Saturday, 12 August 2023 20:56

የዓለም ሻምፒዮናውና ሦስቱ አሰልጣኞች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና  ከሳምንት በኋላ ቡዳፔስት ላይ እንደሚካሄድ ይታወቃ230ል። በሐንጋሪ የዓለም ሻምፒዮናው አዘጋጅ ኮሚቴ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ከአትሌቶች ባሻገር ለአሰልጣኞችም  የሜዳልያ ሽልማቶች ተዘጋጅተዋል። “በምንሸልማቸው ሜዳሊያዎች ስፖርትን፣ ጀግንነትንና ብሄራዊ ማንነትን ማስተሳሰር ግድ ይለናል። ስለዚህም በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ  አሰልጣኞች በሽልማት መድረክ ላይ ሜዳሊያዎችን ይቀበላሉ ብለዋል።" በቡዳፔስት የዓለም ሻምፒዮናው አዘጋጅ ኮሚቴ ዋና ስራ አስፈፃሚ ባላዝ ኔሜት።
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር በሳምንቱ አጋማሽ ላይ የተሳታፊ አትሌቶችን ዝርዝር ያስታወቀ ሲሆን፤ በሻምፒዮናው ከ202 አገራት የተውጣጡ ከ2100 በላይ አትሌቶች መመዝገባቸውን አረጋግጧል። ለዓለም ሻምፒዮናው ከ2 ወራት በላይ ዝግጅት ያደረገው የኢትዮጵያ ቡድን በሁለቱም ፆታዎች ቋሚ ተሰላፊዎችና ተጠባባቂዎችን ጨምሮ 48 አትሌቶች ማስመዝገቡን ለማወቅ ተችሏል። የአትሌቲክስ ቡድኑ ዝግጅት ፌዴረሽኑ ከክለቦች፤ ከአሰልጣኞች፤ ከማናጀሮችና ከአትሌቶች ተቀራርቦ በመሥራቱ በቡድን መንፈሱ የተጠናከረ ሆኗል። የቡድኑ ዝግጅት በስፖርት መሰረተ ልማቶች አለመሟላት አሳሳቢ ፈተና እንደገጠመው ግን መታዘብ ይችላል። ስፖርት አድማስ ከቡድኑ አሰልጣኞች ጋር ያደረጋቸው ቃለምልልሶች ከቡዳፔስት የዓለም ሻምፒዮና በኋላ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በቀጣይ በ2024 ለሚካሄደው የፓሪስ ኦሎምፒክ ብዙ መስራት ይጠበቃል፡፡



       የአትሌቶች ማናጀርና አሰልጣኝ ተሰማ አብሽሮ  ከሩጫ ዘመኑ በኋላ ወደ አሰልጣኝነት ሙያው በመግባት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስኬታማ ከሆኑ ባለሙያዎች አንዱ ነው። በአሰልጣኝነት ከ9 ዓመታት በላይ የሰራ ሲሆን ከግሎባል ስፖርት ኮምኒኬሽንና ከNN የሯጮች ቡድን ጋር በዓለም ሻምፒዮናው ተሳታፊ ይሆናል። ሁለቱ የአትሌቲክስ ተቋማት በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ 70 አትሌቶች (45 ሴቶች ናቸው) ጋር በመስራት ከፍተኛ እውቅናና ስኬት እያገኙ ናቸው። አሰልጣኝ ተሰማ ለስፖርት አድማስ እንደገለፀው ቡዳፔስት ላይ በግሎባል አትሌቲክስ ስር ከ45 በላይ አትሌቶች ተሳታፊ ይሆናሉ።
"ካለፉት ሻምፒዮናዎች በተለየ መልኩ ማናጀሮቹና አሰልጣኞቹ በአንድ ላይ መስራታቸው የቡድኑን የአንድነት መንፈስ አጠናክሮታል"
በኢትዮጵያ የማራቶን ቡድን ዝግጅት ዙርያ አሰልጣኞችና ማናጀሮች በልዩ ሁኔታ ተግባብተው ሲሰሩ ቆይተዋል።  ለሻምፒዮናው የተደረገውን አጠቃላይ ዝግጅት አሰልጣኝ ተሰማ አብሽሮ ሲገመግም “የማራቶን ቡድኑን አጠቃላይ ዝግጅት በሴትም በወንድም የጀመርነው በ30 ኪ.