Saturday, 23 September 2023 21:09

ጎርፍ በጋምቤላ በርካታዎችን ማፈናቀሉ ተገለጸ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በጋምቤላ ክልል የባሮ ወንዝ ሞልቶ ባስከተለው ጎርፍ፣ በጋምቤላ ከተማና በዘጠኝ ወረዳዎች በርካታ ሰዎችን እንዳፈናቀለ፣ የክልሉ መንግሥት ባለፈው ማክሰኞ አስታውቋል፡፡
የጋምቤላ ከተማ ጤና ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የከንቲባው ተወካይ አቶ ሳይመን ቲያቺ፣ ባለፉት አራት ቀናት ውስጥ ስድስት ሺ  የሚደርሱ ሰዎች ተፈናቅለው በትምህርት ቤቶችና በደረቃማ አካባቢ ላይ እንደሚገኙ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል።
በደረሰው የጎርፍ አደጋ ንብረት እንደወደመና በእንስሳት ላይም ጉዳት እንደደረሰ የጠቆሙት የከንቲባው ተወካይ አቶ ሳይመን፤ እስካሁን በጎርፉ የሰው ህይወት አለማለፉን ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይና የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ኡሞድ ኡሞድ  በበኩላቸው፣ የክልሉ ህዝብ ወንዞችን እየተከተለ የሰፈረ ነው፣ በመሆኑም የባሮ፣ የአልዌሮ፣ የጊሮና የአኮቦ ወንዞች በከባድ ዝናብ ምክንያት ሞልተው በመፍሰስ፣ በዘጠኝ ወረዳዎች ውስጥ ጎርፍ ማስከተላቸውን ገልጸዋል፡፡
አቶ ኡሞድ እንዳሉት፤ በኑዌር ዞን አምስቱም ወረዳዎች፣ የክልሉን ዋና ከተማ ጨምሮ በጎርፉ እጅጉን ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ የ01፣ 02፣ 04 እና 05 ቀበሌዎች ነዋሪዎች በጎርፉ ከብቶቻቸውንና ንብረቶቻቸውን አጥተዋል፡፡ የባሮ ወንዝ መጨመር ተጨማሪ የአደጋ ስጋት መደቀኑን የቀጠለ ሲሆን፤ መንግሥት ለችግሩ ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠው ነዋሪዎች ጠይቀዋል።
በጋምቤላ ከተማ የተከሰተው ጎርፍ በዚህ መጠን ህብረተሰቡን ያፈናቀለው ከ15 ዓመት በፊት በ2000 ዓ.ም እንደነበር ያስታወሱት አንድ የከተማው ነዋሪ፤ የባሮ ወንዝ በሞላ ቁጥር ዳግም ህብረተሰቡን እንዳያፈናቅል መንግስት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ መሠረት፤ ባለፈው ዓመት ከነሐሴ ወር መጀመሪያ አንስቶ እስከ ጥቅምት ወር የጣለውን ከፍተኛ ዝናብ ተከትሎ፣ በ12 ወረዳዎች እንዲሁም በጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት ዋና ከተማ በተከሰተው ጎርፍ 76ሺ631 ሰዎች ለጉዳት ተዳርገው ነበር፡፡
በተመሳሳይ፣ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች፣ የክረምቱ ዝናብ የሚያስከትለው ጎርፍ፣ ከ270ሺሕ በላይ ሰዎች ላይ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ(ኦቻ) ባለፈው ሳምንት  አመልክቷል።





Read 1918 times