Saturday, 02 September 2023 00:00

የወርአበባ ኡደት መዛባት

Written by  ሀይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(2 votes)

  የዩኒሴፍ መረጃ እንደሚያሳየው በዓለምአቀፍ ደረጃ 26በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ልጅ መውለድ በሚችሉበት (የወርአበባ በሚያዩበት) የእድሜ ክልል ውስጥ ይገኛሉ። “የወርአበባ በተለየ ሁኔታ በሰው ልጆች(ሴቶች) ላይ የሚከሰት ኡደት ነው” በማለት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊንየም ሜዲካል ኮሌጅ ውስጥ የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የመካንነት እና ስነተዋልዶ ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር መሰረት አንሳ ተናግረዋል። እንደ የህክምና ባለሙያዋ ንግግር የወርአበባ ኡደትን በተፈጥሮ የሚቆጣጠሩ የሰውነት ክፍሎች (ሆርሞኖች) አሉ። እነዚህ ሆርሞኖች የሴቷን የእንቁላል ማምረቻ እንዲሰራ እንዲሁም የማህፀን ግድግዳ እንዲፋፋ በማድረግ እርግዝና እንዲፈጠር ያደርጋሉ። ይህ ለእርግዝና የተዘጋጀው ክፍል እርግዝና ሳይፈጠር ሲቀር በወርአበባ መልክ ይወገዳል።
የወርአበባ ኡደት ለሁሉም ሴቶች ተመሳሳይ አለመሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ። ኡደቱ ለአንዳንድ ሴቶች በ21 ቀናት እንዲሁም ለአንዳንዶች ደግሞ በ35 ቀናት ውስጥ ሊካሄድ ይችላል። ይህም ማለት በየወሩ አጠረ ከተባለ በ21 ቀናት እንዲሁም ከረዘመ እስከ 35 ቀናት ባለው የጊዜ ልዩነት ውስጥ ኡደቱ ይካሄዳል። ነገር ግን በ1 ወር በ21 ቀናት ልዩነት ኡደቱ ተካሂዶ በቀጣዩ ደግሞ በ35 ቀን ይካሄዳል ማለት አይደለም። ለአንዲት ሴት በወር ከ21 እስከ 35 የቀናት ልዩነት ውስጥ በተለመደ መልኩ ነው (በጥቂት የቀናት ልዩነት) ኡደቱ መካሄድ ያለበት። በተመሳሳይ እንደየ ሰው የወርአበባ የሚፈስበት ቀን ከ2 እስከ 7 ቀናት ሊሆን ይችላል። ይህም በየወሩ ለአንዲት ሴት ተቀራራቢ በሆነ የቀን ብዛት መፍሰስ ይኖርበታል።
ጤናማ (የተስተካከለ) የወርአበባ ኡደት መለኪያ ዘዴዎች
የወርአበባ የሚመጣበት ቀን; ከ21 እስከ 35 ቀናት ውስጥ የሚፈስ እና በየወሩ ከጥቂት ቀናት (ከ5 እስከ 7 ቀናት) በላይ ልዩነት የሌለው መሆን አለበት።
የወርአበባው የሚፈስበት ቀን ብዛት; ከ3 እስከ 7 ቀናት መፍሰስ አለበት።
የሚፈሰው የወርአበባ መጠን; የሚፈሰው ደም መብዛት ወይም ማነስ የለበትም። የወርአበባ በአማካይ በቀን እስከ 80 ሚሊ ሊትር የሚሆን ይፈሳል። ከ80 ሚሊ ሊትር በላይ ወይም ከ30 ሚሊ ሊትር በታች ከሆነ ጤናማ አይደለም። ይህንንም አንዲት ሴት በቀን ውስጥ የምትጠቀመውን የወርአበባ ንፅህና መጠበቂያ ብዛት(ቁጥር) በማስላት መገመት ይቻላል። እንዲሁም በወርአበባ ምክንያት የደምማነስ ችግር ካጋጠመ የሚፈሰው ደም መብዛት መኖሩን መረዳት ይቻላል።
የረጋ ደም መኖር; ጤናማ የሆነ የወርአበባ የረጋ ወይም ረግቶ የተቆራረጠ ደም ሊኖረው አይችልም።
ህመም መኖር; በወርአበባ ወቅት መጠነኛ የምቾት ማጣት ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ከፍተኛ የሆነ እና ለረዥም ጊዜ የሚቆይ የህመም ስሜት ሲኖር የህክምና ባለሙያ ማማከር ያስፈልጋል።
በወርአበባ ወቅት ብዙ ደም በመፍሰስ የደም ማነስ ችግር ካጋጠማቸው ሴቶች መካከል ወ/ሮ ምናሉሽ እንዳለ ተጠቃሽ ናቸው። የወ/ሮ ምናሉሽ እንዳለ ባለቤት የሆኑት አቶ አለልኝ በሪሁን እንደተናገሩት ባለቤታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ከሌላው ወቅት በተለየ መልኩ መጠኑ የበዛ የወርአበባ ሲያጋጥማቸው ትኩረት አልሰጡትም ነበር። “በመጀመሪያው ወር ብዙ ደም ሲፈሳት አጋጣሚ ሊሆን ይችላል ብለን አለፍነው። ከዛ ግን መደጋገም ጀመረ” ብለዋል አቶ አለልኝ በሪሁን። አክለውም “ከተለመደው የወርአበባ ኡደት በተጨማሪ በመሀል መፍሰስ እና ማዞርም ጀመራት። ከዛም በምትሰራበት ቦታ መታመሟ ተነግሮኝ ስሄድ ይሄ ነገር ችላ የሚባል እንዳልሆነ አወኩ” በማለት ተናግረዋል። አቶ አለልኝ ባለቤታቸውን ወደ የህክምና ተቋም ወሰዷቸው። እናም የደም ማነስ ችግር መኖሩ ተነገራቸው። ነገር ግን ምርመራ የተደረገው በአነስተኛ የህክምና ተቋም በመሆኑ የችግሩን መንስኤ ማወቅ አልቻሉም ነበር።