ሜ የረጅም ርቀት ሩጫ ነው። አትሌቶቹ ከተለያዩ አሰልጣኞችና ማናጀሮች የመጡ ቢሆንም ለአገር አብረው መስራት እንዳለባቸው በመወሰን ነው ስራ የጀመርነው። የማራቶን አትሌቶቹ ከአራት የተለያዩ ማናጀሮች የተገኙ ናቸው። ከግሎባል አትሌቲክስ፣ ከጃኒ፣ ከገመዶ ከሁሴን፤ ከሃጂና ከጌታመሳይ የመጡ ቢሆንም አንድ ላይ ተቀላቅለው ሲሰሩ ቆይተዋል። የልምምዱን ሂደት ዲዛይን ያደረግነው ከአራት በላይ አሰልጣኞች ቁጭ ብለን ባደረግነው ምክክር ነው። የማራቶን ቡድኑ አብሮ በመስራቱ በአጠቃላይ ዝግጅቱ ጥሩ ነገር እያየን ነው። በሻምፒዮኖቹ ታምራት ቶላና በጎይተቶም ገብረስላሴ መሪነት ጥሩ ውጤት ለማምጣት እየሰራ እንገኛለን። ካለፉት ሻምፒዮናዎች በተለየ መልኩ ማናጀሮቹና አሰልጣኞቹ በአንድ ላይ መስራታቸው የቡድኑን የአንድነት መንፈስ አጠናክሮታል” ብሏል አሰልጣኝ ተሰማ እንደገለፀው ለማራቶን ቡድኑ የአንድነት መንፈስ መጠናከር የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት ጥያቄ ማቅረባቸው አስተዋፅኦ አድርጓል። ፌዴሬሽኑ ለቡድኑ ዝግጅት ሃሳብ ካቀረበ በኋላ አትሌቶች፤ ማናጀሮችና አሰልጣኞች  ፈቃደኞች ነበሩ። ባለፈው የዓለም ሻምፒዮና በማራቶን የተመዘገበው የላቀ ውጤትም ለትብብሩ መነሻቸው ሆኗል። “ማራቶን የቡድኑ ስራ ነው። አብረህ ልምምድ ስትሰራ  ረጅም ርቀት አብረህ ነው የምትጓዘው። ዞሮ ዞሮ አንድ ሰው ነው የሚያሸንፈው ግን በውድድሩ ውሃ መቀባበል አለ፣ አይዞሽ፣ አይዞህ መባባል አለ። ስለዚህ አትሌቶችን በዚህ አሰራር ላይ እንድንዘጋጅ ስንጠይቅ በጥሩ መንፈስ ተቀበሉት። ሁሉም አትሌቶች የአምናውን ውጤት ዘንድሮም ለማስመዝገብ ፍላጎት አላቸው።” ብሏል አሰልጣኙ ።
“ተሰላፊ አትሌቶች በይፋ መግለፃቸው በቡድኑ ላይ የተሰጠውን መተማመን ያመለክታል።”
 የኬንያ የማራቶን ቡድን ቋሚ ተሰላፊዎች ከ2 ወራት በፊት ነው የታወቁት። በኢትዮጵያ በኩል ግን በቋሚ ተሰላፊዎችን  ለመለየት አልተቻለም። ይህ ሁኔታ በቡድኑ አቋም ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ የለም ወይ? ለሚለው ጥያቄ አሰልጣኝ ተሰማ አብሽሮ ምላሽ ሲሰጥ “የማራቶን ቡድኑን ለመወሰን የአትሌቶች ወቅታዊ ብቃት ወሳኝ ይሆናል። እንደ አሰልጣኝ ብጠየቅ፤ በሻምፒዮናው እነ እገሌ  ቢመረጡ ጥሩ ብቃት ያሳያሉ ብዬ ለመግለፅ አልቸገርም። አጠቃላይ ቡድኑን መጨረሻ ላይ የሚወስነው የቴክኒክ ኮሚቴና የፌዴሬሽን አመራር ነው።ሻምፒዮናው አንድ ሳምንት እስኪቀረው እነ እገሌ ይሰለፋሉ የሚል ነገር በኦፊሴላዊ መንገድ አልተገለጸም። በእኔ አስተያየት ይህ አትሌቶቹ ላይ የተወሰነ ጫና ሊፈጥር ይችላል። እኔ እመረጣለሁ  እንትና ይመረጣል የሚለው ነገር ልምምዱን  ወደ ፉክክር ይከተዋል። በጠቃላይ ቡድኑ በግልጽ አለመታወቁ የሚፈጥረው ተፅእኖ ሊኖር ይችላል። ከቤጂንግ ኦሎምፒክ ጀምሮ ያለኝ ልምድ የኢትዮጵያ ቡድን ውድድሩ አንድና ሁለት ቀን ሲቀረው የሚገለፅበት አሰራር ልክ አይመስለኝም። በሻምፒዮናነታቸው በቀጥታ የሚሳተፉትን  አትሌቶችን ጨምሮ በሁለቱም ፆታዎች የሚሰለፉትን 8 ተሰላፊ አትሌቶች በይፋ መግለፃቸው በቡድኑ ላይ የተሰጠውን መተማመን ያመለክታል። በአትሌቶች የሚፈጥረውንም ጭንቀት ይቀንሰዋል።” በማለት ተናግሯል።
 “ለመሸለምም ሆነ ለመሸለም በመጀመሪያ ሜዳው ሊኖረን ይገባል፡፡”
በዓለም ሻምፒዮናው ለኢትዮጵያ ቡድን ከተጋረጡ ስጋቶች አንዱ የቡዳፔስት ሞቃታማ አየር  ንብረት ነው። አሰልጣኝ ተሰማ በዚህ ሁኔታ ላይ ሲናገር “የዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች ብዙውን ጊዜ በነሐሴ ወር ላይ ነው የሚደረጉት። እኛ አገር የክረምት ወቅት ነው። በሌላው ዓለም በተለይ በአውሮፓ ደግሞ በጋ  ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን የአየር ሁኔታ እንደተገመተው አይሆንም። በማራቶን በሁለቱም  ፆታዎች ውድድሮች በማለዳ መደረጋቸው ይታወቃል። በዚያ ተንተርሰን ዝግጅታችን ላይ በተቻለን መልኩ የአየር ሁኔታወን የምንቋቋምበት ልምምድ እየሰራን ቆይተናል። አሁን ባለኝ መረጃ ቡዳፔስት ላይ የሙቀት ሁኔታ ከ29- 300C  ይደርሳል እየተባለ ነው። አትሌቶችን ከሰዓት ላይ እያሰራን ቆይተናል።  አምናም ኦሬጎን ላይ ሙቀቱ በጣም ያስቸግራል ሲባል ነበር። አጋጣሚ ሆኖ ግን ተፈጥሮን ማንም መቆጣጠር ስለማይችል ጥሩ አየር ሆኖ አስደናቂ ውጤት ተመዝግቧል። በአጠቃላይ የአየሩ ሁኔታ ለሁሉም አገሮች ነው፤ ለኢትዮጵያ ብቻ አይደለም። በውድድር ቦታ ላይ የሚገጥመንን ችግር በዝግጅት ማስተካከል አለብን በሚል ሰርተናል።” ብሏል።
