Saturday, 16 September 2023 00:00

ሀገሬ ምን ተባልሽ - ልብ ያለው ልብ ይበል!

Written by  ቶማስ በቀለ
Rate this item
(1 Vote)

ይቺ ሀገራችን ብዙ ተብሎላታልም፤ ብዙ ተወርቶባታልም፤ ሀገሪቱ በቅኝ ያልተገዛች ብቸኛ ሀገር (ላይቤሪያን ጨምሮ) ከመሆኗ አኳያ የሚነገርላት ብዙ ጥሩና የሚገርሙ ነገሮች ያሉትን ያህል ከረሀብ፤ ከጦርነትና ከድህነት ጋር ተያይዞ ደግሞ ክብረ-ነክና አሳዛኝ የሆኑ ነገሮች ሲነገሩ እንሰማለን፡፡ እስቲ ከነዚህ ጉዳዮች ለአጠቃላይ ግንዛቤ ሁለቱን በዚህ አጭር ፅሁፌ ውስጥ አንስቼ በነሱ ላይ የተወሰኑ ሀሳቦች ልስጥ።
እርዳታ፡
በኢኮኖሚ ያደጉ ሀገራት ላላደጉት የአለም ሀገራት የተለያዩ አይነት እርዳታዎች እንደሚሰጡ ይታወቃል፡፡ ፅሁፌ በሁለቱ ላይ ማለትም ለኢኮኖሚ ዕድገት የሚጠቅም ዕርዳታ (Development aid) እና ለዕለት ፍጆታ የሚውል ዕርዳታ (Subsistence aid) በሚባሉት ላይ ያተኩራል፡፡ ይህን ታሪክ የሰማሁት በ1990ዎቹ መገባደጃ ላይ ነው፡፡ ስለ ዕርዳታ አይነቶች በተለይም “Development aid” እና “Subsistence aid” በተባሉት የእርዳታ አይነቶች ላይና ለማን እንደሚሰጥ የሚወያይ ከምዕራብ ሀገራት በአንዱ በተካሄደ ብዙ ሀገራትን ያሳተፈ አንድ ትልቅ ስብሰባ መካሄዱን አንድ ጓደኛዬ አጫወተኝ፡፡ ከዚያም ጓደኛዬ ጨዋታውን እንዲህ ቀጠለ፤ “በስብሰባው ላይ “Development aid” እና “Subsistence aid” ስለተባሉ የዕርዳታ አይነቶች በሰፊው ማብራሪያ ተሰጠ፤ በመቀጠልም የትኞቹ ሀገራት የትኛውን የዕርዳታ አይነት እንደሚሰጣቸው በአጭሩ ማብራሪያ ተሰጠ፤ በስብሰባው ላይ ከኢትዮጵያ የተሳተፉ ተወካዮች ነበሩ፤ በአጋጣሚ የኢትዮጵያ ስም በስብሰባው ላይ አልተነሳም፤ በመሆኑም በውይይቱ ሰአት ከኢትዮጵያ ከሄዱ አንዱ ተወካይ እጁን አነሳ፤ ተራው ሲደርስ ሀሳቡን እንዲያቀርብ እድል ተሰጠው፤ ከዚያም እጁን ያነሳው ተወካይ “ስለ “Development aid” እና “Subsistence aid” የተሰጠን ማብራሪያ ጥሩ ግንዛቤ እንድናገኝ ረድቶናል፤ የትኞቹ ሀገራት የትኛውን አይነት ዕርዳታ እንደሚያገኙ ተገልፆልናል፤ ከተጠቀሱት ሀገራት ውስጥ ግን ኢትዮጵያ የለችም፤ እውነታው ግን ኢትዮጵያ የሚሰጣት “Subsistence aid” ነው፤ በሱ በኩል ችግር የለብንም፤   “Development aid” ግን አግኝታ አታውቅም፤ ሁልጊዜ “Subsistence aid” እየሰጣችሁን ከምናስቸግራችሁ “Development aid” ሰጥታችሁን ኢኮኖሚያችን እንዲያድግ ብታደርጉ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት አይሆንም ወይ?” የሚል መንፈስ ያለው ጥያቄ ጠየቀ፡፡ ከዚያም ዋናው አወያይ ፈረንጅ ቀበል አደረገና ፍርጥም ብሎ፤ “Excuse me sir, we don’t want to create another Japan” በአማርኛ ሲተረጎም “ይቅርታ አድርጉልኝ ጌታው፤ ሌላኛዋን ጃፓን መፍጠር አንፈልግም” አለው ብሎ አጫወተን፡፡
