Saturday, 19 August 2023 20:05

አሰብ - ቀይ ባህርና ወደባችን በዚያን ጊዜ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“--ቢሆንም የዮሃንስ ተፈራ አጻጻፍ መንፈሱ በሕይወት ታሪክ ላይ ስለተመሰረተ፣ እንደ ሕዋስ
ቆዳን ዘልቆ ይገባል። ሌላው ጠንካራ ጎን የደራሲው የጽሁፍ ጥንቅር በግብዝነት ስላልተመሰረተ፣
ከታችኛው ማህበረሰብ ተናንሶ መብላት መጠጣቱ የምርም ‘ጥበበኛና ከንቲባ ከሕዝቡ ጋር ነው
መኖር ያለበት።’ የሚለውን ተለምዷዊ ብሂል ማሟላቱ መልካም ነው።--”

ጥንካሬ፦
ጠንካራው ጎኑ ስራው ብቸኛና አንጡራ የሚባል ነው። ስለ አሰብ የዚህ አይነት መጽሐፍ ተጽፎ አያውቅም። በልብወለድ ተደርጎ “ሄላ” የሚል መጽሐፍ አስታውሳለሁ። በኢ-ልብወለድ ግን ይህ መጽሐፍ ብቸኛው ነው። የዶ/ር  ያእቆብ ኃ/ ማርያም  “አሰብ የማናት” የሚለውም ቢሆን፣ የፖለቲካ ትንታኔ እንጂ እንዲህ ሰነድና ዋቢ መጻህፍት አልቦ ከሆነ፣ የህይወት ነጸብራቅ ላይ የተመሰረተ የእውቀት ብልጭታ አይደለም። የጽሁፍ ስራውን አድካሚ፥ መጽሐፉንም ወሳኝ የሚያደርገውም ይህ ነው።
የአሰብ ነዋሪዎችን ሕይወትና ውጣ ውረድ፥ የገቢ ምንጫቸውንና ባህሪያቸውን ለመሳል የተከፈለው ዋጋ፣ ከ400 ገጾች በላይ ያሉትን ኪታብ አል-አሰብ መስጠቱ ጥኡም ነው። የደራሲው ግልጽነትና አይኑን በRomanticism መነጽር ጋርዶ፣ ስለሌላው ጾታዊ ንሸጣው አልደበቀም። አንገቱ እስኪበጠስ እንደኔም ባያይ በአፋር ሴቶች መልክ መማረኩን አምኗል። Realism technic ተጠቅሞ መጻፉ ያስመሰግነዋል። ለምን? አኗኗራችን ንፍጥ ይበዛዋል።
ከአወቃቀር አኳያ ዘርፈ ብዙ (multi layered) ነው። ባህላዊ ዘውግም ማህበረሰባዊ ጠባይም አስተያይቶ ነው የጻፈው። ስለ ወደብ ጥቅሞች ይህ ትውልድ እንዲያውቅ የለፋበት ሂደት መልካም ነው። በርግጥ እዚህ ጋ ባለ ዳሰሳ፣ የ“አረናው” አስራት አብርሃም ባሳተመው፣ “ከሀገር በስተጀርባ” በሚለው፣ ህወሓትን በሚወግርበት መጽሐፉ፣ በአጭርና በእጭቅ ትንታኔ ገልጿል። ቢሆንም የዮሐሃንስ ተፈራ አጻጻፍ መንፈሱ በሕይወት ታሪክ ላይ ስለተመሰረተ፣ እንደ ሕዋስ ቆዳን ዘልቆ ይገባል። ሌላው ጠንካራ ጎን የደራሲው የጽሁፍ ጥንቅር በግብዝነት ስላልተመሰረተ፣ ከታችኛው ማህበረሰብ ተናንሶ መብላት መጠጣቱ የምርም ‘ጥበበኛና ከንቲባ ከሕዝቡ ጋር ነው መኖር ያለበት።’ የሚለውን ተለምዷዊ ብሂል ማሟላቱ መልካም ነው። ጠንካራ ግለሰቦች እንደ ኮማንደር ዘለቀ ቦጋለ፣ ጥናታዊ ፊልም ቢሰራባቸውና፣ በስማቸው መንገድ ብሎም የግንባታና የሀገርን መውደጃ ዝግጅቶች ላይ በስማቸው Conference Paper ቢቀርብ ጥሩ ነበር-ይህም የመጽሐፉ ትሩፋት ነው።
ድክመት፦
አንዳንድ ቦታ ላይ የሀሳብ ወጥነት ጉድለት ይታያል። ‘ስለምን የሀሳብ ወጥነት ጎደለው?’ ሊባል ይችላል። ይህም የሚከሰተው የጽሁፍ አባዜው እንደ ዛር ሲሰፍር ከሚመጣው የሃሳብ ግትልትል ናዳ ለማምለጥና ድምጹንና ምስሉን ከመፍራት ነው፡፡ ጽሁፉ ከውስጥ በግፊት መውጣት ሲጀምር፣ ምስሉና ድምጹ ከውጪ ኩልል እያለ ይመጣል፣ ይሄኔ ሰዎች ከውጪ የሚሰሙትን ድምጽ መበርገግ ይጀምራሉ። በዚህም የተነሳ በሰላሙ ጊዜ ሲታሰቡ የነበሩ ሀሳቦችን ማስገባት ይመጣል-(አላበድኩም ለማለት)። እንግዲህ ዛሩ ደግሞ ነጭናጫ ነገር ስለሆነ ትእግስት የለውም፤ ተቀይሞ እብስ ሲል ጸሃፊው በአእምሮው Mechanical ትግል ይጀምራል። ይሄኔ ቅልቅሉ ብቅ ይላል። የእርግጠኝነት ስሜት መጉደል፥ የእርማት ችግርና የዋቢ መጻሕፍት አሰዳደር መጽሐፉ ለአራተኛ ዙር ከታተመ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው።
መጽሐፉ ባያልቅም እኛ ስንጨርስ፦
እንግዲህ- የድንቁርና ማሰሪያው ንባብ ነውና፤ መጽሐፉ ይነበብ ዘንድ የጥበብና የታሪክ ስንክሳር ያስገድዳል።

Read 648 times