በዘንድሮው ዓለም ሻምፒዮና ለአትሌቶች የሚሰጠው የሜዳልያ ሽልማት ለውጤታማ አሰልጣኞቻቸውም እንደሚበረከት እየተገለጸ ሲሆን የዓለም አትሌቲክስና ኦሎምፒክ የሚያስከብር ትልቁ ታሪካዊ ውሳኔ እንደሆነ አሰልጣኝ ተሰማ አብሽሮ ገልጿል። በኢትዮጵያ አትሌቲክስ  ታሪክ የማይረሳው ወርቃማ ታሪክ ያስመዘገቡ እንደሆነ ወልደመስቀል ኮስትሬ አይነት አሰልጣኖች ለታላላቆቹ አትሌቶች ትልቁን ስራ ከጀርባ ሆነው በመስራት የአንበሳውን ድርሻ እንደወሰዱ ያስታወሰው አሰልጣኙ ወደፊትም ውጤታማ አሰልጣኞችን በዚህ አይነት ማበረታቻ መፍጠር እንደሚቻል እምነት አለኝ ሲል አስረድቷል።በአለም አትሌቲክስ ላይ ስታየው አሰልጣኞች ይለፋሉ፣ ይደክማሉ ግን ዋጋውን የሚወስደው አትሌቱ ነው፡፡ ለአሰ“ልጣኞቹ የተሰጠ እውቅና ቢሰጣቸውም በቂ ግን አይደለም፡፡ የአለም አትሌቲክስ አሰልጣኞች ወደ ሜዳልያ ሽልማት ለማምጣት መስራቱ ትልቅ ምስጋና የሚቸረው ነው፡፡ አሰልጣኞች የተሻለ ስራ ለመስራት የሚነሳሱበት ይሆ” ናል፡፡
"ኢትዮጵያ በአለም አደባባይ ከፍ ብላ የምትታይበት ስፖርት ቀይ መብራት አብርቷል፡
፡ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ መንግስትም፣ ህዝብም፣ ባለሃብትም ማተኮር ያለበት በአትሌቲክስ ማዘውተሪያ ስፍራዎች ልማት ላይ ነው፡፡"
ከሽልማት ባሻገር ግን በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዮ ትኩረት መሠጠት የሚያስፈልገው በስፖርት መሠረተልማት ዙርያ መሆኑን አሰልጣኝ ተሰማ በጥብቅ ነው የሚያሳስበው።  “ኢትዮጵያ በአለም አደባባይ ከፍ ብላ የምትታይበት ስፖርት ቀይ መብራት አብርቷል፡፡”ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ መንግስትም፣ ህዝብም፣ ባለሃብትም ማተኮር ያለበት በአትሌቲክስ ማዘውተሪያ ስፍራዎች ልማት ላይ ነው፡፡”  በሚልም ተናግሯል።የማዘውተሪያ ስፍራዎች በጣም ያስፈልጉናል። አለበለዚያ የኢትዮጵያ አትሌቲክስን አደጋ ላይ ነው ያለው። በቂ “ማዘውተሪያ የለም፤ ትራክ የለም። የማራቶን ቡድን የሚሰራበት 20 ኪ.ሜ - 30 ኪ.ሜ የተዘጋጀ ቦታ የለንም።  እስዛሬ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሚስተዳድረው አንድ ማዘውተሪያ ቦታ አለመኖሩ ያሳዝናል። ይህ መሰረተ ልማት ባልተሟላበት ሁኔታ ላይ ለአትሌቶችም ሆነ ለአሰልጣኞች የሚሰጠው የገንዘብ ሽልማትና ስጦታ ልጓጓለት አልችልም። ባለመሰጠቱም አልደነቅም። ምክንያቱም በመጀመሪያ የስፖርት መሰረተ ልማቱ አስፈላጊ ነው። ለመሸለምም ሆነ ለመሸለም በመጀመሪያ ሜዳው ሊኖረን ይገባል፡፡ አትሌቲክሱ ላይ ህፃናቶችና ታዳጊዎች የሚለማመዱበት የሚሰሩበት የስፖርት መሰረት ልማት ላይ ባለሃብቱም መንግስትም ተረባርቦ መስራት አለበት፡፡  ይህ ችግር ካልተቀረፈ በምንሳተፋቸው ውድድሮቹ ሚኒማ የማናሟላባቸው ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። የሜዳ እጥረት መኖሩ በአጭርና በመካከለኛ ርቀት አትሌቶች እንዳይኖሩ አድርጓል፡፡ በተለያዩ የአለም ክፍሎች ላይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ  የሚውለበለበው በአትሌቲክስ ነው፡፡ ስለዚህ ቅድሚያ ትኩረት መስጠት የሚገባን ለስፖርት መሰረተ  ልማት ነው፡፡  


