Saturday, 12 August 2023 20:46

ሩሲያ ለኢትዮጵያ አስተማማኝ አጋር ሆና እንደምትቀጥል አምባሳደር ኢቭጌኒ ቴሬሂን ገለጹ

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(0 votes)

በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ቴሬሂን፣ ከትናንት በስቲያ ሃሙስ፣በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በሁለተኛው የሩሲያ - አፍሪካ ጉባኤ የውይይት አጀንዳዎች፤ የትኩረት አቅጣጫዎችና የተገኙ ውጤቶች ዙርያ ማብራርያ ሰጥተዋል።
ጉባኤው የሩሲያና አፍሪካን አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያጠናክር አምባሳደሩ ጠቁመዋዋል፡፡
በሁለተኛው የሩሲያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ የተገኙትን ዋና ዋና ስኬቶችና አቅጣጫዎች በማንሳትም፣ የሩሲያ-አፍሪካን አጋርነት በጥራት ወደ አዲስ ደረጃ ለማድረስ ያለመ  ነው ብለዋል።
በሴንትፒተስበርጉ ጉባዔ ላይ የተሳተፉት አምባሳደር  ኢቭጌኒ፤ ሩሲያና አፍሪካ ለእድገትና ልማት የሚኖራቸው ትብብር እየተጠናከረ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአጠቃላይ ጉባዔው ገንቢ ውይይቶች የተደረጉበትና በወዳጅነት መንፈስ የተካሄደ እንደነበር መሥክረዋል።
ሩሲያ በውጭ ጉዳይ ፖሊስዋ የአፍሪካን ሉአላዊነት እንደምታከብርና እንደምትደግፍ የጠቆሙት አምባሳደሩ፤ ስትራቴጂካዊ አጋርነታችን ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን በዓለም ላይ መዘርጋት ነው ብለዋል። ኒዮኮሎኒያሊዝምን፤ ህገ-ወጥ ማዕቀቦችንና ባህላዊ እሴቶችን የመናድ አዝማሚያዎችን እንቃወማለን ሲሉም ተናግረዋል።
በሩሲያ የሚገኙ  ኩባንያዎች በሕዝብ አስተዳደር፣ በባንክና በሌሎች የኢኮኖሚ መዋቅሮች ላይ አስፈላጊ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን የገለፁት አምባሳደሩ፤ በአለም አቀፍ የምግብ ዋስትና ላይ የሚደርሱ ስጋቶችን ለማስቆምና ለታዳጊ ሀገራት እርዳታ ለመስጠት ጥልቅ ውይይት መካሄዱን፤ ለአፍሪካ ወዳጆቿ በግብርናው መስክ ዘላቂ ውጤት ለማግኘት  እንደምትሰራ በጉባኤው መረጋገጡን ጠቅሰው፤ በአፍሪካ የጤናውን ዘርፍ ለማገዝ  የህክምና መሳሪያዎችን በማቅረብ፣ ወረርሽኞችን ለመዋጋት የሚደረጉ ዘመቻዎችን በመደገፍ ሩሲያ መሥራቷን እንደምትቀጥልም በስምምነቱ መካተቱን ጠቁመዋል፡፡
 ሩሲያ በቴክኖሎጂ መስክ ለአፍሪካ ከፍተኛ እገዛ ለመስጠት እንደተዘጋጀች በጉባኤው ላይ መነሳቱን የገለፁት አምባሳደር ኢቭጌኒ፤ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለአፍሪካ በፍጥነት ለማድረስና ለማስተዋወቅ፤ በኢንፎርሜሽን ቴክሎጂ፣ በቴሌኮሚኒኬሽንና በጠፈር ሳይንስ የየእውቀት ሽግግር ለማድረግ  ማቀዷንም  አብራርተዋል።
በአፍሪካ አህጉር ያለውን የሃይል አቅርቦት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመዘርጋት ሩሲያ በጂዮ- ተርማል፣ በሐይድሮ ፓወርና በሰላማዊ የኒኩሌር ኃይል ግንባታ ላይ ለመሥራት በሩሲያ ዘንድ ፍላጎት መኖሩንም ጠቅሰዋል። የኒውክሌር ኃይልን ለሰላማዊ ጥቅም ለማዋል በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል ከ4 ዓመት በፊት በሶቺ ከተማ የተፈጸመው ስምምነት፣ ሴንትፒተርስበርግ ላይ እንዲሻሻል መደረጉንም አምባሳደር  ኢቭጌኒ ገልፀዋል።


Read 689 times