Saturday, 05 August 2023 12:34

ከ”ሜዳልያ አዳኙ” ረ/ኮሚሽነር ሁሴን ሼቦ ጋር

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

   (የኢትዮጵያ ቡድን የ5ሺ ሜ . እና 10ሺ ሜ ዋና አሰልጣኝ)
                   

       በዓለም አትሌቲክስ  በተለይ የትራክ ሩጫ የላቀ ስኬት ያገኙ ናቸው። በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ባስመዘገቡት ውጤት “ሜዳሊያ አዳኙ” በሚል ልዮ ስም ተሞካሽተዋል። በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከ30 ዓመታት በላይ ባሳለፉት የአሰልጣኝነት ዘመናቸው  6 ኦሊምፒኮች ፤ 6 የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ፤ 12 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ተሳትፈዋል። በአጠቃላይ  ከ370 በላይ ሜዳሊያዎችን ከኢትዮጵያ ቡድን ጋር አግኝተዋል።


          ረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሼቦ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከፍተኛ ውጤት ካስዘገቡ የዓለማችን ምርጥ የረጅም ርቀት (10ሺና 5ሺ) አሰልጣኞች አንዱ ናቸው። ይህን ልምዳቸውን በማስመልከት ለስፖርት አድማስ ሲናገሩ “ዓለም ሻምፒዮና እንደቤቴ ነው። አሰልጣኝ ከሆንኩ 31 ዓመት ሆኖኛል። በተሳተፍኩባቸው “የዓለም ሻምፒዮናዎች አብዛኛውን ጊዜ በብቃት አትሌቶችን እንደማስመረጤ የስራ ፍሬውን ለማየት ችያለሁ። አገራችን ኢትዮጵያ ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገበችባቸው ዓለምአቀፍ  ውድድሮች የዓለም ሻምፒዮና አንዱ ነው። የድሉ ተቋዳሽና ባለቤት በመሆኔ እጅግ በጣም ደስተኛ
ኢትዮጵያ ዛሬም ቢሆን በ10ሺ ሜትር እና በ5ሺ ሜትር ከዓለም ከፍተኛውን የሜዳሊያ ስብስብ ያስመዘገበች አገር መሆኗ መታወቅ ይኖርበታል።
የኢትዮጵያ ታላላቅ አትሌቶች በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በተለይ በረጅም ርቀት ውድድሮች ተደጋጋሚ ውጤቶችን በማስመዝገብ ይታወቃሉ።  በከፍተኛ የሜዳልያ ስብስባቸው በከፍተኛ የሜዳልያ ስብስባቸው ከዓለም ቀዳሚ የሆኑትን ኃይሌ ገ/ስላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለና ጥሩነሽ ዲባባን መጥቀስ ይበቃል። ባለንበት አትሌቶች በሚወዳደሩባቸው ሻምፒዮናዎች ውጤታማነታቸውን ለመቀጠልና ሻምፒዮናነትን ለማስጠበቅ ለምን ይቸግራቸዋል? በሚልም ለአሰልጣኙ ጥያቄ ቀርቧል።
“ዛሬም ቢሆን ብቃት ያላቸውን አትሌቶች እያፈራን ነው። አለመገጣጠም ሆኖ ነው። አትሌቶቻችን ከፍተኛ ብቃትና አቋም ላይ  በሚገኙበት ወቅት ውድድሮች ባለመኖራቸው፣ የአየር ሁኔታው አለመመቻቸትና  የተለያዩ ምክንያቶች ይኖራሉ።