         የኢትዮ ኤሌክትሪክ አትሌቲክስ 10 አትሌቶችና ዋና አሠልጣኝ ቶሌራ ዲንቃ
የኢትዮ ኤሌክትሪክ የስፖርት ክለብ በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለሚሳተፉ 10  አትሌቶችና 1 አሰልጣኝ  አሸኛኘት አድርጓል። የስፖርት ክለቡ ለዓለም ሻምፒዮናው ካስመረጣቸው አትሌቶች መካከል በማራቶን የዓለም ሻምፒዮንና የሻምፒዮናው ሪከርድ የያዘችው ጎይተቶም ገብረስላሴና በ10 ኪሜ የጎዳና ሩጫ የዓለም ሪከርድ ባለቤት የሆነችው ያለምዘርፍ የኋላው ይገኙበታል። ሌሎቹ አትሌቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች ከፍተኛ ልምድ ያላቸው በሪሁ አረጋዊ፣ ሀጎስ ገብረሂወት፣ገብረፃዲቅ አብራሃ፣ ታደሰ ወርቁ፣ ፀጋዬ ጌታቸው፣ ያለምዘርፍ ሀብታም  አለሙ፣ ሂሩት መሸሻና  ሚዛን አለም ሲሆኑ፤ በአሰልጣኝነት ደግሞ ቶሌራ ዲንቃ ናቸው።የኢትዮ ኤሌክትሪክ የስፖርት ክለብ ባለፈው ሻምፒዮና በጎይተቶም አማካኝነት በማራቶን የወርቅ ሜዳልያ ማስመዝገቡ የሚታወስ ነው። የክለቡ የስራ አመራር ቦርድ ቡዳፔስት ላይ  አትሌቶቹ ከወርቅም ባሻገር ተጨማሪ የብርና ነሐስ ሜዳሊያዎችን ለኢትዮጵያ እንደሚያመጡ ተስፋ አድርጓል።  የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ ውጤታማ አትሌቶችን በማሰባሰብ በሰጠው ትኩረትና ለኢትዮጵያ ቡድን ባደረገው ከፍተኛ አስተዋጽኦ በታዋቂ አሰልጣኞችና የፌዴሬሽን አመራሮች ሊመሠገን በቅቷል።
7 የዓለም ሻምፒዮናዎች፤ 3 ኦሎምፒኮች
አሰልጣኝ ቶሌራ ዲንቃ በአሰልጣኝነት ሙያ ውስጥ ከ14 ዓመታት በላይ ቆይቷል። የኦሮሚያ ፖሊስ ክለብ ሲመሰረት ከነበሩ አትሌቶች አንዱ ሲሆን ለ11 ዓመታት በኦሮሚያ ፖሊስ አትሌትነት አገልግሏል። ከዚያ በኋላ በኦሮሚያ ፖሊስ የስፖርት ክፍል ኃላፊነትና አሰልጣኝነት ሲሰራም ነበር። ከታዋቂ የኢትዮጵያ አትሌቶች መካከል በማራቶን የዓለም ሻምፒዮን የሆኑትን እነ ታምራት ቶላና ማሬ ዲባባን ከጅምሩ መልምሎ በማውጣት ለውጤት ያበቃ ነው። በተለይ የማራቶን ሻምፒዮኑን ታሞራ ቶላ ከቢሾፍቱ ክለብ አንስቶ ለ7 ዓመታት አሰልጥኖ ታላቅ ደረጃ አድርሶታል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደረጃ ደግሞ ከእነጥሩነሽ ዲባባ ጀምሮ አሁን እስካሉት ታላላቅ አትሌቶችን ከረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሽቦ ጋር በረዳት አሰልጣኝነት ስኬታማ ለማድረግ የቻለ ነው።አሰልጣኝ ቶሌራ ዲንቃ በዓለም ሻምፒዮና በኦሎምፒክ ከፍተኛ ልምድ ካላቸው አሰልጣኞች አንዱ ነው። ከ7 በላይ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎችን፣ 3 የኦሎምፒክ መድረኮችን ተሳትፏል።አሰልጣኝ ቶሌራ ጠንካራ አትሌቶችን ከስር ጀምሮ መልምሎ በማውጣትና ለውጤት በማብቃት የተሳካለት ነው። ይህን አስመልክቶ ለስፖርት አድማስ ሲያብራራ “ከብዙ የኢትዮጵያ አትሌቶች ጋር  ተሰሚነት እና ቀረቤታ አለኝ።  