Monday, 14 August 2023 20:33

ስካር ይለቃል፤ ድድብና አይለቅም!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)


“…ከመሰላሉ ማውረድ አለባቸው የሚላቸውን ሰዎች ዝንተ አለማቸውን ስማቸውን እንደ ተራራ ሲቆለል የኖረ ነው” የሚል የፅሁፍ መግቢያ ያደረገውን… የፅሁፉም ርእስ … “ደራሲ ብሎ ጠቢብ አይታየኝም” … የሚል ነበር፡፡ በእኔ በኩል ፀሃፊ ከመግቢያውም መስተካከል አለበት እላለሁ፡፡ ለዚህም የማነሳው ሃሳብ እነዚህ ሰዎች… ወደ መሰላሉ እንዴት ወጡ? ማን አወጣቸው? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። በመጀጨመሪያ ደረጃ ሰዎቹን ወደ መሰላሉ ያወጣቸው ስራቸው በማስከተለም ህብረተሰቡ ነው፡፡ ህብረተሰቡ ወደ ላይ ለመውጣቱም ሆነ ወደ ታች ለመውረድ ከፍተኛውን አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡ ስለሆነም ማህበረሰቡ ወደ መሰላሉ ማውጣት ብቻ ሳይሆን እንድትመላለስ የሚያደርግህ ዝም ብሎ አይደለም፡፡ ይህም ሲባል ጠቃሚ የሆነ ምርምር በህክምና፣ በእርሻ፣ በሳይንስ፣ በፍልስፍና እንዲሁም በስነ ፅሁፍ በድርሰት… በግጥም… በቅኔ… ህይወትን መምራት የምትችልበትን ቀመር  በመቀመር ህብረተሰቡ… አንድ … ሁለት… እርምጃ ቀድመህ ስትገኝ ህብረተሰቡ እራሱ እዛ መሰላል ላይ ያስቀምጥሀል፡፡ ምክንያቱም ሁሌም ማህበረሰቡ ለህይወቱ ተሞክሮውን፣ መፍትሄ፣ ብሎም ብርሃንን አግኝቶበታል፡፡
ኤፍራጠስ፤ አንተ እንዳልከው ላንተ ማዳም ሲጁ ወከር ትበልጥብሃለች …. ይሁን ስራዋ ለውጫዊ ውበት ይጠቅማልና… ለውስጣዊ ውበትህስ ማንን? ወይስ ለውስጣዊ ውበት አትጨነቅም? አለኝ ካልክስ ከየት አመጣኸው?... እንደው ለማለት ያህል ማህበረሰቡም የራሱ የሆነ ውስጣዊ ውበት አለው፡፡ በእኔ እምነት ስነፅሁፍ ድርሰት፣ ግጥም፣ ቅኔ ብሎም ፍልስፍና አለ ሊባል የማይችል ውስጣዊ ውበት ወይም ንቃተ ህሊና ፍላጎትን እና ጉጉትን እያንዳንዱ ግለሰብ ውስጥ ይፈጥራሉ፡፡ ይህ ደግሞ ምን አይነት እንደሆነ ከጊዜ በፊት ለማስረዳት ጊዜ መፍጀት ይመስለኛል፡፡
እዚህ ላይ እኔ ከነዚህ ሰዎች አልተጠቀምኩም ማለት ሌላ ነገር ነው፡፡ አይጠቅሙም ማለት ግን ትንሽ አስገዳጅነት ባህሪ አለው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን የተጠቀሙትን መንካት፣ የናንተን አፍሩስና በእኔ አይነት ገንቡ እንደ ማለት ነው። … እኔ በበኩሌ የዚህ አይነቱን አቀራረብ አልጣመኝም፡፡ እስቲ ሳነብ ያገኘሁትን ላካፍልህ።
