Friday, 20 October 2023 15:05

የልጆች አመጋገብ እና ሁለንተናዊ እድገት (ክፍል 1 )

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ምግብ በልጆች ሁለንተናዊ እድገት ላይ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል። በተለይ ልጆች ከተወለዱበት እስከ 2 አመት እድሜያቸው ድረስ ያለ አመጋገባቸው ለአእምሮአዊም ሆነ አካላዊ እድገታቸው እጅግ ወሳኝ ነው፤ ስለዚህ በዚህ ወቅት አስፈላጊው ሁሉ ተሟልቶላቸው እንዲያድጉ በልጆች ዙርያ ያሉ ሁሉ ኃላፊነት መውሰድ ይኖርባቸዋል።

በቅድሚያ ልጆችን በምንመግብበት ወቅት ማወቅ ከሚገቡን ነገሮች መካከል ማሳተፍ (responsive feeding) የምንለውን ነው ፤ ይህም ልጆች ምግብን እንዲሁም የአመጋገብ ሂደትን እንዲወዱት ይረዳናል።
ልጆችን ስንመግብ የስነ ልቦና እና ማህበራዊ እድገታቸውን ታሳቢ ያደረጉ መመርያዎችን (principles of psychosocial growth and development) መከተልም እጅግ አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም በዚህ እድሜአቸው ከአመጋገብ በተጨማሪ ለእነርሱ ብዙ አይነት ክህሎቶችን (life skills) የሚማሩበት ጊዜ ስለሆነ ነው።

ልጆችን ስንመግብ ተሳትፎአቸውን የምንጨምርባቸው መንገዶች ምን ምን ሊሆኑ ይችላሉ?

1ኛ. ልጆች እንደየእድሜአቸው ራሳቸውን ችለው እንዲመገቡ ማበረታታት።
ጨቅላ ህፃናት በትልልቅ ሰዎች መመገብ ሲኖርባቸው ፤ ልጆች እድሜያችው ከፍ ሲልና በእጅ የሚያዝ ምግብ ካስጀመርናቸው በኋላ ግን በራሳቸው እንዲበሉ ማበረታታት እና ማገዝ (assist) ብቻ በቂ ነው፤ ሁል ጊዜ በእኛ እጅ ብቻ እንዲመገቡ መፈለግ የለብንም (ይህም ምግባቸውን እንዲወዱት እና በአመጋገብ ስርዓታቸው ላይ ኃላፊነት እንዲሰማቸው ከማድረግም በላይ በራስ መተማመናቸው እንዲጨምር ያግዛል)

2ኛ. የልጆችን የምግብ ምርጫ ማስፋት።
አንዳንድ ጊዜ ልጆች የምናቀርብላቸውን ምግብ ያለመፈለግ ሊያሳዩ ይችላሉ፤ በዚህ ጊዜ አልወደዱትም ብለን ሙሉ በሙሉ የምንተው / የምንቀይር ከሆነ ጠባብ የምግብ ምርጫ እንዲኖራቸው ወይም picky eaters እንዲሆኑ ስለሚያደርጋቸው በተለያየ ጊዜ በተለያየ አዘገጃጀት ደጋገመን መሞከር ይኖርብናል። ይህም የምግብ ምርጫቸውን እንዲያሰፉ እንዲሁም ከየምግቡ አይነት ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም ሁሉ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። እንዲሁም ይህንን በተደጋጋሚ በማድረግ ባህርይ አድርገው እንዳይዙትም ጭምር ያግዛል።
   
3ኛ. በምግብ ሰዓታቸው ተግባቦትን ማዳበር።
ለልጆች የምግብ ጊዜ ከመብላትም ባለፈ ከቤተሰባቸው እና አካባቢያቸው ካሉ ሰዎች ብዙ የሚማሩበት ስለሆነ እያዋራናቸው፣ እያጫወትናቸው እንዲሁም በተለያየ በሚገባቸው መንገድ communicate እያደረግናቸው ልንመግባቸው እና አብረናቸው ልንሆን ያስፈልጋል፣ በዚህ ጊዜ የተለያዩ ማህበራዊ ክህሎቶችን (social skills) እና ፍቅርን ይማራሉ፤ ስለ ምግብም መጥፎ አመለካከት ይዘው እንዳያድጉ ያደርጋቸዋል። ልጆችን በሚመግቡበት ጊዜ ከልጅዎ ጋር ጥሩ የጋራ ፣የመቀራረብ እና የአብሮነት ወይም bonding ጊዜ ያሳልፉ።

4ኛ. ልጆችን በማንኛውም ምክንያት በአመጋገብ ሁኔታቸውና በምግብ ምርጫቸው ከሌሎች ልጆች ጋር አለማወዳደር።
በማንኛውም ምክንያት በልጆች ላይ ይህን ማድረግ በፍጹም አያስፈልግም፤ ይህ ይበልጥ ምግብን እየጠሉ እንዲሄዱ እና ነፃነት እንዳይሰማቸው ከማድረጉም በላይ በራስ መተማመናቸውን የሚያወርድ ተግባር ስለሆነ ፈጽሞ ልናደርገው አይገባም።

