Sunday, 03 September 2023 21:31

ዳሸን ባንክ ከሁለት የውጭ ባንኮች የ40 ሚ. ዶላር ብድር አገኘ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት (ቢ.አይ.አይ) እና የኔዘርላንድ የሥራ ፈጠራና ልማት ባንክ  (ኤፍ.ኤም.ኦ)  እያንዳንዳቸው 20 ሚሊየን ዶላር፣ በድምሩ 40 ሚሊየን ዶላር ብድር  ለዳሸን ባንክ  ማቅረባቸውን ሰሞኑን  ይፋ አድርገዋል፡፡
 ይህ የብድር አቅርቦት ኢትዮጵያ ለውጪ ገበያ የምታቀርበውን የግብርና ምርት ለማሳደግና በእጅጉ አስፈላጊ የሆነውን የውጪ ምንዛሬ አቅርቦት ለማሻሻል ያስችላል ተብሏል፡፡
ቢ.አይ.አይ እና ኤፍ.ኤም.ኦ ለዳሸን ባንክ ያቀረቡት ብድር፤ በኢትዮጵያ 80% የህብረተሰብ ክፍል በተሰማራበት፣ ለጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት 39% ድርሻ ላለውና ለወጪ ንግዱ 90% አስተዋጽኦ ለሚያበረክተው  የግብርና ዘርፍ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ  ተነግሯል፡፡
የቀረበው ብድር ባንኩ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ ለሚያደርገው ጥረት የበኩሉን እገዛ እንደሚያደርግ የተጠቆመ ሲሆን፤ በተለይ በእርሻ ስራ ላይ ለተሰማሩ ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችሉ ግብአቶችን በማሟላት ከኤክስፖርት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሏል፡፡
የፋይናንስ ተቋማት ትብብር ለግሉ ዘርፍ እድገት ጉልህ ሚና እንዳለው የሚታወቅ ሲሆን፤ በዚህ ትብብር ቢአይአይ እና ኤፍኤምኦ፣. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እ.ኤ.አ በ2021 አዲስ ባወጣው የውጭ ምንዛሪ ማቀላጠፊያ መመሪያ መሠረት፣ በኢትዮጵያ ለሚገኝ የፋይናንስ ተቋም በውጭ ምንዛሪ የቀረበ የረዥም ጊዜ ብድር ሲሰጡ የመጀመሪያዎቹ ናቸው፡፡ ይህ ፋና ወጊ ተግባር ገበያውን በማነቃቃት ከዓለም አቀፍ መዋዕለ-ንዋይ አቅራቢዎች ተጨማሪ ሀብት ለማሰባሰብ የሚያስችል መተማመንን ለመገንባት እንደሚያግዝ ተጠቁሟል፡፡
በዚህ ትብብር ቢአይአይ እና ኤፍኤምኦ ከዳሸን ባንክ ጋር በአመራር ስጋት አስተዳደር፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በማህበራዊና ስርዓተ - ጾታ ዘርፎች ዙሪያ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን በኢትዮጵያ ለማስተዋወቅና ለማስረፅ  በቅርበት ይሰራሉ ተብሏል፡፡
የዳሸን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ ብድሩን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ ”ተምሳሌታዊ በሆነው ቢአይአይ እና ኤፍኤምኦ በትብብር የሰጡን ብድር የውጭ ምንዛሪ ማመንጨት የሚችሉ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ከውጭ የፋይናንስ ተቋማት በኢትዮጵያውያን ባንኮች በኩል ፋይናንስ ማግኘት የሚችሉበትን የብሄራዊ ባንክ መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ ፋና ወጊ በመሆናችን ደስታችን የላቀ ነው፡፡ በውጭ ምንዛሪ የቀረበው ብድር በውጭ ንግድ ላይ የተሰማሩ ደንበኞችን ለማገዝ እንደሚውልና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በእጅጉ የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ባንካችን ከሁለቱ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመስራቱ ለሀገር የሚተርፍ በርካታ ልምድ፣ እውቀትና የአሰራር ዘይቤ ተቀስሟል፡፡ ባንካችን ከሁለቱ የልማት አጋሮቹ ላገኘው ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና አለን።” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ሁለቱ ተቋማት በዳሸን ባንክ ውጤታማነትና በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ላይ ሙሉ እምነት በመጣል የፋይናንስ አቅርቦት በማድረጋቸው፣ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸውም ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡


የቢአይአይ ዋና ስራ አስፈጻሚና የፋይናንሺያል አገልግሎት ኃላፊ ስቴፈን ፕሪስትሊ፤ በአለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ላይ የመጀመሪያዎቹ ተቋማት በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፣ ቢአይአይ በኢትዮጵያ ከ50 አመታት በፊት ኢንቨስት ማድረጉንም አስታውቀዋል፡፡
“በዚህ የፋይናንስ አቅርቦት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየከፈተ ወዳለው ገበያ ቀድመን ለመግባት ከቀዳሚዎቹ ውስጥ በመሆናችን ኩራት ተሰምቶናል፡፡ ባለፉት 50 ዓመታት ቢአይአይ በኢትዮጵያ ቀዳሚ መዋዕለ-ነዋይ አፍሳሽ ሆኖ ቆይቷል፡፡  ከኤፍኤምኦ ጋር የደረስንበት አጋርነት ወደ ኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ በልማት የፋይናንስ አቅራቢዎችና የንግድ መዋዕለ-ንዋይ አንቀሳቃሾች ትብብር ሊመጣ የሚችለውን ከፍ ያለ ሀብት አመላካች ነው፡፡” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የኤፍኤምኦ የፋይናንሺያል ኢንስቲትዩሽን ዲፓርትመንት ዳይሬክተር ማርኒክስ ሞንስፎርት በበኩላቸው፤ “ዳሸን ባንክና  ኢትዮጵያ  የውጭ ቀጥታ መዋዕለ-ንዋይና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እንዲያገኙ በሚያስችለው በዚህ ፈር ቀዳጅ አጋጣሚ በመሳተፋችን ደስተኞች ነን፡፡
በእጅጉ አስፈላጊ የሆነውን በውጭ ምንዛሪ ብድር በውጪ ንግድ ላይ ያተኮረ ግብርና በመደገፍ ለሥራ ፈጠራና በገጠር አካባቢ የፋይናንስ አካታችነትን በማስፈን አስተዋጽኦ ማድረግ ህልማችን ነው፡፡ ለዚህ ታላቅ ትብብር ዳሸን ባንክንና ቢአይአይን እናመሰግናለን፡፡” ብለዋል፡፡





Read 779 times