“የሰው ልጅ ጌጡ ጥበብ ነው እና ለጠቢባን እውቀትን ያበዙ ዘንድ መናገር ተገቢ ነው፡፡”
ጠቢብ እንዲህ አለ፡- “በጭለማ ማየት እችላለሁ…” የጠቢቡን አባባል ያልተረዳ ሰነፍ ደግሞ ጠየቀ፡-
“በጨለማ ማየት ከቻልክ ታዲያ ለምን መብራት ይዘህ ትሄዳለህ?” ጠቢቡ ከሰነፍ የሚጠብቀው ጥያቄ ነውና ሳይደነቅ መለሰለት፡- “እንደ አንተ አይነት በጨለማ ማየት የማይችል መጥቶ እንዳይገጨኝ ነው” አለው፡፡ ጠቢብ መሆን ባይቻል፣ የጠቢብን ብርሃን ማየት ይቻላል፡፡ ስለሆነም ብርሃኑን በመጠቀም ለህይወት የሚጠቅመውን (የሚበጀውን) ማየት የተመረጠ ይሆናል ብዬ ነው፡፡
እብደት ማለት ምን ማለት ነው? ለእኔ እብደት ማለት … አንድ ሰው ካለው ማህበረሰብ ወጣ ያለ አስተሳሰብ ሲኖረው ነው… ሰዎች ያ ሃሳብ ከራሳቸው በላይ በሆነ ጊዜ አበድን ይላሉ… ግን ያበደው ማን ይሆን? ኤፍራጠስ፤ በፅሁፍህ ላይ “ግማሹ አብዶ ነው የሚሞተው” ብለሀል። ለዚያም የጠቀስከው አማኑኤል ካንትን ነው። ምን አልባት ‘አማኑኤል’ እንደ ‘ባህሉ’ ሆኖ ሊሆን ይችላል፡፡ ባህሉን የቱንም ያህል በጥበብ ቢበስል፣ በዚሁ ምክንያት የሚደርስበትን አደጋ ፍራቻ ጥበብን በእብደት መጋረጃ ሸፍኖት ነበር። ለዚሁም ምሳሌ፡-
አንድ ቀን ባህልን ከንጉስ መቀመጫ ተቀምጦ ተገኘ፡፡ በዚህ ምክንያት ወታደሮቹም ቆዳው እስኪላጥ ሲገርፉት… ጩኸቱን የሰማው ንጉስ፣ መጣና ወታደሮቹን “እናንተ እብዶች፣ ባህሉን እብድ መሆኑን አታውቁም” አላቸው፡፡
ባህልሉን “ንጉስ ሆይ ወታደሮችህን ተዋቸው፤ እኔን ያስለቀሰኝ ሌላ ነው” አለ፡፡ በዚህ ንግግር የተደነቀው ንጉስ ምን ለማለት እንደፈለገ ጠየቀው… ባህሉንም አለው፡-     “እኔ አንድ ቀን ለተቀመጥኩበት ይሄን ያህል ከሆንኩኝ፣ አንተማ ለሀያ አመታት የተቀመጥከው… ያንተ ስቃይና መከራ ትዝ ብሎኝ ነው” አለው፡፡ ንጉስ ለአመታት ያላየውን እውነት እብዱ ባህሉን አሳየው፡፡ ንጉስም አለ “ከእብደት፤ ሚስጥር የእውነት ምንጭ ይገኛል፡፡”
ሌላው የጠቢባኑን የግል ሰብእና ከሚሰጡን እውቀት፣ ጥበብ፣ ብርሃን ጋር በመደባለቅ ማየት አግባብ አይመስለኝም፡፡ ለዚሁም አንድ ሻማ ሲበራ መጠቀም ያለብህ፣ ሻማው የሚሰጠውን ብርሃን በመንተራስ ሌላ ጥበብ… ምርምር… ሌላ እውቀትን ለህብረተሰቡ ሊሰጡና መሰላል ሊያወጡ የሚችሉ የህይወት ቀመሮችን በመቀመር ነው፡፡ አለዚያ ግን ይሄኛው ጥቁር ሻማ… ያኛው ነጭ… ቀይ… እያልን ጊዜያችንን ስናባክን ብርሃኑን በአግባቡ ሳንጠቀም ያልፈናል። ስለሆነም ከውስጣቸው የሚፈሰውን ከኔና ካንተ ውስጥ የሌለውን እውቀት፣ ብርሃን፣ … ጥበብ … መቅሰም ይጠቅማል ባይ ነኝ። ስብሃት ስካር ሲነጋ ይለቃችኋል፣ የኔና ያንተ ደደብነት ግን ዝንታለም አይለቀንም፡፡
