Saturday, 05 August 2023 11:33

“ጦሳችንን ይዞ ይሂድ...” ይባል ‘ነበር!’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሐምሌ ‘ፉት’ ልትል ነው፣ አይደል! ለቃላት አጠቃቀም ከይቅርታ ጋር ይሄ አስቀያሚ፣ እጅግ አስቀያሚ ዓመትም ሊወጣ ጥቂት ሳምንታት ነው የቀሩት፡፡ ዘወትር ስንል እንደኖርነውና እንደተለመደው ቢሆን በማንኛውም መለኪያ መልካምነት አጠገብ እንኳን ያልደረሰ ዓመት ሊወጣ ጫፍ ሲደርስ “ጦስ ጥምቡሳሳችንን ይዞ ጥርግ ይበል!” እንል ነበር፡፡ መከራችንን ሲያበላን ሲያሰቃየን ለከረመ ዓመት በቀላችን ምላሳችን ላይ ብቻ ነውና! ነገሮች እንደነበሩ ወይም ሊኖሩ በማይገባቸው ቦታ መሆናቸውን የምታውቁት ክፉ ዓመት ሲወጣ በሙሉ ልባችሁ “እሰይ! እንዲህ እፎይ እንበል እንጂ!” ማለት እንደማትችሉ ስታውቁት ነው፡፡ ለምን ቢባል እየቀረበ ያለው ዓመት ከወጪው ዓመት የተሻለ ለመሆኑ አፍን ሞልተው የሚያናግሩ፣ “ቢሆንም፣ ባይሆንም ደግ መመኘት ክፋት የለውም፣” የሚያሰኙ ብዙ ነገሮች ማየት ሲያቅታችሁ የሌለ ጽጌረዳ ማሽተት አስቸጋሪ ነውና፡፡
ስሙኛማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ የምር እኮ አሁን...አለ አይደል...አሮጌው ዓመት ጦሳችንን ይዞ ለመሄዱ እዚህ ግባ የሚያሰኝ እምነት ስለማይኖረን ግፋ ቢል ለአፋችን ካልሆነ በቀር “ጦሳችንን ይዞ ይሂድ...” ማለት መተው ብቻ ሳይሆን የሚናፍቀን ነገር እየሆነ ነው፡፡ ለከርሞ እኮ ምንም ያህል ችግር ቢኖር አሮጌ ዓመት አልፎ አዲሱ ሲቃረብ ሁሉም ዘንድ እንጥፍጣፊም ትሁን ትንሽም ተስፋ ቢጤ አይጠፋም ነበር፡፡ አዲሱ ዓመት ሁሉም ባይሆኑ ብዙዎቹ ችግሮቻችን የሚቀንሱበት ይሆናል የሚል ተስፋ፣ ጥላቻ፣ ተንኮልና ክፋት ከአሮጌው ዓመት ጋር ጓዛቸውን ጠቅልለው ወጥተው በቦታቸው የፍቅር፣ የመተሳሰብና ያለምንም አጋጅ አጥሮች በጋራ የመኖር ዓመት ይሆናል የሚል ተስፋ፤ የተመናመነው መሶባችን ባይሞላ እንኳን ከሆነ ግማሹ፣ ካልሆነ እሩቡ ይሞላል የሚል ተስፋ!  
