Monday, 24 July 2023 00:00

ለስልጣንና ለተቃውሞ “ሕዝብ ያሰከራቸው” ዛሬ የት ናቸው?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(3 votes)

      - አንቺም´ኮ አብዝተሽው ነበር!
        - አንተም´ኮ ስልጣን አናትህ ላይ ወጥቶብህ ነበር!
        

          ቅዳሜ ሄደን እንያቸው… ማለቴ ሄደን እንጠይቃቸው ….
በወሬ መሃል የመጣ ድንገተኛ የሃሳብ ብልጭታ ይመስላል። ለጓደኞቹ ግን አዲስ አይደለም። ሲጠብቁት የነበረ ነው። ከሰሞኑ ምን ዓይነት ቪዲዮዎችን ሲያሳያቸው እንደሰነበተ ታዝበዋል። “ለምን ቅዳሜ አንሄድም?”… የሚል “ድንገተኛ” ሃሳብ እንደሚያመጣ ያውቃሉ።
“ትንሽ ምግብ ካዘጋጀን፣ መኪና ነዳጅ አስሞልተን”… ይላቸዋል።
የጉዞ እቅዱን አቅልሎ ይግራቸዋል። የእሱ ድርሻ የጉዞ ሃሳብና አቅድ ማምጣት ነው። ጓደኞቹ፣ መኪና ከነነዳጁ ያዘጋጃሉ። ምግብ ያስቋጥራሉ። ባይስማሙም ግን ዘዴ ፈጥሮ ብቻውን ይሄዳል። ድሬዳዋ ሻሸመኔ የሄደው ብቻውን ነው። ለመዝናናት አይደለም። የድሮ  ዝነኛ ሰዎችንና የድሮ ባለስልጣናትን  ለማየት ነው ጉዞው። ማለት… እስረኞችን ለመጠየቅ ነው። እንዴት እምቢ ይላሉ?
የእስር ቤት ጉብኝት እንደሚመጣ ጠብቀዋል። አላሳፈራቸውም።
በየዕለቱ፣ እልፍ አዳዲስ ፎቶዎችን በፍጥነት እያንሸራተተ፣ ትኩስ ቪዲዮዎችን እየተረተረ ያያል። ግን፣ ከየት ከየት ጎልጉሎ እንደሚያወጣቸው እንጃ፣ ሦስት ዓመት የቆዩ የጥንት ፅሁፎችና ቪዲዮዎችንም ያመጣል። የድሮ የጥንት፣… አምስት ዓመት የሞላቸው ቪዲዮዎች አይቀሩትም። ፈልፍሎ አስሶ ያያል። የቅርስ ቁፋሮ ተመራማሪ ይሉታል ጓደኞቹ።
“ይዋት ይህችን፣… አታስታውሷትም? ሕዝብ ያሳዝነኛል። የትናንት ታሪኩን ይረሳል” ብሎ ያስረዳቸዋል።
“የዛሬን አያድርገውና ካቻምና አገር ምድሩን ያንቀጠቀጠች ጀግና ነበረች።  ንግግሯ ከሚስማርና ከመዶሻ ይበልጣል። ትገርመኛለች። ድፍረቷ… አደንቃታለሁ። የጊዜና የሕዝብ ነገር ሆኖ መረሳቷ… ይህን ልብ በሉ። ትልቅ ትምህርት ነው” ይላቸዋል። “ያነበብኩት ነው” ብሎ ይጨምርላቸዋል። አዋቂ ለመባል አይደለም የሚናገረው። ታሪክን ይመረምራል። ቪዲዮዎችን አስሶ ያያል።
“መጀመሪያ ይህን እዩት… ጠብቁት፤ ጠብቁት፤ ቀጥሎ ምን እንደሚል ስሙት… ወኔው፣ ስሜቱ አይገርምም? ውስጡኮ እየተንጨረጨረ ነው። በጣም ሲናደድ ንግግር ይመጣለታል። ሲፈልግ አለንጋና ጅራፍ የሆኑ ቃላት ያወርድባቸዋል። ሲፈልግ እንደ ላባ የለሰለሱ አበባ የመሰሉ ቃላት እያጠጣ አዘናግቶ፣ ጉድ ይሰራቸዋል። በዙሪያው የከበቡት ተቀናቃኞች ብዛታቸውን ተመልከቱ። አስር ሀያ ቢሆኑ ለሁሉም እንደ ቁጥራቸው ብዙ ምላስ የያዘ ይመስላል”።
