Saturday, 07 October 2023 20:27

"ምን እንዳይመጣ!..."

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

 “ስሙኝማ… ከእነዚህ  ከ‘አለቆቻችን ፈረንጆች’ ነገረ ሥራ ደስ የሚለኝ መብታቸውን ሲያስከብሩ የሚሏት ነገር ነች። "አይ ፔይ ማይ ታክስስ፣" ይላሉ። “ያው ታክስ ስለምከፍል አገልግሎት ማግኘት መብቴ ነው" ነገር መሆኑ ነው። ልጄ እኛ አገር የሆነ ቢሮ "ታክሴን እከፍላለሁ…" ብትሉ የሚሰጣችሁ መልስ "እና ምን ይጠበስ?" የሚል አይነት ቢሆን ነው።--”
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ… እንዲሁ ‘ግንባር’ አይቶ የሚያበድር ባንክ ከተገኘ… ሰሞኑን የሆነ ማሰልጠኛ ነገር ለመክፈት እቅድ አለኝ። እናላችሁ ‘የዓይኔ ቀለም ደስ’ ብሎት የሚያበድረኝ ባንክ ካለ… የሆነ ማሰልጠኛ እከፍታለሁ ብያለሁ…ለ‘ፕሮሞሽኑ’ ምን ችግር አለው። "ከሚመለከተው ክፍል ቅድመ- እውቅና ለማግኘት በሂደት ላይ ነን" ማለት ነው። የምር ይቺ  ‘ቅድመ እውቅና’ የሚሏት … ነገር ቀላል ፈጠራ አይደለችም! ‘ሰፋ’ አድርጎ ለመጠቀም በር ይከፍትልናል። [እንትናዬ…‘እስክትወስኚ’ ድረስ… ቅድመ እሺታሽን ብትነግሪኝ!]
ስሙኝማ… ዘንድሮ አንድ በየቦታው ‘ባህል’ እየሆነ የመጣ ነገር ያለ ይመስለኛል። አለ አይደል.. ልክ በቃ ሁላችን ገና ‘ያልነቃን’ ዓይነት ነገር እያደረጉን ነው። የሆነ ነገር ቢያበላሹባችሁ… የሆነ አገልግሎት ቢነፍጓችሁ… በ‘ጮሌነት’ ኪሳችሁን ቢያሳሱላችሁ… "አቤት" የሚባልበት የጠፋ ነው የሚመስለው።
አሁን ለምሳሌ መአት ‘ማሰልጠኛዎች’ አሉ… ከመሃላቸው መአት አሪፎች አሉ። አልፎ አልፎ ደግሞ… አለ አይደል… ‘አሪፍ ያልሆኑ’ አሉ። ተማሪ ከፍሎ ተመዝግቦ ስልጠና ከተጀመረ በኋላ… በየሰበቡ ተጨማሪ ክፍያዎች ይመጡላችኋል። ተሜ ደግሞ "ለምን መጀመሪያ አትነግሩንም። አሁን ከየት ልናመጣ ነው?" ሲልላችሁ… "ካልከፈላችሁ ሰርተፍኬት አታገኙም!" ይባላል። በቃ’ኮ "ሰማይ ብትቧጥጡ… ምን እንዳታመጡ ነው!" አይነት ነገር ነው።
የምር የሚገርም ነገር ነው። ይቺ  "ምን ታመጣላችሁ?" አቀራረብ ያልገባችበት የለም።
አሁን እዚህ አገር የሙዚቃ ዝግጅቱ መዓት ነው። እናላችሁ "የጨዋ…" ዝግጅቶች ያሉ ያህል.. አለ አይደል… ይሄ የአራዳ ልጆች "የነፈሰበት…" የሚሉት ዓይነት ብልጠት አለላችሁ። በየፖስተሩ ላይ ‘ጥይት’ የተባሉ ዘፋኞች ይደረደሩላችሁና… ህዝቤ እነሱን ለማየት አዳራሽ ይሞላል። ‘የጎበዝ’  አገር አይደል… ‘ታላቁ’ ‘ዝነኛዋ’ የተባሉት ሁሉ በዛው ጭልጥ። "ተመልካቾቻችን ይቅርታ… እንትና የተባለ ድምጻዊ በችግር ምክንያት ሊገኝ አልቻለም…" ይባልላችኋል። እና በምትኩ "ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም…" በሚለው መመሪያ ‘ማይክ’ የጨበጡ ይመጡላችኋል። እና… ነገርዬው "ግፋ ቢል ፉጨት እንጂ…ምን እንዳታመጡ" መሆኑ ነው።
እኔ’ኮ የምለው… በፊት’ኮ አለ አይደል… የሆነ ሰው ሊያስፈራራችሁ ሲሞክር… ወይ "ከሷ ጋር ሻይ መጠጣት ብትተው ይሻልሃል…" ብሎ ሲዝትባችሁ… "ምን እንዳታመጣ!" ትላላችሁ። ዘንድሮ የጨዋታው ህግ ተለውጦ… እንኳን ሳንፎክር… እየተፎከረብንም "ምን እንዳታመጡ ነው!" ይሉናል።
እዚህ እኛ ዘንድ… ዋጋ ለመጨመር ምንም ‘ዲማንድ ኤንድ ሰፕላይ’ ቅብርጥስዮ የሚባል ቀለም ቀለም የሚሸት ነገር አያስፈልግም። በቃ…‘ደስ ያለው’ መጨመር ይችላል። "እንዴ… እንደፈለጋችሁማ ልትቆሉሉብን  አትችሉም…" ቢባል መልሱ "ምን እንዳታመጡ!" ነው። የምር አይገርማችሁም… ልክ’ኮ በቃ ‘እጅና እግራችን በስውር ገመድ የታሰረ’ ነው የሚመስለው።
