Sunday, 06 August 2023 00:00

አርባምንጭ ደርሶ መልስ - አይረሴ ጉዞ ! (በወፍ በረር)

Written by 
Rate this item
(0 votes)

እንግዲህ ከሰሞኑ   ያደረግነውን  የአርባምንጭ  ጉዞ በተመለከተ በራሴ ተነሳሽነት (በህዝብ ሳልጠየቅ ማለቴ ነው) አስተያየት የጻፍኩኝ የመጀመሪያው ጋዜጠኛ እኔ ሳልሆን አልቀርም፡፡ በእርግጥ እኔም ቀልቤ ጻፍ ጻፍ ብሎ ቢወተውተኝ ነው፣ ከመሸ  ወዲህ የከተብኩት፡፡

አስተያየቱ ምን ላይ ያተኩራል ለሚለው ጥያቄ፣ ምላሼ፣ አንብባችሁ ድረሱበት የሚል ነው፡፡ በጣም አጭር ስለሆነ  ትንሽ ብቻ  ታገሱ፡፡

እስካሁን ድረስ እንደ ብዙዎቹ ሪፖርተሮቹ ባይሆንም፣ ብዙ ቦታ ተጉዣለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ ሁለቴ ናይሮቢ ለሥልጠና የተጓዝኩትን ጨምሮ፣ በርካታ የአገር ውስጥ ጉዞም አድርጌያለሁ፡፡ ነገር ግን የትኞቹም ጉዞዎች የአርባምንጭን አያክሉም፡፡ አርባምንጭ እንዴት ከናይሮቢ ጋር ይወዳደራል ከተባለ ምክንያቶቼን በቅጡ አቀርባለሁ፡፡ ለእኔ የአርባምንጩ ድንገተኛ የ4 ቀን ጉዞ፣ የሥራ ብቻ አይደለም፤ የመዝናናት፣ አገር የማየት፣ አየር የመለወጥ፣ የማላውቃቸውን አዳዲስ ጋዜጠኞች የመተዋወቅ (ኔትዎርክ የማስፋት) ጭምር ነው፡፡ አዲስ የህይወት ተሞክሮ እንደማለት ነው፡፡ ድንገተኛም መሆኑ  ልዩ ያደርገዋል፡፡ በአንድ ቀን ተነግሮኝ ነው ለጉዞ የተነሳሁት፡፡ በዚህ ወቅት ከአዲስ አበባ መውጣት ለራስም ለቤተሰብም ስጋት ስለሚፈጥር በቅርቡ ከፊንፊኔ ወጥቼ አላውቅም፡፡

ከመጀመሪያውም የአርባምንጩ  ጉዞ ሲነገረኝ፣ (ያውም በአንድ ቀን ብቻ Notice)፣ለምን እንደምንሄድ እንኳን ሳልጠይቅ ነው የተስማማሁት፡፡ ቀልቤን (ፈረንጅ instinct እንዲል) አድምጬ ነው እንጂ፣ በቅጡ አስቤበት አይደለም፡፡ ለቤተሰብ  እንኳን ሳላሳውቅ ነው በራሴ የወሰንኩት፡፡ ደግነቱ እነሱም  ብዙ አልተቃወሙም፡፡

ቀልቤን በማዳመጤም ሳይሆን አይቀርም፣ ጉዞው የተቀዋጣለትና የሰመረለት የሆነው፡፡ ከሁሉም በላይ ጉዞውን አስደሳች ያደረገው ግን ተጀምሮ እስኪጠናቀቀቅ ድረስ በፍቅር፣ በጨዋታ፣ በመተሳሰብና በመከባበር የታጀበ በመሆኑ ይመስለኛል፡፡ ( ከተሳሳትኩ እታረማለሁ)  ጉዞው በተጨማሪም  ነጻነትና እኩልነት፣ ፍትህና ዲሞክራሲያዊነት የሰፈነበት (ያውም ከአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች በእጅጉ የተሻለ) ነበር ማለት ይቻላል፤ያለ ምንም ማጋነነን፡፡  