“በአንድ ዓረፍተ ነገር፣ አንዱ ላይ አላግጦ፣ ሌላኛውን ሰድቦ፣ ሦስተኛውን ወንጅሎ፣ አራተኛውን አሞኝቶ፣ አንዱን እንደ ውሸታም፣ ሌላኛውን እንደ መሃይም ቆጥሮ፣ ደጋፊዎችን አነሳስቶ፣ ሌሎቹን አበሳጭቶ…. በአንድ ጊዜ ሁሉንም ያዳርሳል። ዘጠኝ ሆነው ቢመጡበት በአንድ ጊዜ ሁሉንም ደህና አድርጎ ይገርፋቸዋል። አይደንቅም? እኔ እንኳ አይገባኝም ነበር፤ አንብቤ ነው” ይላቸዋል።
 ቪዲዮዎችን ያሳያቸዋል። የሁለት የሦስት ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ ቪዲዮዎችን ቆፍሮ ያወጣል።
“ይህችን እዩዋት፣… አነጋገሯን ስሟት፣… ስቱዲዮዋ፣ ወንበርዋ ጠረጴዛዋን ሁሉ ታስረሳሃለች። ወደ ቤቷ የጋበዘችህ፣ ወደ ሳሎን ቤት ያስገባችህ፣ ሶፋ ላይ ነጭ ድመት እያሻሸች የምታጫውትህ ታስመስላለች።… ያነበብኩት ነው የምነግራችሁ። እይዋት። ዘመድ ጎረቤታችን ትመስላለች አይደለም? ቆዩ፣ ትንሽ ታገሱ… የነጭ ድመት ለስላሳ ፀጉር እየደባበሰች የፍቅር ወሬ የምታጫውተን ትመስላለች… እያዋት ስትለወጥ፣…
ራሷ ከአስፈሪ ድመት የባሰች አስፈሪ ነብር ትሆናለች። ሰማችኋት የምትናገረውን? ድፍረቷ፣ ወኔዋ፣… ከሷ አፍ ውስጥ አትግባ! ዓይንህን ቦጫጭቀው የሚያጠፋ ስለታም ጥፍሮች የነብር ሹል ጥርሶች ይሻሉሃል- የሷ ቃላት ከሚያርፉብህ”።
“በዚህ ቪዲዮ ላይ ደግሞ እያዋት”… እያከታተለ ያሳያቸዋል።
አዲስ ቪዲዮ አይደለም። ድሮ የሚያውቋቸው ፊቶች ሳይሆኑ እንደማይቀሩ ትንሽ ትንሽ ትዝ ይላቸዋል።
የጥንት ነው ይሉታል በቅሬታ። ደስ ይለዋል።
የሉሲ ዘመን ቆፋሪ የቅሪተ አፅም ተመራማሪ ነህ ይሉታል። ኩራት ይሰማዋል።
ያው ድሮ ጥንት ማለት፣ ሦስት ዓመት አራት ዓመት ማለት ነው። ከአምስት ዓመት በፊት ደግሞ፣ እንደ ቅድመ ታሪክ እጅግ ሩቅ ዘመን ነው። የሙዚዬም ጉብኝት ይሉታል ጓደኞቹ።
“ይህን እዩት፣ እዚህኛው ስብሰባ ላይ ስሙት… ቤተመንግስት ውስጥ፣… የተቃዋሚ ፓርቲ ሰዎች ከባለስልጣናት ጋር የተጋበዙበት ስብሰባ ላይ ምን እንደተናገረ ስሙት።… ከጀርባ የተቀመጠችውን አያችኋት? ተነስታ ምን እንደምትል እዩልኝ…ዛሬ ማንም አያስታውሳቸውም” ይላል በቁጭት።
“እዩት፣ እይዋት” እያለ የቁፋሮ ምርምሩን ሲያስጎበኛቸው ከሰነበተ፣ ቀጥሎ ምን እንደሚመጣ ያውቃሉ።
ቅዳሜ ሄደን እንያቸው… ማለት ቅዳሜ ሄደን እንጠይቃቸው ብሎ ለጉዞ ያዘጋጃቸዋል።
ጥንት ድሮ ዝነኛ የነበሩ፣… ማለትም ከሁለት ዓመት በፊት እጅግ ዝነኛ የነበሩ ፖለቲከኞች፣… ታዋቂ ባለስልጣናት ወይም ተቀናቃኞች፣ ሹመኞች ወይም ሽፍቶች… ዝነኛ የኢንተርኔት አስጨፋሪዎችና አስለቃሾች፣… ዛሬ ግን ቦታ የተለዋወጡ፣… እስር ቤት ገብተው የተረሱ ሰዎች ላይ ነው የምርምሩ ትኩረት።