እነ ኃይሌ፣ ቀነኒሳ፣ ሞፋራህ ለአትሌቲክሱ ዓለም ክስተቶች ነበሩ። በተሟላ ብቃት ጎልተው በሚመጡበት ጊዜ ውድድሮች በብዛት በመኖራቸው በውጤታቸው የበላይነት ያሳያሉ። ኢትዮጵያ ዛሬም ቢሆን በ10ሺ ሜትር እና በ5ሺ ሜትር ከዓለም ከፍተኛውን የሜዳሊያ ስብስብ ያስመዘገበች አገር መሆኗ መታወቅ ይኖርበታል። አሁንም በዛ ደረጃ ላይ ነው የምንገኘው። ያንንም ለማስቀጠል እየሰራን ነው።” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ቡዳፔስት ከምታስተናግደው የዓለም ሻምፒዮና በፊት ኢትዮጵያ በተሳተፈቻቸው ያለፉት 18 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ካስመዘገባቻቸው የሜዳሊያ ስብስቦች ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስዱት በ10ሺና በ5ሺ ሜትር ውድድሮች በሁለቱም ፆታዎች የተመዘገቡ ውጤቶች ናቸው። በ10ሺ ሜትር በወንዶች 9 የወርቅ፣ 6 የብርና 4 የነሐስ ሜዳሊያዎች እንዲሁም በሴቶች 8 የወርቅ፣ 8 የብርና  4 የነሐስ ሜዳሊያዎች ተገኝተዋል። በ5ሺ ሜትር በሴቶች 6 የወርቅ፣ 2 የብርና 8 የነሐስ ሜዳሊያ እንዲሁም በወንዶች ደግሞ 3 የወርቅ፣ 5 የብርና 4 የነሐስ ሜዳሊያዎች ተመዝግበዋል።

“ክብራችንን ለማስመለስ በቁጭት
እየሰራን ነው።”
በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የኢትዮጵያ ቡድን ይህን ታሪክ ለማስጠበቅ ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደረግ ቆይቷል። በሁለቱም ርቀቶች በሁለቱም ፆታዎች ተቀራራቢ ብቃት ያላቸው አትሌቶች መያዛቸው የሜዳሊያ ግምት ያሳድራል። በ10ሺ ሜትርና በ5ሺ ሜትር በሁለቱም ፆታዎች 13 አትሌቶች ዝግጅት ሲያደርጉ ሰንብተዋል። በሪሁ አረጋዊ፣ ሰለሞን ባረጋ፣ ይሰማው ድል፣ ታደሰ ወርቁ፣ ለተሰንት ግደይ፣ ጉዳፍ ፀጋይ፣ እጅጋየሁ ታዬ፣ ለምለም ሃይሉ፣ ሚዛን ዓለም፤ ዮሚፍ ቀጀልቻ፣ ጥላሁን ኃይሌ፣ ሀጎስ ገ/ህይወት መዲና ኢሳ ናቸው።
በዓለም ሻምፒዮና በ10ሺ ሜትር ወንዶች ኢትዮጵያ የነበራት በላይነት ላለፉት 5 ሻምፒዮናዎች መነጠቁ ይታወቃል። ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፈው በ2011 እ.ኤ.አ በኮርያ ዳጉ ኢብራሂም ጄይላን ነበር። በ2013፣ 2015ና 2017 ላይ የእንግሊዙ ሞፋራህ፤ በ2019 እና በ2022 ኡጋንዳው ጆሸዋ ቼኘቴጊ የወርቅ ሜዳሊያውን ወስደዋል። ዘንድሮ 10ሺ ሜትርን ክብር ወደ ኢትዮጵያ ስለመመለስ ዋና አሰልጣኝ ሁሴን ሼቦ (ረዳት ኮሚሽነር) አጭር አስተያየት አላቸው።
