“ጥያቄው አገሪቱ ከአጎራባቾቿ ጋር ያለትን የቆየ ቁርሾ እንደመቀስቀስ ይቆጠራል”
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ሰሞኑን ለጎረቤት ሀገራት ያቀረቡትን የወደብ ባለቤትነት ድርድር ጉዳዪ የሚመለከታቸው ሁሉም አገራት ውድቅ አደረጉት ። ኤርትራ ጅቡቲና ሱማሊያ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥያቄ እንደማይቀበሉ ይፋ አድርገዋል ። የወደብ ባለቤትነት ጥያቄው አገሪቱ ከአጎራባቾቿ ጋር ያለትን የቆየ ቁርሾ እንደመቀስቀስ ይቆጠራል ተብሏል ።
ሱማሊያ ከጠ/ሚኒስትር የቀረበውን የወደብ ባለቤትነት ውይይት እንደማትቀበለውና የወደብ ጉዳይ ልክ እንደ ሌሎች የሉኣላዊነት ጉዳዮች የሚታይ ነው ማለቷን ብሉንበርግ ዘግቧል ።የሶማሊያ ፕሬዝዳንት አማካሪ አብዲራህማን አብዲሻኩር በኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት በኩል በተደጋጋሚ የወደብ ባለቤትነትን አስመልክተው የሚሰጡትን አስተያየት እንዲሁ ችላ የሚባል አለመሆኑንና መንግስታቸው ሁኔታውን በትኩረት እንደሚከታተለው መግለፃቸውን ሶማሊ ጋርድያን በድረገጹ አስነብቧል።
የሶማሊያ ብሔራዊ የደህንነት መስሪያ ቤት (NISA) ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት ኢስማኤል ኦስማን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በቀይባህር ዙሪያ የወደብ ባለቤት ለመሆን እየሄደችበት ያለው መንገድ አለም አቀፍ አካሄድን የጣሰ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።ኢስማኤል ኦስማን በሰጡት ትንታኔ፤ የአለም ሀገራት የራሳቸው የሆነ በርካታ የተፈጥሮ ሀብት እንዳላቸው ጠቁመው፤ ሀገራት ይህንን የተፈጥሮ ሀብት ማለትም ነዳጅም ሆነ ወደብ በአለም አቀፍ የትብብርና በሰላማዊ መንገድ በሽያጭና በተለያየ መንገዶች በጋራ እንደሚጠቀሙ አስታውቀዋል።
ከዚህ ውጭ ግን በጉልበት ለማግኘት መጣር አለም አቀፍ አካሄድን የጣሰ ነው ሲሉ ተችተዋል።
ጠ/ሚኒስትር በቀይባህር ዙሪያ የወደብ ባለቤት ለመሆን ያቀረቡት ሀሳብና ለማግኛነት ያቀረቡት አካሄድ የተባበሩት መንግስታት ቻርተርንና አለም አቀፍ ህግን የጣሰ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የቀድሞ የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት ባላል ሞሃመድ ኩስማን በበኩላቸው፤ የጠ/ሚኒስትሩ የወደብ ባለቤትነት ሀሳብ፣ ኢትዮጵያ ከአጎራባቾቿ ጋር ያለትን የቆየ ቁርሾ እንደመቀስቀስ ይቆጠራል ሲሉ ተችተዋል።
ባላል ሞሃመድ፤ ሂራን ድረገጽ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍም ጠ/ሚኒስትር አብይ ዛይላ ወደብን አስመልክቶ የሰጡት አስተያየት፣ በብዙ ጥረት ወደ መልካም ግንኙነት የተመለሰውን የሶማሊያና ኢትዮጵያን ግንኙነት የሚያበላሽ ነው ሲሉ አሳስበዋል።
ጉዳዩ ቀጠናውን ወደ ቀውስ የሚወስድ ነው ሲሉም አስጠንቅቀዋል። ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ሰሞኑን ለጎረቤት ሀገራት ያቀረቡትን የወደብ ባለቤትነት ድርድር ጉዳይ የተቃወመችው ሌላኛዋ አገር ጅቡቲ ነች ። የጅቡቲ ፕሬዝዳንት እስማኤል ኡመር ጊሌ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አሌክሴስ ሞሃመድ፤ ጅቡቲና ኢትዮጵያ ጠንካራ የሆነውን ግንኙነታቸውን አስጠብቀው የሚኖሩ ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ “ ነገር ግን ጅቡቲ ሉአላዊ ሀገር ናት፤ የግዛት አንድነታችን ዛሬም ሆነ ወደፊት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም” በማለት ጥያቄው በሀገራቸው በኩል ተቀባይነት እንደሌለው መግለጻቸውን ብሉምንበርግ ዘግቧል ። ኤርትራ በማስታወቂያ ሚኒስትሯ በኩል በሰጠችው ምላሽ፤ ኤርትራ የኢትዮጵያን የወደብ ባለቤትነት ጥያቄ እንደማትቀበለውና ቦታ እንደማትሰጠው ገልፃለች፡፡ ኤርትራ አክላም፤ በባሕር በር ዙሪያ የተነሳው ትርክት “ከመጠን ያለፈ” እና “ግራ የሚያጋባ ነው” ስትል ጉዳዩን ውድቅ አድርጋዋለች ።