ተስማምቼ፤ ተግባብቼ ነው የምንሰራው። አትሌቶቹን የምመለምልበት የራሴ መንገድ አለኝ። በውድድሮቹ ላይ ደረጃ ማግኘት ባይችሉም ጠንካራ ውጤት ያላቸውን፤ ከትምህርት ቤት ጀምሮ ጥሩ አቅም ያላቸውን ሯጮች በመመልመል ነው የምሠራው። ከኢትዮ ኤሌክትሪክ አትሌቲክስ ክለብ በፊት በኦሮሚያ ፖሊስ የሚገኙ በርካታ አትሌቶችን መልምዬ ያወጣሁበት ልምድ ምሳሌ ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል። እነ ታምራት ቶላ፣ ሹራ ደምሴ፣ ማሬ ዲባባ፣ አዱኛ ታከለ፣ ብርሃኑ በቀለና ሲሳይ ለማ የእኔ ምልምሎች ናቸው። በኢትዮ ኤሌክትሪክ ክለብ ለዓለም ሻምፒዮናው ከተመረጡ 10 አትሌቶች ከ800 ሜትር ሯጯ ሐብታም አለሙ በቀር ሁሉም አትሌቶች በእኔ የተመለመሉና የሚሰለጥኑ ናቸው። ታዳጊዎችን ከስር መልምሎ ለማሳደግ ብልሃት ያስፈልጋል። በኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ  ከዓለም ሻምፒዮናው ቡድን 33 በመቶውን ማስመረጤ በተምሳሌትነት የሚያስጠቅስ ነው።  
"በየትኛውም ክለብ የስራ አመራር ቦርድ በቂ በጀት በመሸፈን መስራት ይኖርበታል እንጅ በአትሌቶች  ምልመላ ላይ እጁን ማስገባት የለበትም።"
ከኢትዮ ኤሌክትሪክ የስፖርት ክለብ ሌሎች የአገሪቱ ክለቦች ምን ሊማሩ ይችላሉ በሚል ከስፖርት አድማስ ለቶሌራ ዲንቃ ጥያቄ ቀርቦለታል። “ማንኛውንም አስተዳደር አመራሩን ነው የሚመስለው። የስራ አመራር ቦርዱ፣ ፕሬዚዳንቱ፣ አሰልጣኙ ሁሉም የየራሱ የኃላፊነት ድርሻ አለው። በየሙያችን የተመደብንበት ኃላፊነት በተግባር  መተርጎም ከሁላችንም ይጠበቃል። አንዱ በአንዱ ኃላፊነት ላይ ጣልቃ መግባት የለበትም። ሁሉም በሙያው ተማምኖ እንዲሰራ መደገፍ ያስፈልጋል። በየትኛውም ክለብ የስራ አመራር ቦርድ በቂ በጀት በመሸፈን መስራት ይኖርበታል እንጅ በአትሌቶች  ምልመላ ላይ እጁን ማስገባት የለበትም። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከተመሰረተ ከ50 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም ለበርካታ ዓመታት ብዙ በጀት እያወጣ ውጤታማ አትሌቶችን  ያቀፈ አልነበረም። ከእኛ በፊት ለክለቡ ብዙ ግምት አይሰጠውም ነበር። አልፎ አልፎ አንዳንድ አትሌቶች ወጥተዋል። እነ መሰለች መልካሙ ውዴ አያሌው… በአሁኑ ወቅት ግን ብዙ ለውጥ አድርጓል። በክለቡ ስምንት አሰልጣኞች መስራት ስንጀምር በአመላመሉ፣ በአሰራሩ ላይ ሙሉ በሙሉ ተሃድሶ ተደርጎ ነው። በአሁኑ ወቅት በኢትዮ ኤሌክትሪክ ያለው የሥራ አመራር ቦርድ አትሌቶችን ለማሰባሰብ በተደረገው ጥረት ለአሰልጣኞቹ ሙሉ ድጋፍ ሰጥተዋል። ከኢትዮጵያ ክለቦች በሚሰጠው የደሞዝ ክፍያ አንደኛ ነው። ለአትሌቶቹ ከቤት ኪራይ አንስቶ የተሟላ ድጋፍ በመስጠት እየሰራ የሚገኝ አስተዳደር ነው። ጥሩ አመራር ካገኘህ የአትሌቲክስ ክለብን ማደራጀት፣ ማዋቀር፣ ጠንካራ አትሌት ማፍራት  የአሰልጣኙ ስራ ነው። “ ሲል መልሷል።
 የቶሌራ የዓለም ሻምፒዮና አስደሳችና አሳዛኝ ትውስታዎች
በአጭር ጊዜ አሰልጣኝነት ልምዴ ብዙ የሚያስደስቱ፣ የሚያሳዝኑ ታሪኮች ገጥመውኛል። በ2013 እ.ኤ.አ ላይ “በሞስኮ በተካሄደው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምዮና እነጥሩነሽ፣ መሰረት ደፋር፣ መሀመድ አማን ወርቅ ሜዳሊያዎች ያገኙበት ነበር። በለንደን ኦሎምፒክም የተመዘገበው አስደናቂ ውጤት ይታወሳል።
እነጥሩነሽ፣ መሠረት፣ ቲኪ ገላና አስደናቂ ውጤት ነበራቸው። በ2015 እ.ኤ.አ ላይ በቤጂንግ በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና ደግሞ ያዘንኩባቸው ተሳትፎዎች ነበሩ። በ10ሺ ሜትር  በወንዶችም በሴቶችም ዝቅተኛ ውጤት አስመዝግበን ነበር።