“ክብራችንን ለማስመለስ በቁጭት እየሰራን ነው። ልጆቹም ይህን እንደሚያደርጉት እጠብቃለሁ። ዋና ዓላማችንም ይሄው ነው። የእነኃይሌን፣ የእነቀነኒሳን ታሪክ መድገም ነው የምንፈልገው።”

“ሔልሲንኪ ላይ አትሌቶቻችን ተከታትለው የገቡባቸው ድሎች የማይረሱ ናቸው።”
በብዙዎቹ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አፍሪቃዎች የማይረሱ የዓለም ሻምፒዮናዎች አሉ። በ2003 እ.ኤ.አ ላይ በፈረንሳይ  ሲንት ኢቴን ጥሩነሽ ዲባባ በ17 ዓመቷ ያስመዘገበችው የወርቅ ሜዳሊያ፤ ቀነኒሳ በቀለ በ2009 በርሊን ላይ በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር ያስመዘገበው ድርብ ድል… ለዋና አሰልጣኝ ሁሴን ሼቦ (ረዳት ኮሚሽነር) የማይዘነጉት የዓለም ሻምፒዮና የቱ ይሆን? “በ2005 እ.ኤ.አ ላይ በፊንላንድ ሄልሲንኪ ዓለም ሻምፒዮና በታሪክ የመጀመሪያው ከፍተኛ ውጤት ነው። በርግጥ በ2022 እ.ኤአ ዮጂን ላይም በሜዳልያ  ስብስብ የላቀ ውጤት ተመዝግቧል። ሔልሲንኪ ላይ አትሌቶቻችን ተከታትለው የገቡባቸው ድሎች የማይረሱ ናቸው። ባለፈው ሻምፒዮና በማራቶን ለሁለቱም ፆታዎች የተመዘገበው ውጤትም የሚያስደንቅ ነው። በአብዛኛዎቹ ሻምፒዮናዎች ቀዳሚ ሆነን ነው የምንገኘው። ቢያንስ ከዓለም ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ይዘን ነው የምንጨርሰው። በአፍሪካ ትልቁን ውጤት እያስመዘገብን መቆየታችን ለእኔ ትልቅ ትዝታ ነው።”
የዘንድሮው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዝግጅት በስፖርት መሰረተ ልማቶች አለመሟላት ተፈትኗል። አሰልጣኞችና አትሌቶች የልምምድ ቦታዎች ተሟልተው ባለመኖራቸው በዝግጅታቸው ላይ ጫና እንዲደረግባቸው በተለያየ መንገድ ገልጸዋል።
“በቀጣይ ኦሎምፒክ፣ የዓለም ሻምፒዮና፣ መላው አፍሪካ ጨዋታዎች፣ አገር አቋራጭ አለ… ከሚያሳስቡን ነገሮች አንደኛው የማዘውተሪያ ስፍራ ነው። ትራክ የለም። አሁን ያለንበት ክረምት ነው።  በየጫካው መሠረተ ልማቱ የተሟላ አይደለም። አንድ አይናችን ለሆነው አትሌቲክስ ለወደፊት እንዴት መስራት እንደሚቻል እንደመንግስት ሊታሰብበት ይገባል።….. ያው አልተኛንም። እንደመፍትሄ ባገኘነው አካዳሚው ትራክ ላይ ተጨናንቀን እየሰራን ነው።
ወደ ሱሉልታ፣ ሰንዳፋና ገላን ከተሞች በመሄድም ለዓለም ሻምፒዮናው ዝግጅት ስናደርግ ቆይተናል። ያሉንን መልክአ ምድሮች ተጠቅመን እየሰራን እንገኛለን።” በማለት ዋና አሰልጣኙ ሁሴን ለስፖርት አድማስ ተናግረዋል።

“አትሌቶች ለውጤቶቻቸው፣ ለአገራቸው፣ ለባንዲራቸው ነው የሚሰሩት።”
