Saturday, 23 September 2023 21:13

በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው የሰዎች ማቆያ ስፍራ እያወዛገበ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

- ኢሰመኮ በክልሉ ገላን ከተማ ውስጥ በሚገኘው ጊዜያዊ የሰዎች ማቆያ ስፍራ በተላላፊ በሽታ
ሰዎች እየሞቱ መሆናቸውን ገልጿል
- የኦሮሚያ ክልል በበኩሉ በክልሉ ምንም አይነት የሰዎች ማቆያ ስፍራ የለም ብሏል

በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ገላን ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ጊዜያዊ የሰዎች ማቆያ ስፍራ ውስጥ በተቀሰቀሰ ተላላፊ በሽታ ሰዎች መሞታቸውንና ከ190 በላይ የሚሆኑ ደግሞ የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታውቋል፡፡
በማቆያ ስፍራው ከሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል 3 ሰዎች በተላላፊ በሽታ ሳቢያ ህይወታቸው ማለፉን የጠቆመው ኮሚሽኑ፣ 3 ሰዎች ደግሞ በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ እንደሚገኙና 190 የሚሆኑት የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሆነ አመልክቷል፡፡ የኦሮሚያ ክልል በበኩሉ፤ ይህንኑ በሰበአዊ መብቶች ኮሚሽን የተሰጠው መረጃ ያልተረጋገጠና ሃሰተኛ መረጃ ነው ሲል አጣጥሎታል፡፡
ኮሚሽኑ ሰሞኑን ይፋ ባደረገውና በነሐሴ 24፣ ጳጉሜ 2 እና 3/2015 ዓ.ም በሸገር ከተማ ሲዳ አዋሽ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው የማቆያ ስፍራ ተገኝቼ አደረኩት ባለው ቅኝት፤ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ አረጋዊያን ሴቶችና ህፃናት እንዲሁም አካል ጉዳተኞች በስፍራው ማየቱን ጠቁሟል፡፡
ኮሚሽኑ በስፍራው ከየሚገኙ የህክምና ባለሙያዎችን፣ የማዕከሉን አስተባባሪዎችና በጥበቃ ስራ ላይ የተሰማሩ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላትን በማነጋገር አገኘሁ ባለው መረጃ መሰረት፤ በስፍራው ከነበሩት ሰዎች መካከል የሞቱ፣ ፅኑ ህክምና ክፍል የገቡና ህክምና የሚደረግላቸው ዜጎች መኖራቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
ኢሰመኮ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫው፣ ይኸው በገላን ከተማ ውስጥ የሚገኘው የማቆያ ማእከል ለሰዎች መጠለያ ወይንም ማቆያ ስፍራ እንዲሆን የተዘጋጀ አለመሆኑን ይልቁንም ለኢንዱስትሪ ዕቃዎች ማከማቻ የሚያገለግል መሆኑን ማየቱንና በማቆያ ማዕከሉ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች በቀን ሶስት ጊዜ ምግብ እንደሚቀርብላቸውና የመጠጥ ውሃም እንደሚያገኙ ጠቁሟል፡፡
ስፍራው ለግል ንፅህና መጠበቂያ የሚሆን የውሃና የንጽህና መጠበቂያ አቅርቦት የመኝታ አልጋና ፍራሽ አልባሳት የሌለው፣ በቂ አየርና የፀሀይ ብርሃን የማያገኝና ከፍተኛ የንፅህና ጉድለት ያለበት ስፍራ መሆኑንም ገልጿል። በገላን ከተማ ከሚገኘውና በኮሚሽኑ ቅኝት ከተደረገበት ከዚህ ማቆያ ሌላ ሌሎች በተለያዩ ስፍራዎች የሚገኙ የማቆያ ቦታዎች መኖራቸውን ኮሚሽኑ አመልክቷል፡፡
ይህንኑ በኮሚሽኑ የቀረበውን መግለጫ የኦሮሚያ ክልል “እውነትነቱ ያልተረጋገጠ ሀሰተኛ መረጃ ነው” ሲል አጣጥሎታል፡፡
ክልሉ ሰሞኑን ባወጣው ማስተባበያ፤ በክልሉ በሸገር ከተማም ሆነ መሰል አካባቢዎች ምንም አይነት የማቆያ ስፍራ የለም ብሏል፡፡
ኢሰመኮ በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ከተሞች ተመለከትኳቸው ባለው የሰዎች ጊዜያዊ የማቆያ ስፍራዎች ላይ ያለውን የሰዎች አያያዝ ሊስተካከል የሚገባውና አደገኛ መሆኑንም አመልክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ በአሁኑ ወቅት በማዕከሉ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን አያያዝ ለማሻሻልና ሰብአዊ ክብርና አያያዝን ለማረጋገጥ የሚያስችል በቂ የምግብ፣ የመጠጥ ውሃና የመኝታ እንዲሁም የንፅህናና የህክምና አገልግሎቶችን በአፋጣኝ ማሟላት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ሲል አሳስቧል፡፡
ዜጎችን በግዳጅ ወደ አንድ የማቆያ ማእከል ማስገባት የሰብአዊ መብት ጥሰትን እንደሚያስከትል የገለፀው ኮሚሽኑ፤ ይህ አስገዳጅ አሰራር በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል ብሏል በመግለጫው፡፡


Read 2361 times