Sunday, 03 September 2023 21:31

የትራፊክ አደጋን ይቀንሳል የተባለ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ይፋ ተደረገ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 • አምና ከ400 በላይ፣ ዘንድሮ ከ300 በላይ ሰዎች ህይወት በትራፊክ አደጋ ተቀጥፏል - ትራፊክ ፖሊስ


         በአገሪቱ እንዲሁም በመዲናዋ  እየተከሰተ ያለውን የትራፊክ አደጋ በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል የተባለ በተሽከርካሪዎች  ላይ የሚገጠም አውቶማቲክ አደጋ ጠቋሚ መሳሪያ ይፋ ተደረገ።
አዲሱ የቴክኖሎጂ ፈጠራ የተሰራው አቶ ጎይቶኦም ገ/ዮሐንስ በተባሉ የፈጠራ ባለሙያ ሲሆን፤ በዚህም የፈጠራ ሥራቸው ከአዕምሮአዊ ንብረት ባለስልጣን ፓተንት ማግኘታቸው ታውቋል። ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር እንዲሁም ከአጋር ተቋማትም የድጋፍ ደብዳቤና ዕውቅና አግኝተዋል ተብሏል።
የፈጠራ ባለሙያው አቶ ጎይቶኦም ገ/ዮሐንስ፣ ይህን የፈጠራ ሥራቸውን አስመልክቶ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በሃርመኒ ሆቴል ለባለድርሻ አካላትና ለሚዲያ ባለሙያዎች መግለጫና ማብራሪያ  ሰጥተዋል።
የፈጠራ ባለሙያው በመጀመሪያ ስለ ትራፊክ አደጋ ያብራራሉ፤ ”በተለምዶ አንድ አሽከርካሪ እያሽከረከረ ሳለ ከፊት ለፊቱ ከቀኝ ወደ ግራ የሚያቋርጡ እግረኞች፣ ተሽከርካሪዎች ወይም እንስሳት ሲያጋጥሙት፣ የተሽከርካሪውን ፍጥነት ቀንሶ በመቆም በግራ ስኮፒዮ ሲመለከት በሱ ግራ በኩል ደርቦ የሚመጣ ተሽከርካሪ ካየ፣ ግራ እጁን አውጥቶ በማወዛወዝ፣ በግራ በኩል ደርቦ ለመጣው አሽከርካሪ ፍጥነቱን እንዲቀንስና እንዲቆም በማድረግ፣ ከቆመው ተሽከርካሪ በኩል በሚሻገሩት እግረኞችም ሆነ ተሽከርካሪዎች ላይ አደጋ እንዳይደርስ ያደርጋል፡፡”
ባለሙያው ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉም፤ “ነገር ግን በተቃራኒ በኩል እግረኞችም ሆኑ ተሽከርካሪዎች ከግራ ወደ ቀኝ በሚያቋርጡበት ጊዜ፣ በቆመው ተሽከርካሪ ቀኝ ጎን ደርቦ ለሚመጣው አሽከርካሪ ምልክት መስጠት ስለማይቻል ከ80 በመቶ በላይ በእግረኞች ላይ የሚደርሰው አደጋ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው በቀኝ ጎን ደርቦ በሚመጣ አሽከርካሪ የሚከሰተው  ነው፡፡ ይህም የሚሆነው ልክ እንደ ግራ እጃችን ቀኝ እጃችንን አውጥተን ምልክት ለመስጠት ስለሚያዳግተን፣ እንደ አማራጭ የምንጠቀመው ሃዛርድ ወይም ቀይ ፍሬቻን በማብራት ነው፡፡ ሆኖም በእጃችን የምንሰጠውን ያህል አያግዝም፡፡ በዚህ የተነሳ ደርቦ የሚመጣው ተሽከርካሪ ፍጥነቱን ጨምሮ በመሄድ ከፍተኛ አደጋ ያደርሳል፡፡” ይላሉ፡፡