እናላችሁ...ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን አሮጌው ዓመት ሊወጣ በተቃረበ ቁጥር የጠቆረው ደመና ከመግፈፍ ይልቅ እየከበደ ጦሳችንን ይዞ አንዲሄድ የምንረግመው ዓመት እየናፈቀን ነው፡፡ በሁሉም በኩል የሚታየውና የሚሰማው ሁሉ ተስፋ ከማለምለም ይልቅ ጭርሱን ስጋት የሚጨምር፣ ጭንቀትን የሚያባብስ ነው፡፡ እናማ ለብዙ ዘመናት ህዝባችን ተከታታይ መልካም ዜናዎች፣ የ“እንኳን ደስ አላችሁ!” ብስራቶች የመስማት ዕድሉን ባያገኝም...አለ አይደል... “ደግ አስብ ደግ እንዲገጥምህ፤” በሚል እሳቤ ከዛሬ ነገ ይሻላል የምትል የተስፋ እንጥፍጣፊ አትጠፋም ነበር፡፡
ታዲያላችሁ... ለመድገም ያህል ይህ አስቀያሚ፣ እጅግ አስቀያሚ ዓመት ደፋፍኖና ግሳንግሱን እኛ ትከሻ ላይ ከምሮ  ከሚያልፍ አንድዬ ትንሽ ዘና ብለን ለመሸጋገር ያብቃን ከማለት ውጪ ምንም ማለት አይቻልም፡፡ አይደለም የምንሄድበትን አጥርቶ ለማየት የመጣንበትን ትናንትናና ከትናንት ወዲያን እየረሳን እዛው ድፍርስ ወንዝ ውስጥ መልሰን መላልሰን ስንገባ “ያለ አድልዎና ያለ ልዩነት ሁሉንም ሰው ድፍርሱን ወንዝ የማሻገር ድልድይ የሚባል ነገር አለ፣” የሚል ምድራዊ ማጽናኛና ማበረታቻ ስናጣ አንጋጠን ማየቱ የመጨረሻ ምሽጋችን ነው፡፡ ትናንትን መርሳቱ ያስጨነቀው ምስኪኑ ሀበሻም የአንድዬን በር ማንኳኳቱ ቢጨንቀው ነው፡፡  
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ... አንድዬ!
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ እንዴት ነህ! ተወው፣ ተወው መልሱን ስለማውቀው ተወው፡፡ ያው እንዳልተመቻችሁ ነው የምትነግረኝ፣ አይደል እንዴ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ይሄን ያህል ታዝበኸኛል እንዴ?
አንድዬ፡- ትዝብት አልከው እንዴ ምስኪኑ ሀበሻ? ትዝብት እኮ አይደለም። እንደውም ተመችቶናል ብትለኝ ነበር የሚገርመኝ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እሱማ አንድዬ፣ እሱማ ሁሉም ነገር ላም አለኝ በሰማይ ሆኖብን ግራ ግብት ብሎናል እኮ፡፡
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ መቼ የሰጣችሁኝን ላም ነው በሰማይ አለን የምትሉት!  
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ኸረ አንድዬ! እንደሱ...
አንድዬ፡- ስቀልድ ነው ምስኪኑ ሀበሻ። ይልቅ ሰሞኑን ጠብቄህ ስላልነበር ዛሬ በመምጣትህ ትንሽ ገርሞኛል፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ለምን አንድዬ? ሁልጊዜ እመጣ የለ እንዴ! የዛሬው ለምንድነው የተለየ የሆነብህ!
አንድዬ፡- አይ፣ አንደኛውን አዲስ ዓመታችሁ ሲገባ መጥተህ በዚህ ዓመት ለገጠማችሁ ሁሉ እንደተለመደው እኔ ላይ “ምን አደረግንህ!” “ምን በደልንህ!” እያልክ ባልዋልኩበት ሀጢአተኛ ታደርገኛለህ ብዬ ነበር የጠበኩት፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ኸረ ተው አንድዬ እንደሱ አትበል፣ ኸረ ተው! እንደው ምንስ ቢቸግረን፣ ምንስ መከራው ቢበዛብን ምን ያህል አአምሯችንን ብንስትና ቢለይልን ነው አንተን ሀጢአተኛ የምናደርገው!