ስሙኝማ… የአዲስ አበባ ሰዎች፣ … መቼም የምናየው ነገር አናጣም! አሁን አንዳንድ ጊዜ ታርጋቸው የግልም፣ የመንግስትም ያልሆኑ ‘ሌላ ታርጋ’ መኪናዎች በሞቀው ከተማ… የተከለከለ ቦታ አቁመው ምናምን ታያላችሁ - ትራፊክ እያለ። እና… ይሄ ምን ማለት ነው! ነገርዬው ያው "የፈለግንበት ብንገትረውስ… ምን እንዳታመጡ!" መሆኑ ነው።
እና… አለ አይደል ግርም ነው የሚላችሁ። እኔ መቼም ‘ጉልበተኛ’ ሲበዛ… አለ አይደል… ጥሩ ምልክት አይመስለኝም። አሃ ተቸገርና! አሁንም አንዳንድ መሥሪያ ቤት ይሄ የሻይ ሰዓት የሚሉት ነገር አለ አይደል… ምንም አይሻሻል። ተገልጋዩ በሁለትና በሦስት ረድፍ ተኮልኩሎ የሚመለከተው ሰራተኛ፣ ሻይ ጠጥቶ ለመምጣት 1 ሰዓት ይፈጅበታል። ሲመጣ ደግሞ… ምን አለፋችሁ… የአንድ አውራጃ ህዝብ ግብር የጠራ ባላባት ነው የሚመስለው። ትንሽ’ኮ ፍርሃት የለም። "ለኔ ሲል ለምን ሳምንት ተሰልፈው አይከርሙም… ምን እንዳያመጡ ነው" ዓይነት ነገር ነው።
አሃ… እዚህ መብት መጠየቅ አልተለመደማ። እንዲያውም አንዳንዱ መብቱን ለማስከበር ተቃውሞ ቢያነሳም  "ኧረ ዝም በል… ጭርሱን  ቆልፎብን እንዳይሄድ!" የምንል ዓይነት አለን፡፡ እናላችሁ!... "ምን እንዳያመጡ ነው…" የሚሉንን ያህል፣ ብዙዎች "ምን እንዳናመጣ ነው…" ብለን ‘እጅ የሰጠን’ ነው የሚመስለው።
ስሙኝማ… ከእነዚህ  ከ‘አለቆቻችን ፈረንጆች’ ነገረ ሥራ ደስ የሚለኝ መብታቸውን ሲያስከብሩ የሚሏት ነገር ነች። "አይ ፔይ ማይ ታክስስ፣" ይላሉ። “ያው ታክስ ስለምከፍል አገልግሎት ማግኘት መብቴ ነው" ነገር መሆኑ ነው። ልጄ እኛ አገር የሆነ ቢሮ "ታክሴን እከፍላለሁ…" ብትሉ የሚሰጣችሁ መልስ "እና ምን ይጠበስ?" የሚል አይነት ቢሆን ነው። [ከ‘አራድነት’ ጋር ላለመላቀቅ ትግል ላይ ያለነው "አይ ፔይ ማይ ታክስስ" ቢሉን… አለ አይደል… ምን እንል መሰላችሁ… "እሱን ስትገረፍ ታወራዋለህ!" ኧረ እዛም፣ አንደርስ… ‘ከተቆጡን’ ይበቃናል!]
አሁን ለምሳሌ… የሆነ ሆቴል ቤት "ምግብ በአዲስ መልክ ማዘጋጀት ጀምረናል…" ምናምን ሲል ስትገቡ… ያው ‘አሮጌ’ ምግብ በ‘አሮጌ’ ሳህን ታገኛላችሁ። ሳልናገር አልተውም ብላችሁ "ጣዕሙ ትክክል አይደለም …" ብትሉ "አይ የኔ ጌታ… ካልጣፈጠህ መተው ትችላለህ" ዓይነት መልስ ብታገኙ ነው። ይኸው ነዋ… ነገርዬው "ባይጣፍጥስ… ምን እንዳታመጣ ነው!" መሆኑ ነው።
እናላችሁ… እንዲህ ‘ተናንቀን’ … "ምን እንዳያመጣ ነው!" እየተባባልን… መጨረሻችን አይናፍቃችሁም! [በቀደም አንድ ወዳጄ ምን አለኝ መሰላችሁ…"አይተህ እንደሁ… ሰው ፊት ለፊት መተያየት ትቶ ሲያወራም እንደ ኳስ የማዕዘን ምት በጎን እያየ ነው።" እስቲ ጥናት እናካሂዳለን!] ብቻ የሆነ የጎደለ ነገር አለ። ‘አለቆችም’ አንድ ነገር ሲያዙን፣ "ኧረ ጊዜ ስጡን…" ስንል ጡንቻቸውን አምጥተው ማጅራታችን ላይ ያጋድሙታል። ያው "ምን እንዳታመጡ ነው!" መሆኑ አይደል። አለ አይደል በየቦታው አለምክክር ባለከረባቶቹ ከላይ ሆነው ታች ወዳሉት ባለጃኬቶች የሚወረውሩት ‘መመሪያ’ ምናምን… ያው "ባይደግፉትስ… ምን እንዳያመጡ ነው!" ነገር መሆኑ ነው።
ስሙኝማ… አንድ ወዳጄ ምን አለኝ መሰላችሁ? "ሰሞኑን የምትጽፈው ሁሉ ምርር እያለህ ነው… ተስፋ ቆረጥክ እንዴ!" የኔ መልስ ደግሞ ምን መሰላችሁ… ተስፋ ብቆርጥ ባልቆርጥ… ምን እንዳላመጣ ነው!" [ቂ...ቂ…]
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 896 times