ከሁሉም ደግሞ የሚያስከፋው በ2011 እ.ኤ.አ ላይ በኮርያ ዴጉ በኢብራሂም ጀይልን በ10ሺ ሜትር በአንድ ወርቅ የተመለስንበት ነው። አሰልጣኝ በደስታውም በሀዘኑም በሁለቱም መሐል ነው የሚቆመው። በ2019 እ.ኤ.አ ላይ በዶሐው የዓለም ሻምፒዮና በ5ሺ ሜትር የተመዘገበው ውጤት ታሪካዊ ነበር። ሙክታር ኢድሪስ ሲያሸንፍ ሰለሞን ባረጋ ሁለተኛ ጥላሁን ኃይሌ አራተኛ ሆኖ ነው የጨረሰው።አሰልጣኝ  ይደሰታልም፣ ይበሳጫልም ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ አሰልጣኝም አትሌትም እንቅልፍ አጥተው እ”ንደሚሰሩ ይታወቃል።
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ የወደፊት አቅጣጫ ላይ ብዙ ጀግና አትሌቶች ያፈራች አገር በልምምድ ቦታ እጥረትና በትራክ አለመሟላት መሰቃየት የለባትም።  
የኢትዮጵያ አትሌቲክስን በአጭር ርቀት እና  በዝላይ ውድድር ከብሔራዊ አትሌት ጀምሮ ያለፍኩበት ነው። አሁን “ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ የሚያስፈልገው ቋሚ መዋቅር ያለውና መሠረተልማት የተሟላለት ብሔራዊ ቡድን መገንባት ነው። ብዙ የአገራትን አትሌቶች በስልጠና ዘዴ መበላሸት ፣ በስፖርት ማዘውተሪያዎች አለመኖር፣ በተለያዩ የምልመላ  መንገድ ላይ እየወደቁ ናቸው። በኢትዮጵያ ውስጥ የስልጠና ቦታዎች ችግር በጣም አለብን። ይህን ሁሉ ዝግጅት እያደረግን ያለነው በዛ ውስጥ ሆነን ነው። የአካዳሚው ትራክ ባይኖር ኖሮ የኢትዮጵያ አትሌቶች አስፋልት ላይ እየሮጡ በትራክ ላይ  ለመወዳደር ይገደዱ ነበር ። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የኦሎምፒክ ኮሚቴው በጋራ ሆነው እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ በጋራ መሰራት ይጠበቅባቸዋል። መንግስትን መገፋፋት አለባቸው። የስፖርት መሰረተ ልማት ችግሮች ካልተስተካከሉ በተተኪ አትሌቶች አሳሳቢ አደጋ እየተደቀነ ነው። አትሌቶች በተለያየ ቦታና ሁኔታ ነው እየሰለጠኑ የሚገኙት፡፡ የጋራ ውድድር ለማድረግ እየከበደም መጥቷል፡፡ ወጥ የሆነ የስልጠና መዋቅር መዘርጋት አለበት፡፡
የልምምድ መሥርያ ቦታ መጣበብ እያስጨነቀን ነው፡፡ እየተጠበባቅን ነው እየሰራን የቆየነው፡፡ ብዙ ጀግና አትሌቶች ያፈራች አገር በልምምድ ቦታ እጥረትና በትራክ አለመሟላት መሰቃየት የለባትም። ሕዝቡም መንግስትም ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡በተለይ የሚመለክተው የባህልና ስፖርት ሚኒስተር ነው። ባለድርሻ አካላት አስተባብሮ ለ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ ቶሎ ርምጃ መውሰድ ይጠበቃል። ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ በቂ የስፖርት መሠረተልማት ካልተገነባ በመካከለኛ ርቀት ውድድርሮችም አትሌቶችን ማፍራት የተቸገርንበት ሁኔታ  ወደ ረጅም ርቀት ተሸጋግሮ የባሰ ጥፋት እንዳይ’መጣ ስጋት አለ፡፡

             ባለፈው ሻምፒዮና ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎች ጨምሮ አራት ሜዳሊያዎች የሰበሰበው አሰልጣኝ ህሉፍ ይህደጎ