አንባቢ የሰብሳቢውን አባባል በጥሞና እንዲመረምር እፈልጋለሁ፤ ምን ማለቱ ነው? ለምን ኢትዮጵያ ከጃፓን ጋር ተወዳደረች? ለምን ኢትዮጵያ እንደ ጃፓን እንድታድግ አልተፈለገም? ምን አስፈራው? ይህ ለኛ ስለ ኢትዮጵያውያን ምን ይነግረናል? ሀገራችን በቅኝ የተገዛች ሀገር አይደለችም፤ ህዝቡ ከነኩት የጦረኝነትና የአትንኩኝ ባይነት ስነልቦና ያለው ነው፤ ጃፓን በሁለተኛ የአለም ጦርነት የጦረኝነት መንፈስ ባላቸው የሚሊታሪ ጀነራሎች የተሞላች ስለነበረ ከጀርመን ናዚና ከጣሊያን ፋሺስት ጋር በማበር የቃልኪዳን ሀገር የተባሉትን አሜሪካ፤ እንግሊዝ፤ ፈረንሳይና ሌሎች ሀገሮችን መውጋቷና በዚህ መነሻነት የአቶሚክ ቦምብ በሂሮሺማና ናጋሳኪ ከተሞቿ ላይ እንደተጣለ በታሪክ ይታወቃል፡፡ በመጨረሻም ሁለተኛው የአለም ጦርነት ተጠናቆ እነ ጃፓን እጃቸውን ከሰጡ በኋላ ምዕራባውያን በተለይም አሜሪካ በእነ ጃፓን ላይ የመሳሪያ ማዕቀብ ስትጥል፤ ለካሳ በሚል ለጃፓን  “Development aid” ሰጠች፤ ጃፓኖቹም በጦርነት ሀሳብ የተሞላ ህሊናቸውን ሙሉ በሙሉ ወደ ኢኮኖሚ ግንባታ በማዞራቸው አሁን የደረሱበት የዕድገት ደረጃ ደረሱ፡፡ በተመሳሳይ ኢትዮጵያም  “Development aid” ካገኘች የማደግ አቅም፤ ማለትም፤ የተፈጥሮና የሰው ሀብት ስላላት ማደግ ትችላለች፤ ይሁን እንጂ በታሪኳ፤ ክብሬን አላስነካም ባይነቷ፤ ለሌሎች ጥቁር ህዝቦች አርዓያ ከመሆን አቅሟና በተለያዩ የፖለቲካ ምክንያቶች የኢትዮጵያ ማደግ ስለማይፈለግ  “Development aid” ማግኘት አልቻለችም፡፡ እንደ ቻይናም በራሷ ጥረት እስካሁን ድረስ ማደግ አልሆነላትም፤ በመሆኑም ሌላውን ትናንሽ ነገር ሁሉ ትተንና ያገኘነውን አጋጣሚና የራሳችንን ጥረት ተጠቅመን ከድህነት የምንወጣበት መንገድ ላይ ብናተኩር ያዋጣናልና ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡
ጦርነት፡
በአለማችን ላይ የተካሄዱ  ሁሉም ጦርነቶች ከጥፋት፤ ከውድመትና ከሰቆቃ ውጪ የፈየዱት ምንም ጥሩ ነገር እንደሌለ ታሪክ በተደጋጋሚ ያረጋገጠው ሀቅ ነው፡፡ ምናልባት ኢትዮጵያ ከጣሊያን ጋር ያደረገችው ዓይነት ጦርነት ከተወራሪው ማለትም ከኢትዮጵያ አንፃር ሲታይ ትክክለኛ ጦርነት (just war) ነው ቢባልም፣ ጦርነት ነውና የመጨረሻው ውጤቱ ግን በሰቆቃ የተሞላ እንደነበረ ይታወሳል፤ በአንዱ ወገን በሚታይ ጀብደኝነት ወይም ተቀራርቦ ባለመወያየት ምክንያት በሚፈጠሩ ጦርነቶች አለማችን ቁም ስቅሏን ማየቷ አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡
እስቲ ከአደጉ ሀገራት በአንዱ ውስጥ በተደረገ ዓለማቀፍ  ስብሰባ ላይ ስለተነሳ አንድ ጉዳይ ላጫውታችሁ፤ ስብሰባው የሶስተኛ አለም ሀገሮች በኢኮኖሚ ያላደጉት ለምንድነው? በሚለው ርዕስ ላይ በአለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂነት ያላቸው ባለሙያዎች በሶስተኛ ዓለም ሀገራት ላይ ተመድበው (አንድ ባለሙያ ለአንድ ሀገር) ዝርዝር ጥናት ካደረጉ በኋላ የባለሙያዎቹ ሪፖርት የሚሰማበት ስብሰባ ነበር፡፡ ይህንን ታሪክ የሰማሁት በ1988 ዓ.