Saturday, 22 July 2023 11:27

የቀድሞ ተዋጊዎችን የመበተኑ ስራ ከአንድ ወር በኋላ ይጀመራልለስልጣንና

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 - በመጀመሪያው ዙር 75ሺ የቀድሞ ተዋጊዎችን የመበተኑና ከማህበረሰቡ ጋር የሚቀላቀል ስራ ከ150 ሚ.ዶላር በላይ ያስፈልገዋል ተብሏል

   - በመጀመሪያው ዙር ከሚበተኑት ተዋጊዎች መካከል 50ሺ ያህሉ የሚገኙት በትግራይ ክልል ውስጥ ነው
               
        ትጥቃቸውን የሚፈቱ የቀድሞ ተዋጊዎችንና በመበተን ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱ ለማስቻል የተቋቋመው የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን፤ የመጀመሪያ ዙር ተዋጊዎችን የመበተን ስራውን ከአንድ ወር በኋላ እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡ በመጪው መስከረም ወር ይጀመራል በተባለው የመጀመሪያው ዙር የብተና ስራ 75ሺ የሚሆኑ የቀድሞ ተዋጊዎች እንደሚካተቱ ተገልጿል፡፡
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽንን የሚመሩት የቀድሞው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ከትናንት በስቲያ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ ቀደም ሲል በተሃድሶ ፕሮግራሙ እንዲያልፉ ዕቅድ ተይዞላቸው የነበሩት 250ሺ የቀድሞ ተዋጊዎች ቢሆኑም፣ በአሁኑ ወቅት ይህ ቁጥር ወደ 371ሺ 971 ማሻቀቡን ጠቁመዋል፡፡ ትጥቅ የማስፈታቱን ስራ መከላከያ ሰራዊት እንደሚያከናውንም ተናግረዋል፡፡
ከተቋቋሙ ሳምንት ወራትን ያስቆጠረው የብሔራዊ፣ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ እንደሚናገሩት፤ እስከ አሁን በስምንት ክልሎች፡- ትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ቢኒሻንጉል ጉምዝ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች ውስጥ 371 ሺ 971 የቀድሞ ተዋጊዎች የተለዩ ሲሆን፤ መቀሌ ውስጥ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ተቋቁሞ በተሃድሶ ፕሮግራሙ ማለፍ የሚገባቸውን የቀድሞ ተዋጊዎች የመለየቱ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
ከመጪው መስከረም ወር እስከ ህዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ይከወናል በተባለው መጀመሪያው ዙር፣ የቀድሞ ተዋጊዎችን የመበተኑ ስራ 75ሺ የሚሆኑ ታጣቂዎች የሚካተቱ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 50ሺ የሚሆኑት በትግራይ ክልል ውስጥ እንደሚገኙም ተጠቁሟል፡፡ ቀደም ሲል በተሃድሶ ፕሮግራሙ ተሳታፊ ይሆናል ተብሎ ለተያዙት 250ሺ የቀድሞ ተዋጊዎች የታቀደው 555 ሚሊዮን ዶላር የነበረ ቢሆንም ይህ በጀት በተሃድሶ ፕሮግራም የሚታቀፉ የቀድሞ ተዋጊዎች ቁጥር በማሻቀቡ ምክንያት በቂ እንደማይሆን አምባሳደር ተሾመ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ለፕሮግራሙ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠንን ግን ከመጥቀስ ተቆጥበዋል፡፡
ይህ ተዋጊዎችን የመበተኑና ወደ ማህበረሰቡ የማቀላቀል ተግባር፣ የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው ከመንግስት ጎን ሆነው የተሰለፉትን የማያካትት መሆኑንና በመንግስት ላይ መሳሪያ አንስተው የተዋጉትን ብቻ የሚመለከት እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
ለፕሮግራሙ አስፈላጊ ነው የተባለው ባጀት በአብዛኛው ከውጪ ለጋሾችዎች ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም በዚሁ ወቅት ተገልጿል፡፡

Read 1942 times