በዚያ ላይ የጉዞውን አስተባባሪ ተሼን ጨምሮ፣ ሁሉም ጋዜጠኞች፣ ነጻና ተጫዋች (የማያካብዱ)፣ ቀልድና ተረብ የሚወዱ፤ (የገባቸው የሚባሉ)  ናቸው፤ በጉዞው  ብቸኛዋ የሄዋን ዘር የነበረችውን ጋዜጠኛ ጨምሮ ማለት ነው፡፡

ሌላው ቀርቶ ከዚህ በፊት የማናውቀው ቴዲ የተባለው ሹፌራችን ሳይቀር፣ የጋዜጠኞች ቡድኑን መንፈስና ስሜት በቅጡ ተገንዝቦ፣ በተመሳሳይ ቫይብና ሥልተ-ምት ለመንቀሳቀስ ሲሞክር ነው የተስተዋለው፤ስንሄድም ስንመጣም፡፡ ለዚህ ደግሞ የጉዞው አስተባባሪ፣ ሰብአዊና ወዳጃዊ አቀራረብ ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል ባይ ነኝ፡፡ የተሼ ጠንካራ ጎን የሚጀምረው እንግዲህ ከዚህ ነው፡፡ (የአራዳ ልጅ ይሏል ይሄ ነው!)

የጉዟችን አስተባባሪና መሪ (ተሼ)፤ ከሳቅና ጨዋታ በቀር ጭቅጭና ንትርክ አይመቸውም፡፡ የሥራ ባልደረቦቹ፣ የሥራ ባልደረቦች ብቻ ሳይሆኑ ጓደኞቹም ጭምር ናቸው፡፡ እንደ ጓደኛ ያከብራቸዋል፤ ያስብላቸዋል፤ምቾታቸው እንዳይጓደል የቻለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ ይህንን ነው በ4 ቀናት የአርባምንጭ ጉዟችን የታዘብኩት፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ተሼ የዋህ፣ ቀና አመለካከት ያለው፣ ከጥቃቅን ተራ ጉዳዮች ይልቅ ትላልቅ ረብ ያላቸው ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር መሆኑንም  በግሌ ተገንዝቤአለሁ፡፡  ነገ ሊደርስበት ያለመው ትልቅ ህልምና ግብ በትክክል አስቀምጦ፣ በትጋት እየሰራ ያለ መሆኑን ለማወቅ ነቢይ መሆን አይጠይቅም፡፡  

በሌላ በኩል፤ይሄን ጉዞ አስደሳችና አይረሴ የሚያደርገው ሌላው ጉዳይ ደግሞ ወደ አርባምንጭ የተጓዝንበትን  ዋና ዓላማ፣ ሙሉ በሙሉ ማሳካት መቻላችን ነው፡፡ የምንፈልጋቸውን መረጃዎች በቀጥታ ከጉዳዩ ባለቤቶች (from the horse’s mouth እንዲሉ) አግኝተናል፤ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ይሏል ይኼ ነው፡፡  

አርባምንጭ የቆየነው ለሦስት ቀናት ብቻ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች፣ በሦስት የተለያዩ ሆቴሎች ውስጥ ማደራችንን ወድጄዋለሁ፡፡ አገር ካዩ አይቀር እንዲህ ነው፡፡ የአርባምንጭን ጥሬ ሥጋ በቆጭቆጫ እንዲሁም አገሩ የሚታወቅበትን ምርጥ ዓሳ በጥብሱም በዱለቱም በደንብ አጣጥመናል፡፡ የአካባቢው  ተስማሚ የአየር ንብረትና  ማራኪው መልክአምድርም የሚረሳ አይደለም፡፡ እዚህ  ጋ  የአርባምንጮችን  እንግዳ ተቀባይነትና ልዩ መስተንግዶ  ሳይጠቅሱ ማለፍ ንፉግነት ነው የሚሆነው፡፡ ከልብ እናመሰግናለን፡፡

በመጨረሻም የጉዞውን አስተባባሪና የጋዜጠኞች ቡድን አባላት፣ ላሳለፍነው አስደሳችና አይረሴ ጊዜ ሁሉ ላመሰግናቸው  እወዳለሁ፡፡ ወደፊት ስለ አርባምንጭ ያየሁትንና የማረከኝን በስፋት ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ የነገ ሰው ይበለን፡፡
ፈጣሪ ሰላሙን ያውርድልን !

Read 1355 times