ም. ነበር፡፡ በጥናቱ ውስጥ ከተካተቱት የሶስተኛ ሀገራት ውስጥ አንዷ የኛው ኢትዮጵያ ነበረች። በመቀጠል በጥናቱ ውስጥ የተካተቱት ሀገሮች ሪፖርት አንደ በአንድ መቅረብ ጀመረ፤ በመሀከል የኢትዮጵያ ተራ ደረሰ፤ በኢትዮጵያ ላይ ጥናት አድርጎ ሪፖርት ያዘጋጀው ባለሙያ  ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ማደግ ያልቻለችበት ምክንያቶችን አንደ በአንድ ካቀረበ በኋላ ከምክንያቶቹ ዋናው ብሎ ያቀረበውን ምክንያት በሚቀጥለው አኳኋን ገለፀ፤ “ኢትዮጵያ ባለፉት 800  አመታት ውስጥ በየትኛውም ጊዜ ለአንዲት 10 ተከታታይ አመታት እንኳን ከጦርነት ነፃ የሆነችበት ጊዜ የለም፤ ጦርነት ባለበት ቦታ ደግሞ የኢኮኖሚ ዕድገት አይታሰብም፤ በመሆኑም ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ያላደገችበት ዋና ምክንያት ታሪኳ በተለያዩ ጦርነቶች የተሞላ በመሆኑ ነው፤” ብሎ ሪፖርቱን ማጠናቀቁን ጓደኛዬ አጫወተኝ፡፡
ይህን ታሪክ ስሰማ ገረመኝ፤አዘንኩም፡፡ በእርግጥ የኢትዮጵያ ታሪክ በጦርነቶች የተሞላ ታሪክ እንደሆነ አውቀዋለሁ፤ በጣም የገረመኝ ግን በስምንት መቶ አመት ውስጥ በየትኛውም ጊዜ ለአንዲት 10 ተከታታይ አመታት እንኳን ከጦርነት ነፃ የሆነችበት ጊዜ የለም የሚለው እውነታ ነው፤ ያስደነግጣል! ከላይ እንደገለፅኩት ይህን ታረክ የሰማሁት በ1988 ዓ.ም. ነው፤ በ1983 ዓ.ም. ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ከሻዕቢያና ህወሓት ጋር ይደረጉ የነበሩ ጦርነቶች በመቆማቸው ታሪኩን እስከሰማሁበት ጊዜ ድረስ፤ ለአምስት አመታት፤ ሀገሪቱ በአንፃራዊነት በሰላም ውስጥ ነበረች፤ እና ከ800(ስምንት መቶ) አመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለ10 ተከታታይ አመታት ከጦርነት ነፃ ልትሆን ነው ብዬ በጉጉት እየጠበቅሁ እያለሁ በሚያሳዝን ሁኔታ በስምንተኛው አመት፤ ማለትም በ1991 ዓ.ም. ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ውስጥ ገባች፤ በመቀጠል በ1997 ዓ.ም. በተፈጠረው የምርጫ ሸፍጥ መነሻነት በሀገሪቱ ትርምስ ተፈጥሮ የተወሰኑ ወገኖች ነፍጥ ይዘው ጫካ ገቡ፤ ከ1991 ዓ.ም. የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ካበቃ በኋላም አስር አመት ሳይሞላው ወደ ጦርነት መግባታችንን አንባቢ ልብ ይበል፡፤ ከዚያም ነፍጥ ያነሱት በሽምቅ ውጊያቸው ላይ እያሉ በ2008 ዓ.ም. በወያኔ ስርዐት ላይ የተፈጠረው ተቃውሞ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ በሂደት በ2010 ዓ.ም. የሪፎርም ለውጡ ተካሂዶ ለአንድ አመት ከምናምን ያህል ሰላም ካገኘን በኋላ በተለያዩ አካላት የሚታገዘው ሸኔ በየቦታው ችግር መፍጠር ጀመረ፤ በሪፎርም ለውጡ የፈላጭ ቆራጭነት ስልጣኑን የተነጠቀው ህወሓት በ27 አመት የስልጣን ዘመኑ ያጠራቀመውን መሳሪያና ከሌሎች የሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር ከፌዴራል መንግስቱ ጋር ጦርነት ከፍቶ ለሁለት አመታት ያህል መከራችንን አየን፤ ከህወሓት ጋር በፕሪቶሪያ ከተደረገው የሰላም ስምምነት አንስቶ ለተወሰኑ ወራቶች እፎይ ካልን በኋላ የአማራው ፋኖ ጥያቄዎቼ አልተመለሱም በሚል በፌዴራል መንግስቱ ላይ ጦርነት ከፈተ፤ አሁንም አንባቢው ልብ እንዲለው የምፈልገው ነገር እስካሁን፤ ማለትም፤ እስከ 2015 ዓ.ም. መገባደጃ ቀናቶች ድረስ ሀገራችን ለአንዲት አስር አመታት ጊዜ ያህል እንኳን ሰላም አጥታ የመከራ ጊዜዋን እየገፋች መሆኑን ነው፡፡
