እናጠናለን፡፡ እኔ በማልሄድበት ሰአት ደግሞ ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ተገኝተው ክትትል የማድረግ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ይወጣሉ፡፡” ሲል ለስራው የሚሰጠውን ትኩረት ጠቁሟል፡፡


 የኦሎምፒያው  ባለ 17 ፎቅ ህንጻ የሆቴል አፓርትመንት እንደሚባለው አይነት ነው፡፡  የራሱ መዋኛ ይኖረዋል፡፡ ሳውናና ስቲምም አለው፡፡ ቤትም ሆቴልም እንደማለት ነው፡፡ አንድ ሰው ቤቱን ሲገዛ እንደ ሆቴል አድርጎ በደንብ ከያዘው፤ ጥሩ የኢንቨስትመንት አማራጭም ይሆንለታል፡፡ በቀላሉ ለማከራየትም ይችላል፡፡ ዱባይ ውስጥ እንዳለው ሆቴል አፓርትመንት ማለት ነው፡፡  በግንባታ ዘርፍ ብዙ ተግዳሮቶች እንዳሉ የሚገልጸው ዮናስ፤ ከዋጋ መናር ጀምሮ በርካታ ወቅታዊ ችግሮች  ሲከሰቱ በሥራው ላይ እክል መፍጠራቸው እንደማይቀር ያስረዳል፡፡ የቱንም ያህል ዋጋ ቢንር ታዲያ ችግሮችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመቁጠር፣ ሥራውን አጠንክሮ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡ “የእቃ መጨመር ሁሌም ይኖራል፤ በእኔ እምነት ከነገ ዛሬ ይሻላል፤ የጀመሩትን እንደምንም ብሎ ጥርስ ነክሶ ማጠናቀቁ  ዋና ነገር ነው፡፡” ብሏል፡፡ ጥራት ያለው ነገርን መውደድ ዋጋ ቢያስከፍልም መልሶ ደግሞ ይከፍላል የሚለው  ዮናስ፤ አንድን ስራ በችኮላ ከመስራት ይልቅ በጥንቃቄና በንጽህና ምርጥ አድርጎ መስራት በተለይ በሪል እስቴት ዘርፍ የግድ መሆኑን ያሰምርበታል፡፡  በቢዝነስ ዓለም ውስጥ በተለይ በሪል እስቴት ሥራ ታማኝ ሆኖ መስራት፣ ለጥራት ቅድሚያ መስጠት፣ ለቤት ፈላጊ በሰአቱ ማስረከብ የሚሉት አስተሳሰቦች መሰረታዊ ናቸው፤ ይላል፡፡  “አንድ ሰው አምኖን ገንዘቡን የሚሰጠን እኛም በታማኝነት ሰርተን ስናስረክብ ነው” ሲልም ሀሳቡን ያጠናክራል፡፡  በህብረት ተጋግዞ የመሥራትን ፋይዳ የሚያነሳው ዮናስ፤እኛ አገር የሚጎድለን ግን ደግሞ ለስኬት የሚያግዘን በጎ እሴት መሆኑን ይገልጻል፡፡ “እኔ ለምሳሌ ለሥራ ወደ ውጭ ሀገር ብሄድ ወንድሜ መጥቶ ድርጅቱን ይመራልኛል፤ ይህ አይነቱ ተጋግዞ የመስራት ባህል ኢትዮጵያ ውስጥ መለመድ አለበት” ይላል፡፡ የውጭዎቹ ሰዎች  ተጋግዞ የመሥራት ባህል ስላዳበሩ ነው ለስኬትና ዕድገት የበቁት የሚለው ሥራ ፈጣሪው ዮናስ፤ እኛም የእነርሱን መርህ ብንከተል ያዋጣናል ባይ ነው፡፡

Read 1093 times Last modified on Sunday, 22 October 2023 17:53