Saturday, 07 October 2023 20:53

ኢትዮጵያ በከፍተኛ የደህንነት ስጋት ላይ እንደምትገኝ የሰብአዊ መብቶች መርማሪ የባለሙያዎች ቡድን አስታወቀ።

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

በኢትዮጵያ በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸሙ አስከፊ ወንጀሎች   እየተባባሱ መቀጠላቸውና አገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ አስጊ በሆነ የደኅንነት ስጋት  ላይ እንደምትገኝ   የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መርማሪ የባለሙያዎች ቡድን አስታወቀ። ቡድኑ ባወጣው አዲስ ሪፖርት፤ በተለይ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በአፋር ክልሎች ያለው ሁኔታ  በእጅጉ እንዳሰሰበው አመልክቷል።
 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደገፈውና  በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያለውን ሁኔታ የመረመረው  ኮሚሽኑ  በኢትዮጵያ አሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ በአሳሳቢነቱ ሊቀጥል የሚችል፣ “በከፍተኛ ደረጃ አስጊ” የሚባል መሆኑንና  በአገሪቱ   ውስጥ “በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚፈጸሙ ከባድ ወንጀሎች ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ስጋቶች መኖራቸውን    ሰሞኑን  ባወጣው ሪፖርት  ገልጿል።
መርማሪ ቡድኑ በሪፖርቱ እንዳስታወቀው፤ ከባድ ወንጀሎች የሚባሉት በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸሙ አስከፊ ወንጀሎች ሲሆኑ፣ እነዚህም የዘር ማጥፋት፣ የጦር ወንጀሎችና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ናቸው ብሏል ።መርማሪ ኮሚሽኑ እንዳለው ለእነዚህ ወንጀሎች ሊያጋልጡ የሚችሉ ሁሉም ሁኔታዎች በኢትዮጵያ ውስጥ እየተስተዋሉ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ከእነዚህም ውስጥ ቀጣይነት ያላቸው ከባድ የመብት ጥሰቶች፣ መጠነ ሰፊ ጥቃቶች፣ አለመረጋጋትና ተጠያቂነት አለመኖር ተጠቃሽ የሆኑ  ስጋቶች መሆናቸውን አመላክቷል።
በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ባለሙያዎች ቡድን ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ሪፖርት እንደገለጸው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ “ከባድ የሚባሉ ወንጀሎችን ሊያስከትሉ የሚችሉ አስጊ ሁኔታዎች” በከፍተኛ ሁኔታ በአገሪቱ ውስጥ የሚታዩ መሆናቸውን አመልክቷል።
በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን  ደም አፋሳሽ ጦርነት ተከትሎ   የተቋቋመው ይህ የባለሙያዎች ቡድን፣ ባለፈው ነሐሴ ወር ባወጣው ሪፖርት፣ የትግራይ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ   በአገሪቱ የጦር ወንጀሎች መፈጸማቸውን መግለጹ የሚታወቅ ሲሆን፤ አሁንም በአገሪቱ እየተካሄዱ ያሉ ከባድ የመብት ጥሰቶች፣ መጠነ ሰፊ ጥቃቶችና ለተፈጸሙ ወንጀሎች ተጠያቂነት ያለመኖር ፣ ተጨማሪ ወንጀሎች እንዲፈጸሙ የሚያደርግ፣ ከፍተኛ አደጋን የደቀነ ጉዳይ  ነው ሲል ቡድኑ በሪፖርቱ  ገልጿል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች የባለሙያዎች ቡድን  ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ  በኦሮሚያ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ዓለም አቀፍ ወንጀሎች መፈጸማቸውን መመዝገቡን ገልጿል። እንዲሁም በአማራ ክልል ከሕግ ውጪ የሚፈጸሙ ግድያዎችንና የጅምላ እስሮችን በሚመለከት በቅርቡ የወጡ ሪፖርቶች እንዳሰሳቡትም አመልክቷል።
በትግራይ ጦርነት ወቅት ለተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች መንግሥት በሽግግር ፍትሕ ሂደት አማካይነት መፍትሄ እንደሚሰጥ በመጥቀስ፣ በኮሚሽኑ አስፈላጊነት ላይ ተቃውሞውን ሲያሰማ መቆየቱ ይታወቃል።

ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ ተቃውሞ እያቀረበ ያለው  መንግሥት፣ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች የባለሙያዎች ቡድን የሥራ ጊዜ እንዲበቃ እና በአገሪቱ የሕግ ማዕቀፍም ጥሰቶች እንዲታዩ ከፍተኛ ጫና ሲያደርግ መቆየቱን ሮይተርስ ዘግቧል ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት፣ በትግራይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ተቀስቅሶ ወደ አጎራባቾቹ የአማራና የአፋር ክልልሎች በተዛመተው የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች፣ የስደተኛ ሕጎች እና ሌሎች ጥሰቶችን የሚያጣራ ገለልተኛ ምርመራ የሚያካሂድ መርማሪ ቡድን ለማቋቋም የውሳኔ ሃሳብ ያሳለፈው ታኅሣሥ 2014 ዓ.ም. ነበር።
በአውሮፓ ኅብረት ጠያቂነት በተካሄደው የምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ፣ በሰብዓዊ ምክር ቤቶች ፕሬዚዳንት የሚሾሙ አባላትን የያዘ ዓለም አቀፍ ኮሚሽን ለማቋቋም ውሳኔ ላይ የደረሰውም በዚያን ወቅት ነበር።
በወቅቱም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መርማሪ እንዲቋቋም የተላለፈውን ውሳኔ እንደማትቀበለውና አንዳንዶች የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔን ለፖለቲካ ዓላማ ማራመጃነት ሲጠቀሙበት በድጋሚ ማየቷ እንዳሳዘናት በመግለጽ፤ በውስጥ ጉዳይዋ ጣልቃ ለመግባት የሚደረግ ሙከራን እንደማትቀበልና፣ እንደማትተባበርም መግለጿ ይታወቃል ።











Read 1493 times