Monday, 16 October 2023 00:00

ጦርነት ቅስም ሰባሪ ነው!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ይችን አለም ድንቁርናና ስልጣኔ ተባብረው እንድትጠፋ የፈረዱባት ይመስላል። ጋዛም ይሁን እስራኤል፣ አፍጋንም ይሁን ሶሪያ፣ ሱዳንም ይሁን ዩክሬን፣ አማራም ይሁን አፋር፣ ትግራይም ይሁን ወለጋ ደረጃውና አይነቱ ይለያይ እንጂ የንፁሃን ሰቆቃና ስቃይ ህመሙ አንድ ነው። የሰው ልጆች አንድ ናቸው - ሟች ስጋ ህያው ነፍስ። ልዩነታችን አነጋገር፣ አኗኗርና አበላል ካልሆነ በቀር። ከብረት የተሰራ፣ የመላዕክ ክንፍ ያንጠለጠለ የሰው ልጅ የለም። ደስታችን እንጂ መከራችን የጋርዮሽ ነው። የመከራችን ምንጭ ደግሞ፣ የሰው ልጆች ራስ ወዳድነት፣ ሁሉን የኔ ባይነት ነው። በዘርም ታሰበ በጎሳ፣ ለመረጡት ዘር-ለመሩት ሀገር ዳፋ አውርሰው ያለፉ በታሪክ ብዙ ናቸው።
ጋዛ ወደ ምድር ሲኦልነት ተቀይራለች። ይሄዱበት መንገድ፣ ይኖሩበት ሰፈር ግራ ገብቷቸዋል። እናት ልጆቿን የምታደርስባት አጥታ በእምባ ወደ ሰማይ ትቃትታለች። ማንም ሆነ ማን ጥፋተኛ፣ የጋዛና የእስራኤል እናቶች እኩል እያለቀሱ ነው።
እኛ ድንቁርናችንና ደሃ መሆናችን በጀን እንጂ ይሄኔ በሚሳኤልና በሮኬት እርስ በርስ ተላልቀን ነበር። ተራሮች እስኪስቁብን ድረስ ሰው ባልተረፈን ነበር። ያም ሆኖ እንደ ጋርዮሽ ዘመን በገጀራና በቁመህ ጠብቀኝ ከመጨፋጨፍ አልዳንም።
ጦርነት ምን ያህል ቅስም ሰባሪ እንደሆነ አፋር፣ ምስራቅ አማራና ትግራይ ያየሁት ነገር ከአእምሮዬ ተስሎ አልጠፋ ብሎኛል። በመጨባበጥ የተቋጨው የሰሜን ጦርነት ሚሊዮኖችን ሲኦል በመሰለ የምድር ሰቆቃ ጥሎ እንዳለፈ እኔ ለታሪክም ለተረክም ምስክር ነኝ። እኛ የሰራነውን ዘጋቢ ፊልም፣ እኛ ራሳችን እንኳን አይተን መጨረስ አልቻልንም። የሰው ልጆች ክፋት እንዲህ ይከፋል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር። ዛሬም ሌላ ሰቆቃ…ሌላ እምባ….
ባለፈ ሳምንት ለ20 አመታት በጦርነት የደቀቀችው የአፍጋኒስታን የጤና ሚኒስትር ከነበረ ሰው ጋር አጠር ያለ ውይይት አደረግን። ዋና አላማው ጤናና ሰላም ላይ የሚሰራ አለም አቀፍ ተቋም መመስረት ላይ ቢሆንም፣ ስለ አፍጋን የነገረኝ ነገር ልብ ይሰብራል። ጦርነት የሰውን ልጆች ከመኖር ወደ አለመኖር የሚቀይር ሰቆቃ ነው። በአፍጋን 90 በመቶ የሚሆን ህዝብ አሁን እርዳታ ጠባቂ ሆኗል።
ጦርነት ዝም ብሎ አይጀመርም። ወይ በጠገቡት፣ አሊያም በተገፉት ይጫራል። ከዚያ ይቀጥላል….ንፁሃን ሲያልቁ፣ ወይ በድርድር አሊያም በስልጣን መንበር ይጠናቀቃል። ሲያልቅ ግን 20 እና 50 አመት ወደ ኋላ መልሶን ነው።
ፈጣሪ የንፁሃንን ሰቆቃ ሰምቶ የክፉዎችን ልብ እንዲያራራ ፀሎቴ ነው፡፡
ሰላም ለሰው ልጆች ሁሉ!
(ዘላለም ጥላሁን)


Read 1223 times