ዓመት ሁለት ዓመት ያለፋቸው፣ በዘመናት ርዝመት የተረሱ የጥንት ቪዲዮዎችንና ጽሑፎችን በቁፋሮ ሲመረምር ይሰነብታል። “አቤት ወኔ… ሕዝቡን እንዴት እንዳንጫጫው? አቤት ድፍረቷ!” እያለ ሁለት ሦስት ቀን ራሱንና ጓደኞቹን ለማስደነቅ ይሟሟታል። በዚህ መሃል ነው “ድንገተኛ” የሚመስል ሃሳብ የሚመጣለት።
ወህኒ ቤት ሄደው እስረኞቹን ለመጠየቅ ነው ሃሳቡ። ድንገተኛ ቢመስልም አይደለም። ዝዋይ ሄዶ እስረኞችን አይቷል።
በአካል አያውቃቸውም፤ አያውቁትም።
ግን ለሱ እንደ “ሆቢ” ነው።
እስረኞቹም፣ ጠያቂ ሰው ማየት ይናፍቃቸዋል። አይፈረድባቸውም። ከወር ከሁለት ወር በኋላ ጠያቂ ሰው ይቀንስባቸዋል። ተረሳሁ የሚል ስሜት ይጫጫናቸዋል። የማያውቁት ሰው እስር ቤት ድረስ መጥቶ በስም አስጠርቶ፣ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፤… ሊጠይቃቸውም ይሁን ሊያያቸው ቢመጣ ደስታቸው ነው።
አንዳንድ የድሮ አድናቂዎች አሉ። ያኔ እያደፋሩ እያደነቁ ሲገፋፉ እንዳልነበር፣ አሁን… “ግን ኮ አንተም አብዝተኸው ነበር” የሚል አስተያየት ይሰጣሉ። እስረኛ ሊጠይቁ ሄደው እንዲህ አይነት ወሬ ምንድነው?
አቤት ወኔዋ! እያለ ሲያጋግል የነበረ አድናቂ፣ “አንቺም ግን አብዝተሽው ነበር፤ ቢቀርብሽ ይሻል ነበር” ብሎ ለመናገር ይቸኩላል- ስራዬ ብሎ እስር ቤት ሄዶ።
ስንት ሺህ ተመልካችና ተከታታይ እንደነበራት እየዘረዘረ፣ የአድናቂዋና የአይዞሽ ባይዋ ብዛት ስንትና ስንት እንደነበር ያስታውሳታል። በቁጭት ያወራላታል።
“ይወቴን እሰጣለሁ፣ አለንልሽ፣ ከጎንሽ ነን ሲል ነበረው ሕዝብ ዛሬ የታለ? ምን ዋጠው?” ብሎ ግራ ቀኝ ያያል። ሊጠይቅሽ የመጣ ሕዝብ የለም ለማለት ነው ግራ ቀኝ መመልከቱ።
“እግረ መንገድ ለሰላምታ የመጣ ሰው የለም። በሄድሽበት ሁሉ አድናቆታቸውን ለመግለጽ ሲሽቀዳደሙ የነበሩ ሰዎች፣ “ፈርሚልን” ለማለት ሲሻሙ የነበሩ ሰዎች ዛሬ የሉም። መልክሽን የሚያውቅ ሰውም ጠፋ? አየ ሕዝብ” ብሎ ይገረምባታል።
ምን ዋጠው? የት ሄደ? ብትይኝ ልንገርሽ። ብሎ ከሷ በላይ አዝኖ ይተርክላታል።
“ሕዝብ ማለት ታሪክ ይሰራል። ግን ታሪኩን ይረሳል” ብሎ ያብራራላታል። ያነበብኩትን ነው የምነግርሽ ይላታል። ሕዝብ ወረት ይወዳል። ወረተኛ ሕዝብ… እናንተን አደፋፍሮ ገፋፍቶ ጉድ ካደረጋችሁ በኋላ፣ ወደ አዳዲስ ዝነኞች ተንጋግቶ ይሄዳል። እነሱንም በጥድፊያ አሟሙቆ አርገብግቦ ወደ እሳት በአጀብ ይገፋፋቸዋል።
ይማግዳቸዋል።
ወር ሳይሞላው ይረሳቸዋል።
በየወሩ አዳዲሶችን ያስነሳል።
ይህን የሚያወራላቸው ለእስረኞቹ ነው። ነገር ግን የታሪክ ቆፋሪ እንጂ የታሪክ ተንታኝ የመሆን ፍላጎት የለውም። ያነበብኩትን ነው የምነግራችሁ ይላቸዋል።