የቀድሞ አትሌትና የአሁኑ ውጤታማ አሰልጣኝ  ህሉፍ ይህደጎ የተገኘው ከትግራይ ክልል አድዋ ከተማ ነው። ከዓመት በፊት በአሜሪካ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በዋና አሰልጣኝነት  4 ሜዳልያዎችን 2 የወርቅ፣  አንድ የብርና  1 ነሐስ አግኝቷል። ቡዳፔስት በምታስተናግደው የዓለም ሻምፒዮና ላይ 6 አትሌቶችን በማስመረጥ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል። በ1500 ፍሬወይኒ ሃይሉ እና ብርቄ ሐየሎም፤ በ800 ሜትር ወርቅነሽ መሰለ፣ በ5ሺና በ10ሺ ሜትር ጉዳፍ ፀጋየ፣ ቀ5ሺ ሜትር  ፍሬወይኒ ጸጋዬና ለምለም ሐይሉ ናቸው። አሰልጣኝ ህሉፍ ለዓለም ሻምፒዮናው ያደረገውን ዝግጅት አስመልክቶ ሲናገር “በዓለም አቀፍ ውድድር ውስጥ ስለሆነን  ሁሌም ዝግጅት እናደርጋለን። ለዓለም ሻምፒዮናው ያደረግነው ዝግጅት ልዩ የሚያደርገው ከ1 ወር በላይ ከውድድር ውጭ ሆነን ልምምድ  ስንሰራ በመቆየታችን ነው። በአጠቃላይ ግን አመቱን ሙሉ በጥሩ አቋምና ብቃት ዝግጅትና ልምምድ ስናደርግ ቆይተናል።” ብሏል
ጉዳፍ በመጀመሪያ በ10ሺ ሜትር ከምታደርገው ውድድር በኋላ ነው በ5ሺ ደግሞ የመሮጧ ነገር የሚወሠነው።
በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በከፍተኛ ሁኔታ ከሚጠበቁ አትሌቶች አንዷ ጉዳፍ ፀጋይ ዋንኛዋ ናት። አትሌት ጉዳፍ ቡዳፔስት ላይ ሻምፒዮናነቷን ለማስጠበቅ ከመሮጧ ባሻገር፣ በ10ሺና በ5ሺ ሜትር ለመሳተፍ እንደምትችል ብዙዎች እየገመቱ ናቸው። አሰልጣኝ ህሉፍ በዚህ ዙርያ በሰጠው አስተያየት “በሻምፒዮናው ላይ ጉዳፍ  ብቻ ሳትሆን እነ ጎይተቶም፣ ለተሰንበት፣ ታምራት፣ ሰለሞንና ሌሎችም አትሌቶች ይጠበቃሉ። ጉዳፍ በዚህ የዓለም ሻምፒዮና ላይ በሁለቱም ርቀቶች እንደምትሮጥ ስሟ ተመዝግቧል። ግን በመጀመሪያ በ10ሺ ሜትር ከምታደርገው ውድድር በኋላ ነው በ5ሺ ደግሞ የመሮጧ ነገር የሚወሠነው። ቡዳፔስት ላይ ሞቃታማ አየር ሊኖር ይችላል። ስለዚህም በሁለቱም ርቀቶች የመሳተፉ ነገር በተሟላ ብቃቷ ላይ ይወሰናል ። ሁለቱን ርቀቶች ለመሮጥ ይበልጥ አቅም ይኖራታል አይኖራትም እንደ አሰልጣኝ በውድድር ስፍራ ላይ ተመልክተን ነው  የምንወስነው …”
“ሁሌም ተፎካካሪዎቻችን ኬንያውያን ናቸው”
በረጅም ርቀት ለኢትዮጵያ አትሌቶች ተፎካካሪዎች እነማን ይሆናሉ በሚል ጥያቄ ዙሪያ አሰልጣኝ ህሉፍ አስተያየት ሲሰጥ “ባለፈው የዓለም ሻምፒዮና ከኬንያ በልጠን 10 ሜዳልያዎች አምጥተናል። ሁሌም ተፎካካሪያችን ኬንያውያን ናቸው። በዓለም ሻምፒዮና ላይ የሜዳልያ ውጤትን የሚወስነው  የሌሎች አገራት ተፎካካሪዎች ወቅታዊ ብቃት ነው። ኬንያውያን ዘንድሮ ያላቸውን ብቃት አጠናክረው እንደሚመጡ ነው የምገምተው። ኬንያ በተለይ ከባድ ተፎካካሪያችን ትሆናለች የምለው ከቡዳፔስት ሞቃታማ አየር ጋር በማያያዝ ነው።  አምና የተሻለ ውጤት የነበረን የኦሬጎን አየር ቀዝቃዛ ስለነበር ነው። ከአዲስ አበባ አየር ጋር ይቀራረብ ነበር። ቡዳፔስት ላይ ከኦሬጎን ተቃራኒ አየር ነው የሚጠብቀን። ሞቃታማ ነው። በውድድሩ ሙቀት ከ28 እስከ 33 ዲግሪ እንደሚሆን ይገመታል። ካለፉት ሻምፒዮናዎች ያገኘነው ልምድ እንደሚያመለክተው ደግሞ ኬንያውያን በሞቃታማ አየር የተሻለ ውጤት ያስመዘግባሉ። እንደ አሰልጣኝ የሙቀቱ ጉዳይ ያሰጋኛል”ሲል አሰልጣኝ ህሉፍ ተናግሯል።
ቡዳፔስት ላይ ምን ያህል ሜዳልያ ትጠብቃለህ ተብሎ የተጠየቀው ህሉፍ  “በብዙ ምክንያት ያምናውን ውጤት ለመጠበቅ የሚከብድ ይሆናል፡፡ የኦሬጎን ሻምፒዮና የተካሄደው ሐምሌ ላይ ነው-------- ደግሞ በነሐሴ ነው፡፡ አምና ሰኔ አካባቢ ብዙም ዝናብ ሳይገባ ነው ትሬኒንግ ጨርሰን ወደ ዓለም ሻምፒዮናው የሄድነው፡፡ ሞቹ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ሙቀቱ የሚያሰጋን ቢሆንም ቡዳፔስት ላይ በአጠቃላይ ጥሩ ተፎካካሪ እንደምንሆን እጠብቃለሁ።” ሲል ተናግሯል
"ከሁሉም በማስቀደም ለአትሌቲክስ ተገቢውን መሰረተ ልማት እንዲዘረጋ ነው የምንጠይቀው።”