ስለዚህ እኔ በበኩሌ ከዚህ አይነቱ ሀጥያት ይሰውረኝ ብያለሁ፡፡ ለምን ቢሉ አለማወቅን የመሰለ ሀጥያት የለምና… ለእኔ፡፡
ሌላው አንድ የጠየከው ጥያቄ ነበር። ዳኛቸው ወርቁ፣ በአሉ ግርማ፣ አቤ ጉበኛ… ብለህ ጠርተህ “ለዚህ ህዝብ አንድ ቀን እንጀራ አብስለውለታል?” ብለህ ጠይቀህ ነበር፡፡ አንዱና ዋናው ችግር ይህ ነው፡፡ ለምንድን ነው ህይወታችን በሌላ ሰው ላይ የሚመሰረተው ወይም እንጀራችንን ሰው እንዲጋግርልን የምንፈልገው? ማን ነው የራሱን ትቶ የሰው እንጀራ የሚጋግረው? የቱ ነው የጠቀስከው ሰው፣ ለሰው ብሎ የሚሰራ? ዶክተር? ነርስ? … መሃንዲስ ነው ድልድይ ለሰው የሚሰራ? እኔ የሚመስለኝ… ምን አልባት ይሻገርበት ስለፈለገ… አለዚያ ደግሞ ወደ ቀጣዩ ሌላ እንጀራ እንደሚያሻግረው አስቦ ለራሱ ሲል ነው የሚሰራው፡፡ እዚህ ላይ አንድ የሰማሁት የፈረንሳዮች አባባል ልጥቀስ “ሁሉም ለራሱ፣ እግዜር ለሁሉም”
ስለዚህ ሁልጊዜ ምን ምን ሰራሁ? እኔ ማን ነኝ? ለሀገሬስ በምን መልኩ አስተዋፅኦ አደረኩ ብሎ እራስን መጠየቅ በራሱ እውቀት (ብርሃን) የሚያመጣውን የመጀመሪያ ደረጃ መድስ ማለት ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ የምትመከረው ወይም የምትለመነው የማይጠቅምህን ሁልጊዜ መተው ነው፡፡ ለምሳሌ ሬዲዮንን ስለጋሽ ስብሃት ማውራት ሲጀምር መዝጋት ወይም መስመርን መለወጥ እንዲሁም በETV  ሲመጡህ አሁን አሁን በጣም ተመስገን ነው ወዲያው … TV Africa … መለወጥ የተሻለ ዘዴ በመሆኑም፣ ይህን በመጠቀም የሚያደናቁርህን መሸወድ ትችላለህ፡፡ ስለዚህ ላንተ ያልተፃፈውን አለማንበብ ለምን ቢባል አይጠቅምህም እና… ጊዜና ወቅቱ ሲደርስ ላንተ የሚሆን… ሲፃፍ ማንበብን… ትመከራለህ፡፡ ለዛሬ መፅሀፍ ሳነብ ባገኘሁት ጥቅስ ልሰናበትህ።
“If your mind is not open, keep your mouth shut too” “Let’s hear what you have to say"
“እኔም ብርሃን ከጨለማ እንደሚበልት እንዲሁም ጥበብ ከስንፍና እንደሚበልጥ አየሁ”
መክ፡13
“የሰው ልጆች ደስታ እና ጥበብ የሚከማቹት በመፅሃፍ ውስጥ ነው…
… ምንጊዜም እያንፀባረቁ ፍሬዎቻቸውም በማሰራጨት ለዘመናት አያሌ ሃሰሳቦችን እና ተግባሮችን ያመነጫሉ፡፡
(ምንጭ፡- አድማስ ሃምሌ 5 ቀን 1995)

Read 1475 times