“ሦስት ዓመት ወደኋላ ተመልሶ አንቺን የሚያስታውስ ማግኘት የማይታሰብ ነው። እኔም ታሪክ መቆፈር ስለምወድ እንጂ፣… የተረሱ ሰዎችን ማስታወስ ከባድ ነው።  ከአምስት ዓመት በላይ ወደኋላ ተመልሼ የጥንቱን መመርመር ለኔም ከባድ ሆኗል” ይላታል።
“ትዝ ይልሻል? ያኔ ድሮ ዋና አጨብጫቢ አስጨፋሪ የነበሩት፣… አንቺምኮ ለትንሽ ጊዜ… ለማንኛውም ዛሬ ሌላ ሆነዋል።  የእሮሮ፣ የውግዘትና የእርግማን ፊታውራሪ ሆነዋል።… የዛሬ ሦስት ዓመት ባለስልጣን የነበረው ታስታውሺዋለሽ?… እዚህ እስረኛ እንደሆነ… ታውቂያለሽ?  ትዝ አይልሽም። የጥንት ታሪክ ነዋ። እሱንም ለማየት ነው አመጣጤ። ማለቴ ለመጠየቅ”።
“ያኔ ስልጣን ሹመት ሲጨመርለት፣ የአጨብጫቢው የአሽቃባጩ ብዛት ለቁጥር ያስቸግር ነበር። የሕዝብ ሽንገላና ፍቅር አናቱ ላይ ወጣበት። አገር የጠበበው ባለስልጣን ዛሬ ማንም የማይጠይቀው እስረኛ ሲሆን… አየ ሕዝብ… ያነበብኩትን ነው የምነግርሽ”።
“የመንግስት ዋና ሰዳቢና ረጋሚ የነበረው… ካንቺ ጋር ይፎካከር የነበረው ጀግና፣… አንቺ እዚህ ተረስተሻል፣ እሱ ዋና የመንግስት ወዳጅ ዋና ተጋባዥ ቤተኛ ሆኗል። ሰውን ማመን ምኑን ይዘሽ?”
“የኛ ድምፅ ነህ፣ የልብ ትርታችን ነህ” እያለ ሲያደንቀው የነበረ ህዝብ በአንዴ ተገልብጦ፣ “አንተ ሰይጣን ፊት!” ብሎ አዲስ ስም ያወጣለታል፤ አዲስ ፊት ይለጥፍለታል።
“ይሄ መሰሪ” ብለው ሲሰድቡት የነበሩ ደግሞ፣ ወደ ግራ ተገልብጠው፣ በባለ ቀለም መነፅር ተንቆጥቁጦ እንዲታይ ያቆነጃጁታል። መሪያችን ብለው ያነግሱታል። ሕዝብን ማመን፣ ነፋስን መዝገን ነው። ያነበብኩት ነው”።…
ተቃዋሚ የነበረችውን እስረኛና የዛሬ 3 ዓመት የታሰረውን ባለስልጣን ሁለቱንም በየተራ አይቶ… ሁለቱንም በቅዳሜ ዕለት ጠይቆ፣…ሕዝብ የረሳቸውን አስታውሶ፣ ምግብ ውሃ የቻለውን ያህል አምጥቶ፣… ብር ያስፈልጋቸው እንደሆነ የአቅሙን ያህል ሰጥቶ ይሰናበታቸዋል።
አንቺም አብዝተሽው ነበር፤ አንተም አገር ጠበበኝ ማለት አልነበረብህም የሚሉ ሃተታዎችን ብቻ ሳይሆን፤ የሕዝብ ወረተኛነትንም ነግሯቸዋል። ሕዝብ ረስቷችኋል ብሏቸዋል። ለምን ይነግራቸዋል? ሊያሰቃያቸው?
ሕዝብስ እሺ ረስቶ በሰላም ትቷቸዋል።
አስታዋሻችሁ ነኝ ብሎ ሕመም የሚሰጣቸው ምን በደሉት?
በእርግጥ “ያነበብኩትን ነው የምነግራሁ” ይላቸዋል። ለሱ ዋናው ቁምነገር፣ የተረሱ ዝነኞችን የወደቁ ገናኖችን ማየት ነው። እንደ ሆቢ ነው። የቅርስ ቁፋሮ ተመራማሪ፣ የሙዚዬም አስጎብኚ እንደመሆን ነው።
በምህረትና በይቅርታ እየፈታን፣ እስር ቤቶችን ሙዝዬም እናደርጋቸዋለን ብለን ያወራነው መቼ ነበር? የጥንቱን መርምሮ ቪዲዮዎችን አስሶ ካላሳየን እንዴት እናስታውሰዋለን? ቆይቷል!



Read 1702 times