ወደ ኢትዮጵያ አትሌቲክስ አሰልጣኝነት ከመጣ 6 ዓመት የሆነው ህሉፍ በቶኪዮ ኦሎምፒክና በኦሬጎን የዓለም ሻምፒዮና ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በዋና አሰልጣኝነት እየሰራ መቆየቱ ይታወቃል። በዚህ አጭር የአሰልጣኝነት ዘመኑ በከፍተኛ ደረጃ አሳሳቢ የሆነበት ጉዳይ የስፖርት መሠረተ ልማት በቂ አለመሆኑ ነው። “በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ትልቁ ፈተና የልምምድ ትራክ አለመኖር ነው። ከዓለም አትሌቲክስ ውጤታማ ከሚባሉ አገሮች አንዱ ብንሆንም ከልምምድ ትራክና ከስፖርት ማዘውተርያ ስፍራ ጋር በተያያዘ በቂ መሰረተ ልማት አለመኖሩ በስፖርቱ ለምንገኝበት ደረጃ የማይመጥን ነው። ለዚህ ሻምፒዮና ባደረግነው ዝግጅት ወደ ትራክ እየገባን የነበረው ተራ በተራ፤ በልመናና በግፊያ ነው። የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ለዚህ አሳሳቢ ችግር መፍትሔ እንዲሰጡበት ጥሪ አቀርባሁ። ከሁሉም በማስቀደም ለአትሌቲክስ ተገቢውን መሰረተ ልማት እንዲዘረጋ ነው የምንጠይቀው።”
“የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ውሳኔ ለኢትዮጵያም ትምህርት ነው፡፡ አሰልጣኞቹ መበረታታት ያስፈልጋቸዋል፡፡”
በዓለም ሻምፒዮናው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አትሌቶችን ውጤታማ ላደረጉ አሰልጣኞች የሜዳልያ ሽልማት እንደሚሰጥ ተገልጿል። “የዓለም አትሌቲክስ ይህን አዲስ አሰራር በመፍጠሩ ትልቅ ቁምነገር ነው።  ባሰለጠንካቸው አትሌቶች አራት አምስትም ሜዳሊያዎች ብታመጣ እንደ አሰልጣኝ የተለየ ሽልማት አይገኝበትም ነበር። ጥሩ የሜዳልያ ውጤት ቢኖርም የሚሰጥህ ሽልማት የሚያስደስት አይደለም። ሯጭ የሚያወጣው አሰልጣኝ ነው፡፡ ስለዚህም የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ውሳኔ ለኢትዮጵያም ትምህርት ነው፡፡ አሰልጣኞቹ መበረታታት ያስፈልጋቸዋል፡፡”
“በአዲስ አመት መግቢያ አትሌቶች ድል ሲያስመዘግቡ አዲስ ዘመን የመጣ ነው የሚመስለው፡፡”
የኢትዮጵያ አትሌቶች በአገሪቱ ሁኔታ ላይ የሚፈጥሩትን  ስሜት እንዴት ትመለከተዋለህ የሚል ጥያቄ የቀረበለት  አሰልጣኝ ህሉፍ “ስፓርት በተለይ አትሌቲክስ ለኢትዮጵያ በጣም ወሳኝ መስክ ነው፡፡ አገራችንን የሚያስጠራው አትሌቲክስ ነው፡፡ በአዲስ አመት መግቢያ አትሌቶች ድል ሲያስመዘግቡ አዲስ ዘመን የመጣ ነው የሚመስለው፡፡ ባለፈው ሻምፒዮና የትግራይ አትሌቶች ውጤታማ ሲሆኑ በዚያ ክልል ጦርነትና ሌሎች የከፉ ችግሮች ነበሩ። ከድል በኋላ ሁሉ ነገር ወደ ሠላም መጣ። እውነት ለመናገር አትሌቶቹ በመካከላቸው ምንም ችግር የላቸውም፡፡ የአትሌቶቹ አንድነት እኔም ይገርመኛል፡፡ ምንም ልዩነት የላቸውም። ከአንድ አካባቢ እንደመጡ ነው የሚሰሩት። ይህም ከቶኪዮ ኦሎምፒክ ጀምሮ ያየሁት ነው።  በመጨረሻም የማስተላልፈው መልዕክት የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሌም ከአትሌቲክሱ ጀርባ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ከውጤት በላይ ቢኖር ብታደርግለት ትመኛለህ፡፡ ለአትሌቲክሱ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ በማንኛውም በሚሰጥህ አክብሮት ትረዳለህ ፡፡ ወደፊትም አክብሮታቸውን አብዝ ይስጠን፡፡ ከዚህ በመነሳት የስፖርት ማዘውተሪያዎቹ እንዲገነቡ ህዝባችን ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል”


Read 866 times