አዲሱ የፈጠራ ሥራቸው ይህን ችግር ትርጉም ባለው መልኩ እንደሚፈታው የተናገሩት አቶ ጎይቶኦም፤ የቴክኖሎጂ ፈጠራው መኪና ተከልለው በሚሻገሩ እግረኞች ላይ የሚደርስን አደጋ በከፍተኛ ደረጃ ለመከላከል  የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡ ይህ አውቶማቲክ አደጋ ጠቋሚ መሳሪያ፣ በተሽከርካሪው ዳሽ ቦርድ ላይ በቀኝ ወይም በግራ በኩል  የሚገጠም መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ትራፊክ ጽ/ቤትን ወክለው በመግለጫው ላይ የተገኙት ኮማንደር ሙሉጌታ በሰጡት አስተያየት፤ ክቡሩን የሰው ልጅ ህይወት ለመታደግ አንድ ሰው እንዲህ ያለ የፈጠራ ሥራ ይዞ ሲመጣ በእጅጉ ሊመሰገንና ሊታገዝ ይገባዋል ብለዋል።
አምና በመዲናዋ በደረሰ የትራፊክ አደጋ ከ400 በላይ ሰዎች ህይወት መጥፋቱን እንዲሁም ዘንድሮ ከ300 በላይ ሰዎች ህይወት መቀጠፉን የጠቆሙት ኮማንደር ሙሉጌታ፤ የትራፊክ አደጋን በሂደት ዜሮ ማድረግ የምንችለው በዚህ ዓይነት አገር በቀል የቴክኖሎጂ ፈጠራ ብቻ ነው ብለዋል።
ሌላው የትራፊክ ጽ/ቤት ተወካይ በበኩላቸው፤ በዚህ አሁን በተሰራው የቴክኖሎጂ ፈጠራ የትራፊክ አደጋን ሙሉ በሙሉ ባንቀንሰው እንኳን ወደ ግማሽ ልናደርሰው እንችላለን ብለዋል፤ ለፈጠራ ሥራው ባለቤት  ትልቅ አክብሮት እንዳላቸው በመግለጽ፡፡
ከትራፊክ ጽ/ቤት የተወከሉትን ሃላፊዎች ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በአቶ ጎይቶኦም የፈጠራ ክህሎት የተሰራው የቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ የትራፊክ አደጋን በመቀነስ ረገድ እጅግ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው እምነታቸውን የገለጹ ቢሆንም፣ ከፍተኛ ስጋት እንዳላቸውም አልሸሸጉም፡፡ ይኸውም የቴክኖሎጂ ፈጠራው በፋይናንስ እጦት አሊያም በሌላ ምክንያት ተግባራዊ ሳይሆን እንዳይቀር የሚል ነው ስጋታቸው፡፡
የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ከሚኖረው ከፍተኛ አስተዋጽኦ  አንጻር የቴክኖሎጂ ፈጠራው በፍጥነት ወደ ትግበራ መግባት አለበት  ያሉት ባለድርሻ አካላቱ፤ ለዚህም ባለሃብቶችና የሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ ተባብረው ይህን ፕሮጀክት እውን እንዲያደርጉት አበክረው  ጠይቀዋል።
ፕሮጀክቱን በገንዘብ የሚደግፉ አጋሮችን እያፈላለግን ነው ያሉት የፈጠራ ባለቤቱ አቶ ጎይቶኦም በበኩላቸው፤ “አይዲያን ፋይናንስ” የማድረግ አሰራር ለጀመረው የኢትዮጵያ ልማት ባንክም ማመልከቻ ማስገባታቸውን ገልጸዋል።
አሁን 40 ሚ. ብር ብናገኝ በሁሉም ክልሎች  ወደ ትግበራ መግባት እንጀምራለን” ያሉት የፈጠራ ባለሙያው፤ ”ያን ያህል ገንዘብ ካልተገኘ ብለን ግን አንቀመጥም፣ ባገኘነው ያህል የማምረት ሥራ ውስጥ  እንገባለን” ብለዋል።
በመጨረሻም በሰጡት የማረጋገጫ ቃል፤ “ከዚህ በኋላ ይህ ፕሮጀክት ወደ ኋላ  እንደማይመለስ ቃል እገባለሁ፤ ከባለሃብቶችና የፋይናንስ ተቋማት ጋር አጋርነት በመፍጠር ተግባራዊ ይደረጋል” ብለዋል፤ አቶ ጎይቶኦም ገ/ዮሐንስ፡፡

Read 752 times