Saturday, 19 August 2023 20:19

የሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ምክር

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(1 Vote)

በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ አትሌቶች አንዱ ኃይሌ ገብረስላሴ ነው። በዓለም ሻምፒዮናው ተሳታፊ ለሆነው የኢትዮጵያ ቡድን ሲናገር “በአጠቃላይ ውድድር ዘመኑ ላይ ልጆቹን በተለይ በዳይመንድ ሊግና በሌሎች ውድድሮች እንዳየኋቸው  ውጤት እንደሚያመጡ ተስፋ የሚሰጥ ነገር አለ”  ያለ ሲሆን፤  በአጠቃላይ ግን ማንኛውም ዓለምአቀፍ ውድድር ፈታኝ መሆኑን በመግለፅ ቡድኑ በመለማመጃ ስፍራዎች እጥረትና የአየር ንብረት በመለዋወጥ ካለመሥራቱ ጋር በተያያዘ ልክ የተሰማውን ስጋት ከመጥቀስ አልተቆጠበም። እንደ ኃይሌ አስተያየት የአየር ንብረት በማንኛውም የስፖርት ውደድር ላይ ተፅእኖው ቀላል አይደለም። በእነሱ ዘመን በተለይ ከሞቃታማ አየር ጋር ለመለማመድ እስከ ሶደሬ በመሄድ ይሰሩ እንደነበር ያስታውሳል። “ትንሽ ሞቅ ሲል ለልጆቻችን አይሆንም። ሲድኒ ላይ በኦሎምፒክ ታሪክ ከፍተኛው ውጤት ሲመዘገብ፤ አምና ኦሬጎን ላይ ደግሞ በዓለም ሻምፒዮናው ለተገኘው የላቀ ውጤት የአየር ንብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር መመሳሰሉ እገዛ ነበረው።” ይላል
በተለያዩ የአትሌቲክስ ሚዲያዎች እና ባለድርሻ አካላት ሜዳልያዎችን የመተንበይና የመገመት ባህልንም በተመለከተ ኃይሌ አስተያየት  ከውድድር በፊት ይሄን ያህል ሜዳሊያ እጠብቃለሁ  ማለት ትክክል አይደለም ብሏል። አትሌቶች ላይ ተፅእኖ እንዳናሳድርባቸው በማለትም ያሳስባል። “ዘንድሮ በ10ሺ ሜትር በወንዶችም በሴቶችም ጥሩ ነገር እናያለን። ካሉት ተወዳዳሪዎች አንፃር በቡድኑ በኩል ያለው ጥንካሬ ይህን ያረጋግጣል።”
ለስፖርተኛ የተንዛዛ ምክር አያስፈልግም ያለው ኃይሌ ልምምድ በሚሰሩበት አካዳሚ በመገኘት ቡድኑን በማበረታታት ስለነበረው ቆይታም ለስፖርት አድማስ ገለፃ አድርጓል ። “አትሌቶች በቂ ልምምድ ሰርተዋል። ውደድሩ ሲቃረብ  ዘና ማለት አለባቸው። እረፍት በጣም ያስፈልጋል። ስፖርተኛ በቂ እንቅልፍ መተኛትና በአግባቡ ማረፍ አለበት። አንበሳ ከ24 ሰዓት ውስጥ 22 ሰዓታት ይተኛል። እረፍት ላይ ሆኖ ሚዳቋ እንኳን አጠገቡ ብትዘል አይነካትም። በ2 ሰዓት ውስጥ ግን አድኖ ይኖራል። የአንበሳ ባህርይ የስፖርተኛም ነው።”ብሎ ነው በስፖርት አካዳሚ አትሌቶችን የመከራቸው
