Saturday, 12 August 2023 20:44

የአብን ምክትል ሊቀ መንበር ከሃላፊነታቸው ለቀቁ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ምክትል ሊቀመንበር አቶ መልካሙ ሹምዬ፣ ከድርጅቱ የምክትል ሊቀመንበርነትና ከስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት ሰሞኑን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸው ታውቋል፡፡
በሳለፈው ረቡዕ ነሐሴ 3 ቀን 2015 ዓ.ም ለፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ በተፃፈ ደብዳቤ፣ ከድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበርነትና ከስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ያሳወቁት የፓርቲው ም/ሊቀመንበር አቶ መልካሙ ሹምዬ ሃላፊነታቸው ለመልቀቃቸው ምክንያት የሆነው ጉዳይ ከአብላጫ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጋር ያላቸው የአቋም ልዩነት እየሰፋ በመሄዱ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
“በክልሉ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበርና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆኖ መቀጠሉ የድርጅቱንና የህዝቡን ጥቅም የሚያስከብር ሆኖ ባለማግኘቴ ሃላፊነቴን ለመልቀቅ ወስኛለሁ” ያሉት ም/ሊቀመንበሩ በፓርቲው ማእከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው ግን እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል በጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ላይና በገዢው መንግስት ላይ የሰላ ትችት በመሰንዘር የሚታወቁት  የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባልና የአብን ፓርቲ አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የፀጥታ ሃይሎች ከቤታቸው ወስደው እንዳሰሯቸው ይታወሳል፡፡

Read 1609 times