አንድዬ፡- እሱን እንኳን ተወው ምስኪኑ ሀበሻ፡፡ እዛ ታች ምድር ላይ የምትሉኝን፣ የምታማርሩኝን፣ “ምን አድርገነው ነው እንዲህ የጨከነብን!” የምትሉኝን ሁሉ አልሰማ መሰለህ፡፡ ልክ እናንተ የፊልም ጽሁፍ የምትሉትን አይነት ጽፌ መከራ ያወረድኩባችሁ ይመስል “እሱ ያመጣውን እሱ ይመልሰው፣” የምትሉትን አልሰማ መሰለህ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ... እንደው ሆድ ሲብሰን የምንናገረውን ስለማናውቅ የምንዘባርቀው አንጂ ከአንጀታችን አንተን ለመውቀስ አይደለም እኮ! አንድዬ...አሁን፣ አሁን እኮ የምንናገረውን ብቻ ሳይሆን ራሳችንን ማወቅ አየተሳነን ነው፡፡
አንድዬ፡- ግን ምስኪኑ ሀበሻ ቅድም አለወትሮህ ፈጥነህ መጣህ ማለቴ ልክ አይደለሁም!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ልክ ነህ አንድዬ...ልክ ነህ፡፡ ምን ላድርግ ብለህ ነው አንድዬ! ጭራሽ ለይቶልኝ ራሴን ከመርሳቴ በፊት ልምጣ ብዬ ነው፡፡
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ... ዛሬ ደግሞ ለየት ያለ ጨዋታ ይዘህ ነው የመጣኸው። እንዴት ሆኖ ነው ራስህን የምትረሳው! አይደለም ራስህን ልትረሳ ይኸው በመጣህ ቁጥር ስንትና ስንት ነገር እያስታወስክ ትነግረኝ የለ እንዴ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ! እሱ ሁሉ እኮ “ነበር” ሆኖ አየቀረ ነው፡፡
አንድዬ፡- እኮ ንገረኛ! ራሴን እረሳለሁ ብለህ ይህን ያህል ያሰጋህ ምንድነው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- በቃ አንድዬ...  ምን ልበለህ...አእምሮዬ ሁሉም ነገር ከአቅሙ በላይ እየሆነበት አይደለም የትናንት ወዲያና የትናንቱን ሊያስታውስ የጠዋቱን ከሰዓት በኋላ እየረሳ ነው፡፡
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ አሁን እንኳን በጣም አጋነንክ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ... ማጋነኔ ሳይሆን እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙው ሕዝብ ላይ ታች ሲንከላወስ ሁሉንም ነገር ደህና እያስመሰለብን ነው እንጂ ውስጣችንን ብታይ እኮ...
አንድዬ፡- ቆይ፣ ቆየኝማ ምስኪኑ ሀበሻ፤ እንደሚመስለኝ አሁን ያለባችሁ ችግር ምናልባት መልኩን ይለዋውጥ እንደሁ እንጂ ለስንትና ስንት ዘመን ተሸክማችሁ ትዞሩት የነበራችሁት ነው፡፡ ለዚህ ነው ምን የተለየ ነገር አለና ነው የምልህ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ! አንተም፣ አንተም እንዲህ ትለናለህ!
አንድዬ፡- አልገባኝም...
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ! ውስጣችንን እያወቅኸው፣ ጓዳ ጎድጓዳችንን እያወቅህ ምን የተለየ ነገር አለና አልከኛ! አንድዬ ምን ያልተለየ ነገር አለ!
አንድዬ፡- እኔም ግራ ስለገባኝ እኮ ነው! ምን መሰለህ ምስኪኑ ሀበሻ፣ በትንሹ እንኳን ከችግር ስትላቀቁ ያየኋችሁ ጊዜ ትዝ ስለማይለኝ ግራ ቢገባኝ ነው፡፡ ምስኪኑ ሀበሻ አትቀየመኝና እናንተ እኮ ችግርን “እኛን ትተህ የሄድክ ባለፍክ ባገደምክበት፣ በደረስክበት ቦታ ሁሉ አይመችህ!” ብላችሁ ረግማችሁት እናንተ ላይ ጥብቅ ብሎ የቀረ ነው የሚመስለው፡፡
አንድዬ፡- አንድዬ...አንድዬ፣ ብቸኛ ተስፋችን አንተ ሆነህ እንዲህ ስትል እንዴት ቅር እንደሚለን...
አንድዬ፡- በቃ ይቅርታ፡፡ ምን ላድርግ ብለህ ነው ምስኪን ሀበሻ፡፡ ምድር ላይ ሁላችሁም እንደልባችሁ እየተናገራችሁ ስለሆነ እኔም ከማን አንሼ ብዬ ነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ!
አንድዬ፡- ይልቅ ስማኝ ምስኪኑ ሀበሻ፣ ለክፉ ለደጉም ቀኑ ሲቃረብ ብቅ ብለህ እንኳን አደረሰህ በለኝና ያኔ እንጨዋወታለን። በል በሰላም ግባ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አሜን አንድዬ፣ አሜን! 
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1288 times