Friday, 06 October 2023 00:00

የአሜሪካ ዓለማቀፍ ተራድዖ ድርጅት በኢትዮጵያ አቋርጦት የነበረውን ዕርዳታ ለስደተኞች ብቻ መስጠት ጀመረ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

ለስደተኞች ብቻ መስጠት ጀመረ
በኢትዮጵያ 20ሚ. ሰዎች እርዳታ ይፈልጋሉ ተብሏል

   በኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ሰብአዊ እርዳታዎችን በማቅረብ በቀዳሚነት የሚታወቀው    የአሜሪካ ዓለማቀፍ ተራድዖ ድርጅት (ዩኤስአይዲ) ፤  ለተረጂዎች የታለመውን የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ከታለመለት ዓላማ ውጪ ውሏል በማለት በመላ አገሪቱ  ለወራት   አቋርጦት የነበረውን  የምግብ ዕርዳታ ለስደተኞች ብቻ መስጠት ጀመረ።  
ድርጅቱ፣ የዕርዳታ አቅርቦቱን ዳግም  የጀመረው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ራሱን ከዕርዳታ ሥርጭትና ክምችት ለማግለል በመስማማቱ እንደሆነ አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።
ድርጅቱ  በአገሪቱ የሚያደርገውን የእርዳታ አቅርቦት  በትግራይ ውስጥ ተከስቷል ከተባለው የእርዳታ ምግብ ስርቆት ጋር በተያያዘ ያቋረጠ ሲሆን ፤ በማስከተልም ከወራት በፊት በመላው አገሪቱ የሚያካሂደውን የምግብ እርዳታ አቋርጦ ቆይቷል።
የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት ውሳኔውን ባሳወቀበት ጊዜ “የተደረገውን አገር አቀፍ ቅኝት ተከትሎ ዩኤስኤአይዲ፣ በእርዳታ አቅርቦቱ ላይ ለውጥ እስኪደረግ ድረስ በዚህ ሁኔታ መቀጠል ስለማይቻል፣ አስቸጋሪ ነገር ግን አስፈላጊ ውሳኔ አሳልፈናል”  በማለት ውሳኔውን አሳውቆ ነበር።
ከዩኤስኤአይዲ በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም  በተመሳሳይ የእርዳታ አቅርቦቱን ያቆመ ሲሆን፣ ሁለቱም በአገሪቱ የሚቀርበው የምግብ እርዳታ በከፍተኛ መጠንና በተቀናጀ ሁኔታ ከታቀደለት አላማ ውጪ ጥቅም ላይ ውሏል ሲሉ መክሰሳቸው ይታወሳል።
መንግስት በበኩሉ፤ በአገሪቱ እየተካሄዱ ባሉ ግጭቶችና በድርቅ ምክንያት እርዳታን የሚሹ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች  ባሉበት ሁኔታ  የእርዳታ አቅርቦቱ እንዲቋረጥ መደረጉ ሚሊዮኖችን ለችግር የሚዳርግና ለቀውስ የሚያጋልጥ፣ ተቀባይነት የሌለው ፖለቲካዊ እርምጃ ነው ሲል ተቃውሞውን አሰምቶ ነበር።
የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) ፣ ያቋረጠውን የምግብ እርዳታ፣ የእርዳታ አቅርቦቱ ሥርዓት አስተማማኝ መሆኑ ከተረጋገጠ  መልሶ እንደሚጀመር ማስታወቁ ይታወሣል። በዚሁ መሠረትም   ድርጅቱ  ባወጣው መግለጫ፤ አሁን እርዳታ መልሶ ለመጀመር መወሰኑን ያሳውቅ እንጂ፤ አቅርቦቱ ለስደተኞች ብቻ የሚቀርበውን የሚመለከት መሆኑን ገልጿል።
ድርጅቱ እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው የኢትዮጵያ መንግሥትና አጋሮቹ፣ የስደተኞች የምግብ እርዳታ አቅርቦት መዋቅር ላይ ለውጦችን በማድረጋቸው መሆኑን ጠቅሶ፣ “የኢትዮጵያ መንግሥት የስደተኞች የምግብ እርዳታን የማጓጓዝ፣ የማከማቸትና የማሰራጨት ኃላፊነትን ለሌሎች አጋሮች በማስተላለፉ” መሆኑንም አመልክቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት አሁንም የምግብ ዕርዳታ ለትክክለኞቹ ተረጂዎች እንዲደርስ ተጨማሪ ማሻሻያዎችን እንዲያደርግ ድርጅቱ መጠየቁን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።
 በእርዳታ ስርጭቱ ላይ የተደረገው ለውጥ አቅርቦቶችን በትክክል ለተጠቃሚዎች መድረሳቸውን ለመቆጣጠር በሚያስችል ሁኔታ መሆኑንም ድርጅቱ አስታውቋል።
ዩኤስኤአይዲ ለስደተኞች የሚቀርበው እርዳታ እንደሚጀመር ባሳወቀበት በዚህ  መግለጫው፣ “የምግብ እርዳታ በሚያስፈልግባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ድጋፉ ለታለመላቸው ተጠቃሚዎች እንደሚደርስ ማረጋገጫ እስክናገኝ ድረስ ተቋርጦ ይቆያል” ብሏል። የምግብ እርዳታው ቢቋረጥም የጤና እና የአልሚ ምግቦች እርዳታዎችን ጨምሮ ሌሎች የአሜሪካ መንግሥት የእርዳታ አቅርቦቶች ግን ይቀጥላሉ ተብሏል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ በግጭትና በድርቅ ምክንያት የእርዳታ ድጋፍን የሚሹ ወደ 20 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች እንዳሉ ይነገራል።
 

Read 1057 times