በአሁን ወቅት ሁላችንም፤ በተለይ መንግስት፤ ተቃዋሚ ወገኖች፤ የተለያዩ ሚዲያዎችና አከቲቪስቶች ምን እያደረግን  እንደሆነ ቆም ብለን የምንመረምርበት ጊዜ ላይ የደረስን ይመስለኛል። (እዚህ ውስጥ ህዝቡን (The silent majority የሚባለውን) ማስገባት አልፈልግም፤ ምክንያቱም እሱ በብሄር፤ በሀይማኖትና በተለያዩ ነገሮች ሳይከፋፈል ተደጋግፎ፤ ተቻችሎና ተዛዝኖ የመኖር የቆየ ባህሉን ይዞ እየተጓዘ እንደሆነ ስለማውቅ ነው፤ ማለትም የሚባላው ኤሊቱ ነው፤ የሚያሳዝነው ግን በአንድ ወይም በሌላ መንገድ በኤሊቱ መባላት ገፈት ቀማሹ ህዝቡ መሆኑ ነው፤) ከዚህ በላይ እንደጠቀስኩት፣ የኢትዮጵያን ታሪክ የመረመረው ባለሙያ፣ ኢትዮጵያ  ባለፉት 800 አመታት ውስጥ በየትኛውም ጊዜ ለአንዲት 10 ተከታታይ አመታት እንኳን ከጦርነት ነፃ የሆነችበት ጊዜ የለም ያለውን ታሪክ፣ አሁን ያለው ትውልድ በ1988 ዓ.ም. ላይ 27  አመት ጨምሮ ኢትዮጵያ  ባለፉት 827 አመታት ውስጥ በየትኛውም ጊዜ ለአንዲት 10 ተከታታይ አመታት እንኳን ከጦርነት ነፃ የሆነችበት ጊዜ የለም ወደሚለው ታሪክ ለውጦታል፡፡ ይሄ ነው ለሀገራችን የሰጠናት የዘመኑ ስጦታ!
ታዲያ ምን እያደረግን ነው? አገሪቷን ወዴት እየወሰድናት ነው? ይህ ስራችን አላዋቂ አያስብለንም? ስምንት መቶ ሀያ ሰባት አመታት ባልነው ላይ አሁንም ሌላ አመታት መጨመር እንፈልጋለን? ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አለማደግ ዋናው ምክንያት ጦርነት መሆኑን እያወቅን፤ እየተነገረን የሀሳብ ልዩነቶቻችንን በጦርነት ለመፍታት መሞከራችን ለሀገሪቷ ይበጃል ትላላችሁ? እርስ በርስ በተዋጋንበት ጊዜ ሁሉ ህዝብ ከማስጨረስና ሀገር ከማራቆት ውጪ የፈታነው ችግር አለ? (በነገራችን ላይ ይህ ጥያቄ በተለያየ ምክንያት ኢትዮጵያ በብሔርና በሐይማኖት ሳትከፋፈል በአንድነት ወደ ትልቅ የኢኮኖሚና የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል እንዳታድግ የማይፈልጉ ወገኖችን (ካሉ ማለቴ ነው) አይመለከትም፤)፡፡
በመሆኑም ይድረስ ለመንግስት፤ ተቃዋሚ ወገኖችና አክቲቪስቶች፡ የናንተ የሀሳብ ልዩነት ሀገሪቷ ሰላም በመሆኗ ሊመጣ ከሚችለው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ባህል ዕድገት ጋር ሲነፃፀር ኢምንት ነው፤ ይህንን እናንተም ትቀበሉታላችሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ በሌላ አነጋገር ለሀገራችሁ ሰላም ስትሉ የሀሳብ ልዩነቶቻችሁን በማቻቻል (compromise በመደራረግ) በክብ ጠረጴዛ እንደምትፈቱት አምናለሁ፤ ስለዚህ ተጨማሪ ህይወት ሳይቀጠፍና የሀገር ሀብት ሳይወድም፤ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ፤ የሀሳብ ልዩነቶቻችሁን በክብ ጠረጴዛ እንድትፈቱና ወደሰለጠነ የፖለቲካ ባህል እንድታሻግሩን በኢትዮጵያ በሀገራችን ስም እማፀናችኋለሁ፡፡

Read 594 times