በሐንጋሪ ቡዳፔስት በሚካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ለኢትዮጵያ የቅርብ ተቀናቃኝ የሆነችው ኬንያ ናት። የኬንያ ቡድን 57 አትሌቶች (32ወ፣ 25ሴ) በመያዝ ኪሳራኒ ውስጥ በሚገኘው የሞይ ኢንተርናሽናል የስፖርት ማዕከል ከ2ወራት በላይ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። በወንዶች የአጭር ርቀት ውድድሮች ለሜዳልያ የሚጠበቁ አትሌቶችን የያዘው ቡድኑ በርምጃ  ውድድና በጦር ውድድርና በጦር ውርወራ በመሳተፉ ከኢትዮጵያ በመካከለኛ ርቀት፣ በ10ሺና በ5ሺ ሜትር እንዲሁም በማራቶን ውድድር ከፍተኛ  ፉክክር በማድረግ ከአፍሪካ 1ኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቅን አቅደዋል። የኬንያ ቡድን መሪ ዴቪድበኔይ ይባላሉ።
ጁሊዬስ ኪራዋና ዴቪድ ሴቲንግ ዋና አሰልጣኞች ሲሆኑ 19 አሰልጣኞች በረዳትነት አብረዋቸው ይሰራሉ። 3 ፊዝዮቴራፒስት ያሉት  ቡድኑ በልዩ ክትትል  የሚያግዘው ደግሞ ታዋቂው አትሌት ዴዲድ ሩይሻ እንደሆነ ታውቋል። “ኬንያ አትሌቲክስ” የተባለው ፌዴሬሽን ቡዳፔስት ላይ ከቡድኑ ከፍተኛ ውጤት ይጠብቃል። ዘኔሽን እንደዘገበው የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አትሌቶቻቸው በዓለም ሻምፒዮናው  ከሜዳልያ ውጤቶች ባሻገር በተለያዩ ርቀቶች፣ ሪከርዶች እንደሚያስመዘግቡ ተስፋ አድርገዋል።
በፌዴሬሽኑ  በኩልም ለከፍተኛ ውጤት ዳጎስ ያለ ገንዘብ ሽልማት መዘጋጀቱን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል። የኬንያ መንግስትም አትሌቶች ከፍተኛ ውጤት ሲያስመዘግቡ ልዩ የገንዘብ ሽልማትና ስጦታ በመስጠት ያበረታታቸዋል። በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውስጥ በዚህ ረገድ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል። ከውድድር በፊት ለአትሌቶች የተለያዩ ማበረታቻውን በተለይ የገንዘብ ሽልማቶች ለመስጠት ቃል መግባት አስፈላጊ ነው ወይ? በማለት ለረ/ኮሚሽነር ሁሴን ሼቦ ጥያቄ አቅርበናል።  “እጅግ ያስፈልጋል። ችግሩ ምንድን ነው ለዓለም ሻምፒዮናውም ለኦሎምፒኩም እስከዛሬ ሲሰጥ የቆየው ሽልማት ስታንዳርድ የለውም። መስፈርት የለውም። ማንንም የሚያነሳሳ ነገር አይደለም። አንድ አመራር ወይ ባለስልጣን እንደፈለገው በስሜት የሚሰጠው ውሳኔ ነው። እንደ ቋሚ ነገር አይደለም። አንዳንዴ መሬት ትሸለማለህ ይቀራል። አንዳንድ ጊዜ ከፍተኛ ገንዘብ ትሸለማለህ ይቀራል። አንዳንዴ ወርቆች ትሸለማለህ ይቀራል። ሃቁን ለመናገር እስከዛሬ ሲደረጉ የነበሩ ሽልማቶች ምንም የማያበረታቱ፣ ቀጣይነት የሌለው ቋሚ ያልሆነ ነው። አትሌቶች ለውጤቶቻቸው፣ ለአገራቸው፣ ለባንዲራቸው ነው የሚሰሩት። ከመንግስት ይሄን አገኛለሁ ብሎ የሚጠብቅ የለም። ማበረታቻ ግን እጅግ አስፈላጊ ነው። ለእግር ኳስ ተጫዋቾች እኮ ይደረጋል። ጎል ላገባ፣ ይሄን ጨዋታ ላሸነፈ እየተባለ አይደል…” ብለዋል።