“አትሌቶች በሻምፒዮናው በሚኖራቸው ተሳትፎ በውድድሮቻቸው ላይ ከፍተኛ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል። የኛ አትሌቶች ውድድር ሲሄዱ  ዙረት ያበዛሉ ገበያ ይወጣሉ ይህ ተገቢ አይደለም፡፡ ውድድር እያለ ቁጭ ብሎ በወሬ ሌቱን ማንጋትም አያስፈልግም፡፡ ይህንን ስመክራቸው አሰልጣኞችን ለማገዝ ያህል እንጅ በስራቸው ጣልቃ እየገባሁ አይደለም ፡፡ በሌላ   በኩል የቡድን ስራ ለሚባለው ዋናው ተግባር  ከአስልጣኞች ነው የሚመጣው፡፡ በስፖርተኞቹ መካከል የቡድን ስራን ለማምጣት፤ በአሰልጣኞች መካከል መልካም ግንኙነት መፈጠር አለበት። አሰልጣኞች ርበራሳቸው ከተፎካከሩየቡድን ስራ መጠበቅ ይከብዳል፡፡ ለአትሌቶቹ ማዕከል የሚሆኗቸው አሰልጣኞቹ ናቸው፡፡ ስለዚህም አሰልጣኞቹ የሚከባበሩና የሚተባበሩ ከሆነ ነው፡፡ የአስልጣኞቹ ትብብር የሰልጣኞቹን ትብብር ይፈጥራል፡፡ የአሰልጣኞች መከፋፈል ደግሞ ያለጥርጥር አትሌቶችን ሊከፋፍላቸው ይችላል፡፡ እንደምታውቀው ዛሬ የስልጠናው ሁደት የተለየ ነው፡፡ ሁሉም የራሱ ማናጀር የራሱ አሰልጣኝ ይዞ የሚሰራበት ግዜ ላይ ነን፡፡ ሁሉም አሰልጣኝ የራሱን አትሌት ከሌላው አግዝፎ ይመለከታል፡፡ ይህ እንግዲህ የቡድን ውጤትን ለማምጣት ፈተና ይሆናል። ምክንያቱም ሁሉም ግለኛ ስለሚሆን፡፡ በኛ ጊዜ  ዋና ማዕከል የምናደርገው እነዶክተር ወልደመስቀልን ነው። እነ ዶክተር ወልደመስቀል ደግሞ ልዩነት ቢኖራቸው አንድ ላይ ተከባብረው ሲሰሩ እኛም እንመለከታለን፡፡ ያንን ውድድር ሜዳው ላይ ተግባራዊ እናደርጋለን፡፡”
ለዘንድሮው ቡድን ሌላው ምክር የነገርኳቸው “ልጆቻችን እባካችሁ ውድድር ላይ ስትሄዱ  ሰብሰብ ብላችሁ ታዩ፡፡ በሌላው ተፎካካሪ ላይ በስነልቦና ተፅእኖ ለማሳደር ነው፡፡ ልምምድ ስተሰሩ አንድ ላይ ሁኑ እንድ ላይ በማመሟቅ ተፎካካሪዎችን ማስቀናት ያስፈልጋል፡፡  ይህን አይነቱን ተግባር በእኛ ዘመን ስናደርግ ሌላው ቡድን ትኩረቱ ተስቦ ምን እያደረጉ ይሆን በሚል ይረበሻል፡፡ ለግልም ለቡድንም ስራ ይህ አስፈላጊ ነው፡፡ በአሰልጣኞቹ መካከል ላለው ህብረት ትኩረት ከተሰጠ የአትሌቶችን ትብብር ማግኘት ይቻላል፡፡”
በዓለም ሻምፒዮናው ዝግጅት በሃይሌ ግራንድ ሆቴል ባለፈው ሳምንት ልዩ ሽኝት እና የባንዲራ ርክክብ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡ የአትሌቲክ ቡድኑ ማረፊያ ካምፑን በአቅራቢያው በሚገኘው አራራት ሆቴል በማድረጉ ሁሉም ሲመገቡ የቆዩት በዚህ ሆቴል ነው፡፡
የአትሌቲክ ቡድኑ  በኃይሌ ግራንድ ሆቴል በዝግጅታቸው ወቅት ሲመገቡ የነበረው በክፍያ ነው፡፡ ከምግቡ ባሻገር ማረፊያቸውን በዚያው አድርገው ቢሆን ደስተኞች ነበርን፡። ይላል ኃይሌ። ምናልባት እሱን ለፓሪስ  ኦሎምፒክ እናደርገው ይሆናል፡፡ የዓለም ሻምፒዮናው ቡድን በሃይሌ ግራንድ ሆቴል በነበረው ቆይታ በአመጋገባቸው ላይ የስነ ምግብ ባለሙያ በመመደብ ለስፖርተኞች የሚሆነው ሁሉ እንዲሰራ አደራ ሲል መቆየቱንም ተናግሯል፡፡

Read 565 times