ወ/ሮ ምናሉሽ የፅንስ እና የማህፀን ስፔሻሊስቶችን እንዲያማክሩ የአቶ አለልኝ እህቶች ምክር ሰጡ። በዚህም ምክር መሰረት ወ/ሮ ምናሉሽ ምርመራ እና ህክምና አገኙ። አቶ አለልኝ እንደተናገሩት በወርአበባ ወቅት ብዙ ደም መፍሰስ እና ከኡደቱ በተጨማሪ በመሀል የደም መፍሰስ መኖር ችላ የሚባል ጉዳይ አለመሆኑን ከህክምና ከባለሙያዎች ተረድተዋል። አቶ አለልኝ በሪሁን “ምናልባት ትንሽ ብንቆይ ካንሰር የመሆን እድል ነበረው። ፈጣሪ ሲረዳን ግን ባለቤቴ ታክማ ደህና መሆን ችላለች” በማለት ተናግረዋል።  
የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር መሰረት አንሳ እንደተናገሩት የወርአበባ ኡደት ለ1ወር (1ጊዜ) ወይም ለ2 ወራት ሊያጋጥም ይችላል። በተለይ የወርአበባ ኡደት በሚጀምርበት(የመጀመሪያ 2 ዓመታት) እና በሚያቆምበት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ላይ ያጋጥማል። ነገር ግን በመውለጃ እድሜ ውስጥ ላሉ እና የግብረስጋ ግንኙነት ለጀመሩ ሴቶች እርግዝና መጠርጠር እንደሚያስፈልግ ባለሙያዋ ተናግረዋል።
በዓለምአቀፍ ደረጃ ከ14 እስከ 20 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች የወርአበባ ኡደት መዛባት ያጋጥማቸዋል። ለወርአበባ ኡደት መዛባት ምክንያት የሚሆነው የሆርሞን መዛባት ነው። ለዚህም መዛባት በመውለጃ የእድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ሴቶች እንደምክንያትነት የሚጠቀሰው; እርግዝና፣ ከማህፀን ውጪ እርግዝና፣ ፅንስ ማቋረጥ እና የማህፀን ግድግዳ እርግዝና በሚይዝበት ወቅት የሚፈጠር የደም መፍሰስ ነው። እንዲሁም ለወርአበባ ኡደት መዛባት ምክንያት ከሚሆኑ ጉዳዮች መካከል የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት አንዱ ነው።  የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን በአግባቡ ካለመጠቀም የሚከሰት መሆኑን ዶ/ር መሰረት አንሳ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ጭንቀት፣ ቦታ መቀየር፣ የክብደት መቀነስ እና የክብደት መጨመር መዛባቱን ሊያስከትል ይችላል።
የወርአበባ ኡደት መዛባት በተለይም የወርአበባ መምጣት ከጀመረበት የመጀመሪያ እና ከሚያቆምበት ጊዜያት ውጪ ሲያጋጥም ወደ የህክምና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል። ስለሆነም የወርአበባ ኡደት መዛባት የተከሰተው በተለያዩ ችግሮች(በሽታዎች) ምክንያትነት አለመሆኑን ለማረጋገጥ ይረዳል። “የወርአበባ የሚፈስበት ቀን መርዘም፣ ኡደቱ የሚካሄድበት የቀን ልዩነት ረዥም መሆን እና የሚፈስበት መጠን መብዛት ወይም ማነስ በተደጋጋሚ ሲያጋጥም እርግዝና መሆን ወይም አለመሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል” በማለት የህክምና ባለሙያዋ ተናግረዋል። እንዲሁም የወርአበባ ኡደት ካቆመ(ከማረጥ እድሜ) ከብዙ ጊዜያት በኋላ የወርአበባ ከጀመረ መንስኤው ከባድ በሽታ ሊሆን ስለሚችል ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል። ከችግሮቹ መካከል ሆርሞን የሚያመነጭ የእንቁላል ማምረቻ እጢ፣ የማህፀን ጫፍ እና የማህፀን ግድግዳ ካንሰር ተጠቃሽ ነው። የወርአበባ ኡደት ካቆመ በኋላ(የማረጥ እድሜ ላይ) ማንኛውም የደም መፍሰስ ካለ ወድ የህክምና ተቋም መሄድ እንደሚያስፈልግ ነው ባለሙያዋ የተናገሩት።
ስለሆነም የወርአበባ ኡደት መዛባት ሲያጋጥም የእድሜ ሁኔታን እና ሌሎችም መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን ታሳቢ በማድረግ ወደ የህክምና ተቋም መሄድ እንደሚያስፈልግ የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር መሰረት አንሳ ተናግረዋል። በቀጣይ እትም እንመለስበታለን፡፡


Read 701 times