5ኛ. ልጆችን በግድ እኛ በምንፈልገው መንገድ እና ሁኔታ እንዲመገቡ አለማድረግ።   
ልጆችን ስንመግብ ማስገደድ ተገቢ አይደለም ፤ ምክንያቱም የቀረበውን ምግብም ሆነ የምግብ መብላት ስርዓቱን እንዲጠሉት ሊያደርግ ስለሚችል ነው። ልጆች እያጎረስናቸው እንዲመገቡ ማድረግ ያለብን በእጅ ተይዘው የሚበሉ ምግቦች እስኪጀምሩ ድረስ ብቻ ነው (ይህም ማለት እድሜያቸው 9 ወር እስኪሞላ ነው)፤ ከዚያ በኋላ ግን ለራሳቸው በሰሃን ሰጥተን በሚፈልጉት መንገድ እንዲመገቡ መፍቀድ ይኖርብናል።

በዚህ ጊዜ በሚገባ መረዳት ያለብን ነገር ቢኖር ፤ እኛ ባሰብነው መንገድ ላይበሉ ይችላሉ ማለትም፦
• ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስዱ ይችላሉ
• ራሳቸውን እና አካባቢያቸውን ሊያቆሽሹ ይችላሉ
• ምግባቸውን ሊደፉ ይችላሉ ወይም በተለያየ ምክንያት እኛ በቂ ብለን በምናስበው መንገድ ላይመገቡልን ይችላሉ።

ነገር ግን ታግሰን እንዲለምዱ ማድረግ ይኖርብናል፣ እንዲሁም እርዳታችንን ሲፈልጉ ብቻ ልናግዛቸው ይገባል። ይህም በተመሳሳይ የኃላፊነት እና ተቆጣጣሪነት (control) ስሜት እንዲኖራቸው ስለሚያደርግ የምግብ ጊዜአቸውን እንዲወዱት እና እንዳይጨነቁ ይረዳል ፤ በጊዜ ራሳቸውን እየቻሉ  ስለሚሄዱም ለእኛም በአመጋገባቸው ዙርያ ጭንቀትን በሂደት ይቀንስልናል።
ከዚህም ጋር በተያያዘ ደግሞ ምግብ ሲበቃቸው ያላቸውን ስሜት ልንረዳቸው ይገባል።

6ኛ. ልጆች በልተው ሳይጨርሱ ከስር ከስር ማጽዳት (እጃቸውን ፣ ፊታቸውን እና አካባቢያቸውን መጠራረግ) የለብንም ፤ ይህም ምግብን በትክክለኛው መንገድ እንዳይረዱት ያደርጋቸዋል።

7ኛ. ለልጆች ብቻቸውን ምግብ ከመስጠት ይልቅ በተቻለ ጊዜ ሁሉ ቤተሰብ ምግብ በሚበላበት ሰዓት አብረው እንዲበሉ ማድረግ የምግብ ፍላጎታቸው እንዲጨምር፤ ትኩረታቸው ምግቡ ላይ ብቻ እንዲሆንና ለብዙ ምግቦች ተጋላጭ እንዲሆኑ (exposure እንዲኖራቸው) ይረዳል።

ተጋላጭነት (Exposure) ስንል ግዴታ ስለሚበሉት ብቻ ሳይሆን አካባቢያቸው ላይ የቀረቡ ምግቦችን ማየትን፣ ማሽተትን፣ መንካትን፣ መቅመስን ወይም መሞከርን ሁሉ እንደሚያካትት ልንገነዘብ ይገባል።

በተጨማሪም ልጆች ምግብ ሲበሉ እንደ ቴሌቪዥን ፣ ስልክ እና የመሳሰሉ ትኩረታቸውን የሚስቡ ነገሮችን ማስወገድ ያስፈልጋል። ይህም ትኩረታቸውን በመውሰድ ምግቡን እንዳያጣጥሙት ከማድረጉም በላይ ከመጠን በታች ወይም በላይ እንዲበሉ ሊያደርግ ይችላል። በቀጣይም ካለእነዚህ ነገሮች ለመብላት ስለሚያስቸግሩ ለተንከባካቢዎቻቸው አስቸጋሪ ይሆናል።

ሌላው በሚገባ ማወቅ ያለብን ህፃናት በዚህ ወቅት ያላቸው አመጋገብ በእድገታቸው እና በቀጣይ እድሜያቸው እንዲሁም ጤናቸው ላይ ያለውን አስተዋጽዖ ነው።  የምግቦችን ትክክለኛ የስነ ምግብ ይዘት አለማወቅና ስለ አንዳንድ ምግቦች ያለን መጥፎ አመለካከት ልጆች ከሚመገቡት ምግብ በቂ ንጥረ ነገር እንዳያገኙና በአግባቡ እንዳያድጉ ያደርጋቸዋል።

ኢማን ዘኪ
የስነ ምግብ ህክምና ባለሙያ

Read 496 times