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ለዓለም ሻምፒዮናው ከ8ሚሊዮን 498ሺ ዶላር በላይ አዘጋጅቷል። የወርቅ ሜዳልያ 70ሺ ዶላር ለብር ሜዳሊያ 35ሺ ዶላር እንዲሁም ለነሐስ ሜዳሊያ 22ሺ ዶላር የሚበረከት ሲሆን ለአራተኛ 16ሺ፣ ለአምስተኛ 11ሺ፣ ለስድስተኛ 7ሺ፣ ለሰባተኛ 6ሺ፣ እንዲሁም ለሰባኛ 5ሺ ዶላር ይሰጣል። የዓለም ሪከርድ ለሚያስመዘግብ ደግሞ 100ሺ ዶላር ቦነስ ይሰጣል።
ዋና አሰልጣኝ ሁሴን ሼቦ (ረ/ኮሚሽነር) በመጨረሻም ለ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ጋር በማያያዝ መልዕክት አስተላልፈዋል።
“ቡዳፔስት ላይ ጥሩ ውጤት እንጠብቃለን። ኦሬጎን ላይ ከተመዘገበው የተሻለ ለማምጣት ወይንም ያን ለማስጠበቅ ነው ያቀድነው። የዓለም ሻምፒዮናና የኦሎምፒክ ድሎች ሁልጊዜ አዲስ  ኣመትን ከዋዜማው ጀምሮ በደስታ እንድንቀበል ያደርጋሉ።
የኢትዮጵያ ህዝብ በመልካም ድጋፋቸው በፀሎታቸው እንዲከተሉን፡፡ የሚመጣውንም ውጤት በጸጋ መቀበል ያስፈልጋል። እንደመንግስት ደግሞ ለአትሌቶች ከውድድር በፊትም ሆነ ከውድድር በኋላ አስፈላጊው ድጋፍ እንዲሰጥና ማበረታቻ እንዲኖር አስገባለሁ።”
በ10ሺ ሜትር በሴቶች ሻምፒዮንነት ለማስጠበቅ፤ በወንዶች ሻምፒዮንነት ለመመለስ
በሴቶች 10ሺ ሜትር ባለፈው ሻምፒዮና ኦሬጎን ላይ ለተሰንበት ያገኘችው የወርቅ ሜዳልያ በሻምፒዮናው ታሪክ ለኢትዮጵያ ስምንተኛው የወርቅ ሜዳልያ ሆኖ ተመዝግቧል። ከለተሰንበት በፊት ጌጤ ዋሚ በ1999፤ ደራርቱ ቱሉ በ2001፤ ብርሃኔ አደሬ በ2003፤ ጥሩነሽ ዲባባ በ2005 በ2007 እና በ2013 እንዲሁም አልማዝ አያና በ2017 እኤአ ላይ የወርቅ ሜዳልያዎች አግኝተዋል፡፡ 7 የብር ሜዳልያዎች ብርሃኔ አደሬ በ2001ና በ2005፤ ወርቅነሽ ኪዳኔ በ2003፤ መሰለች መልካሙ በ2009፤ ገለቴ ቡርቃ በ2015፤ ጥሩነሽ ዲባባ በ2017 እንዲሁም ለተሰንበት ግደይ በ2019 እኤአ ላይ አግኝተዋል። 4 የነሐስ ሜዳልያዎችን ደግሞ ጌጤ ዋሚ በ2001፤ እጅጋየሁ ዲባባ በ2005፤ ውዴ አያሌው በ2009 እና በላይነሽ ኦልጅራ በ2013 እኤአ ላይ ተጎናፅፈዋል፡፡
በዓለም ሻምፒዮናው የወንዶች 10ሺ ሜትር ባለፉት 5 የዓለም ሻምፒዮናዎች የወርቅ ሜዳልያ ክብሩን ወደ ኢትዮጵያ መመለሥ አልተቻለም። በእነኃይሌ፤ ቀነኒሳና ስለሺ ዘመን የነበረው አገርን የሚያስቀድም የቡድን ስራ ያስፈልጋል።  በርቀቱ ከፍተኛ ስኬት ሊመዘገብ የቻለው የወርቅ ሜዳልያ ክብሩን የግል ትንቅንቅ ስላላደረጉት ነው። የአገር ክብርን በማስቀደም በሻምፒዮናው ደማቅ ታሪክ አስመዝግበዋል። በዓለም ሻምፒዮና ታሪክ በ10ሺ ወንዶች ኢትዮጲያ የሰበሰበቻቸው ሜዳልያዎች 9 የወርቅ፤ 6 የብርና 4 የነሐስ ናቸው፡፡ 9 የወርቅ ሜዳልያዎችን የተጎናፀፉት ኃይሌ ገብረስላሴ በ1993 በ1995 በ1997ና በ1999፤ ቀነኒሳ በቀለ በ2003 በ2005 በ2007ና በ2009 እንዲሁም ኢብራሂም ጄይላን በ2011 እኤአ ነበር፡፡ 6 የብር ሜዳሊያዎችን አሰፋ መዝገቡ በ2001፤ ኃይሌ ገብረስላሴ በ2003፤ ስለሺ ስህን በ2005ና በ2007፤ ኢብራሒም ጄይላን በ2013 እንዲሁም ዮሚፍ ቀጀልቻ በ2015 እኤአ ላይ ወስደዋል። 