Saturday, 29 July 2023 12:52

ከማህበራዊ ሚዲያ በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የኒጀር ወታደሮች በብሔራዊው ቴሌቪዥን መፈንቅለ መንግሥት!!


        በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ኒጀር ወታደሮች በብሔራዊው ቴሌቪዥን መፈንቅለ መንግሥት አወጁ። ሕገ-መንግሥቱን መበተናቸውን፤ ሁሉም የመንግሥት ተቋማት ለጊዜው ሥራ ማቆማቸውንና የሃገሪቱ ድንበሮች መዘጋታቸውን ይፋ አድርገዋል።
ከረቡዕ ጀምሮ የኒጀር ፕሬዝደንት ሞሐመድ ባዙም በወታደሮች ቁጥጥር ሥር እንዳሉ ተዘግቧል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፤ ዩናይትድ ስቴትስ ለፕሬዚዳንቱ “ድጋፍ እንደምታደርግ” ቃል እንደገቡም ተደምጧል።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ ፕሬዚዳንቱን እንዳገኟቸው ገልጸው ድርጅታቸው ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት ባዙም፣ በምዕራብ አፍሪካ እስላማዊ ተዋጊዎችን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት የምዕራባዊያን አጋር ናቸው።
የኒጀር ጎረቤት የሆኑት ማሊና ቡርኪና ፋሶ በቅርብ ዓመታት በተመሳሳይ በመፈንቅለ መንግሥት ምክንያት ታምሰው እንደነበር አይዘነጋም። በሁለቱም ሃገራት ወደ ሥልጣን የመጡት ወታደራዊ አስተዳደሮች የቀድሞ ቅኝ ገዥ ከሆነችው ፈረንሳይ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አቋርጠዋል።
ልክ እንደ ማሊና ቡርኪና ፋሶ ሁሉ ማሊም በፈረንሳይ ቅኝ ተገዝታ ነበር።
ረቡዕ ዕለት ዘጠኝ የወታደር መለዮ በለበሱ ሰዎች ተከበው በቴሌቪዥን መስኮት መግለጫ የሰጡት ኮሎኔል ሜጀር አማዱ አብድራማኔ፤ “እኛ የመከላከያና የፀጥታ ኃይሎች የምታውቁትን መንግሥት ከሥልጣን አውርደናል” ብለዋል።
የሃገሪቱ ሁሉም ተቋማት ለጊዜው ሥራ እንደሚያቆሙ የገለጹት ኮሎኔሉ፤ ሚኒስትሮች የቀን ተቀን ሥራውን እንደሚመሩ አስታውቀዋል፡፡
 “ሁሉም የውጭ አገራት ጣልቃ እንዳይገቡ እንጠይቃለን። ሁኔታዎች እስኪረጋጉ በምድርም ሆነ በአየር ድንበራችንን ዘግተናል” ብለዋል።
አክለውም፤ ላልተወሰነ ጊዜ ከምሽት 4 ሰዓት እስከ ንጋት 11 የሚቆይ ሰዓት እላፊ መታወጁን  አሳውቀዋል።
ወታደሮቹ በቴሌቪዥን ቀርበው ይህን ካሉ በኋላ፤ ብሊንከን ፕሬዚዳንት ባዙም እንዲለቀቁ ጥሪ አቅርበዋል። ኒው ዚላንድ ሳሉ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ሚኒስትሩ፤ “ይህ በግላጭ ሥልጣንን በኃይል ለመያዝና ሕገ-መንግሥቱን ለመናድ የሚደረግ ጥረት ነው” ብለዋል።
የምዕራብ አፍሪካ የምጣኔ-ሃብት ጥምረት የሆነው ኤኮዋስ በኒጀር የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ያወገዘ ሲሆን፤ የኤኮዋስ ተዋካይ የሆኑት የቤኒኑ ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ታሎን ለሽምግልና ወደ ዋና ከተማዋ ኒያሜይ አቅንተዋል።
ረቡዕ ዕለት በዋና ከተማዋ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰልፈኞች ለፕሬዚዳንት ባዙም ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ አደባባይ ወጥተዋል። የቢቢሲ ዘጋቢ እንደተመለከተው ደግሞ የፕሬዚዳንቱ ታማኝ የሆኑ ወታደሮች ብሔራዊውን ቴሌቪዥን ታጥቀው ሲጠብቁ ነበር።
ምንም እንኳ መፈንቅለ መንግሥት ያሰቡ ወታደሮች ሰልፈኞችን ለመበተን ተኩስ ቢከፍቱም፣ ከተማዋ ከሞላ ጎደል ሰላማዊ ነበረች።
ኒጀር ከማሊና ከናይጄሪያ በሚነሱ እስላማዊ ጂሃዲስቶች ከ2015 ጀምሮ ተወጥራ ቆይታለች። ከአል-ቃይዳና ከኢስላሚክስ ስቴት ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች ኒጀር ውስጥ ሠፍረዋል።
የፈረንሳይና የሌሎች ምዕራባዊያን መንግሥት አጋር የሆኑት ፕሬዚዳንት ባዙም በምርጫ ወደ ሥልጣን የመጡት በ2021 ነው።
(ቢቢሲ)



Read 1544 times