4 የነሐስ ሜዳልያዎች አሰፋ መዝገቡ በ1999፤ ኃይሌ ገብረስላሴ በ2001፤ ስለሺ ስህን በ2003 እና ኢማና መርጋ በ2011 እኤአ ላይ አግኝተዋል።
በ5ሺ ሜትር ሴቶች የበላይነቱን ለማስቀጠል፤ በወንዶች ታሪክን ለማሻሻል
ኢትዮጵያ ባለፉት 18 ሻምፒዮናዎች  በሴቶች 5ሺ ሜትር  6 የወርቅ፤  2 የብርና 8 የነሐስ ሜዳልያዎች  በመሰብሰብ ከፍተኛ ውጤት አላት።  በ1999 እና በ2001 እኤአ ላይ በተደረጉት ሁለት ተከታታይ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች አየለች ወርቁ ሁለት የነሐስ ሜዳልያዎችን በማግኘት ፈርቀዳጅ ነበረች፡፡ ከዚያም በ2003 እኤአ ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ፤ በ2005 እኤአ ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ፣ መሰረት ደፋር የብር እንዲሁም እጅጋየሁ ዲባባ የነሐስ፤ በ2007 እኤአ መሰረት ደፋር የወርቅ፤ በ2009 እና በ2011 እኤአ መሰረት ደፋር ሁለት የነሐስ ሜዳልያዎች፤ በ2013 እኤአ ላይ  መሰረት ደፋር የወርቅ እንዲሁም አልማዝ አያና የነሐስ ሜዳልያዎች፤ በ2015 እኤአ ደግሞ አልማዝ አያና የወርቅ ሰንበሬ ተፈሪ የብርና ገንዘቤ ዲባባ የነሐስ  የነሐስ ሜዳልያዎችን ማግኘት ችለዋል። በ2017 እኤአ አልማዝ አያና የብር ሜዳሊያ የወሰደች ሲሆን በ2022 እኤአ ላይ ጉዳፍ ፀጋይ የወርቅ እንዲሁም ዳዊት ስዮም የነሐስ ሜዳሊያ ተቀዳጅተዋል።
በወንዶች 5ሺ ሜትር በሻምፒዮናው 3 የወርቅ፤ 6 የብርና 4 የነሐስ ሜዳሊያዎች ለኢትዮጵያ ተመዝግበዋል። የመጀመርያው የሜዳልያ ውጤት የተመዘገበው በ1991 እኤአ ላይ በፊጣ ባይሳ በተገኘው የብር ሜዳልያ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ በ1993 እኤአ ላይ ሃይሌ ገብረስላሴ የብርና ፊጣ ባይሳ የነሐስ፤ በ2001 እኤአ ላይ ሚሊዮን ወልዴ የብር፤ በ2003 እኤአ ላይ ቀነኒሳ በቀለ የነሐስ፤ በ2005 እኤአ ላይ ስለሺ ስህን የብር፤ በ2009 እኤአ ላይ ቀነኒሳ በቀለ የወርቅ እንዲሁም በ2011 እኤአ ላይ ደጀን ገብረመስቀል ፣ በ2013 እኤአ ሐጎስ ገብረሕይወት   የነሐስ እንዲሁም በ2015 እኤአ  ሐጎስ ገብረህይወት የብር ሜዳሊያዎች ወስደዋል፡፡ ሙክታር ኢድሪስ በ2017 እና በ2019 እኤአ ላይ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በመውሰድ ከፍተኛውን ውጤት ሲያመዘግብ ሰለሞን ባረጋ በ2019 የብር ሜዳልያ ወስዷል።

Read 694 times