Saturday, 15 July 2023 20:51

ዓመፀኛ ትምህርት፣ አኩራፊ ዘመን ላይ ነን።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(3 votes)

የዓመፀኛ ትምህርት ተሸካሚ አኩራፊ ትውልድ፣ ቤቱን ያፈርሳል- የውጭዎቹ የቅብጠት ነው። የአገራችን አፍራሾች ደግሞ ወገኞች።
ነባር ባሕልና ሥርዓት፣ አንዳንዴ እንደ ተፈጥሮ ዘላለማዊ ይመስለናል። “ምንም ቢያደርጉት አይፈርስም” እንላለን። በመቆርቆር ስሜት እንፅናናለን። “ምንም ብንረግመው አይነቃነቅም” ብለን በጥላቻ ስሜት እንበሳጭበታለን።
እንደ ትናንቱ ዛሬና ወደፊት የሚቀጥል ይመስለናል። በአክብሮት ይሁን በምሬት፣ ስሜታችን ሊለያይ ይችላል። እንደ መተማመኛ ስለምንቆጥረው ይሁን እንደ እጣፈንታ ስለተሸከምነው፣ እንደ ተፈጥሮ ፀጋ ወይም እንደ እርግማን ስለምናስበው ይሁን... ለአገርና ለባሕል የሚኖረን ሃሳብ በተለያዩ ስሜቶች የታጀበ ነው።
አገርና ባሕል፣ “ቋሚ፣ ዘላለማዊና የማይለወጡ ናቸው እንላለን - ለማሞገስ ወይም ለማውገዝ።
በሌላ ጊዜ ደግሞ ነባር ባሕልና ሥርዓት፣ “እለታዊ የምርጫ ጉዳይ” ሊሆኑ ይችላሉ ብለን እንመኛለን፤ አንዳንዴ እንሰጋለን። እንደ ልብስ የምንቀይራቸው፣ እንደ ጨርቅ ባሰኘን ፋሽን በወረት የምሰፋቸው ይመስለናል።
በስጋት ወይም በተስፋ ስሜት እየተነዳን የተሳሳተ ሃሳብ ይዘን እንጋልባለን። በአንድ ጀንበር የሚፈርስ በማግስቱ ሌላ የሚታነፅ ሆኖ ይታየናል። አንዳንዶቻችን በፍርሃትና በሽንፈት ስሜት ነው። ሌሎቻችን በድፍረትና በአሸናፊነት ስሜት።
እንደፈራነው ነባሩ አገርና ባሕል በአንድ እለት ወይም በሳልስት ባይፈርስስ ግን በእፎይታ ያፅናናል? መች አፀናነውና! ቀስ በቀስ እየተሸረሸረ ነው የሚፈርሰው።
 እንደተመኘነው ነባሩን ለማፍረስ ቢሳካልንስ በድል አድራጊነት ልንጨፍር ነው? ምን ተነኘና! ነባሩን ማጥፋት አዲስ ነገር ማግኘት አይደለም። ማፍረስ ችለናል ማለት በምትኩ ሌላ ተገንብቶልን ያድራል ማለት አይደለም።
ነባር ሥርዓትና ባህል፣… በተፈጥሮሯቸው፣ ማለትም በመሰረታዊ ባህርያቸው፣ እንደ ነባር ጥበብ ናቸው። ተጨማሪ አዲስ እውቀት ከመጣብን ወይም ከመጣልን፣ ነባር እምነቶችንና ሃሳቦችን ያፈርስብናል፣ ወይም ያፈርስልናል ብለን እንሰጋለን ወይም እንመኛለን።
ነባር ባሕል  በተቃና መንገድ እየፀና እየበለፀገ ነው እዚህ የደረሰው፤ ወደፊት የሚቀጥለው። የእለት ተእለት መረጃዎችን  እየተመገበ፣ በአዲስ እውቀት እየተገነባ በጥበበኞች ትጋት መሰረቱ እየሰፋ ነው ወደላቀ ከፍታ ማደግ የሚችለው።
አንዳንዴ ደግሞ፣ በአላዋቂነት፣ በየዋህነት ወይም በክፋ መንፈስ፣ ነባሩን የሚያፈርስ ካልሆነ በቀር ምንም አዲስ ነገር ቢመጣ እንደ ቁምነገር አንቆጥረውም። አዲስ እውቀትና አዲስ ጥበብ፣ የተሻለ ለውጥና ስኬት ቢያመጣ እንኳ፣ የድሮውን ካልደረማመሰ በቀር ትርጉም አይሰጠንም። እንዲያውም፣ እድገት ማለት ነባሩን ማፍረስ እንጂ፣ ነባሩን ማሻሻልና የተሻለ ነገር መጨመር ነው ብለን አናስብም።
እድገት ማለት “ነባሩን መሻር” እንደሆነ የሚያምኑ ፈላስፎች፣ “ለውጥ” እውነተኛውና ብቸኛው የተፈጥሮ ህግ ነው ይላሉ። “የማይለወጥ የተፈጥሮ ሕግ፣ የለውጥ ሕግ ብቻ ነው” ይሉ የለ።
በዚህ ስሌትም፣ የፍልስፍና  ዋና አላማ፣ ነባር ሃሳቦችንና መርሆችን የመሞገት አላማ መሆን አለበት ይላሉ። ነባር እውቀቶች እርስ በርስ እንደሚቃረኑ በማሳየት ፉርሽ ማድረግ የፍልስፍና ስራ እንደሆነ ይገልፃሉ።
የሂስ ፍቅር፣ የሙግት ሱስ እንበለው - skepticism and critical theory እንዲሉ።
ስህተትን የማስተካከል ወይም የተሻለ አስተሳሰብ የማሳወቅ አይደለም አላማው። ነባሩን መሻር ብቻ እንጂ!
ፖለቲካ ማለት ደግሞ ነባሩን የመታገልና የማጋለጥ፣ የመጣልና የመገልበጥ ነውጠኛ የለውጥ ንቅናቄ ነው ይላሉ - Anti-establishment Activism, Revolutionary movement እንዲሉ። ለምን አላማ? ነባሩን ለመጣልና ለመለወጥ ነዋ። በምን ለመለወጥ?
አንዱን ነቅሎ ሌላ ለመትከል አይደለም።
የተተከለና ቆሞ ያደረ ነገር ሁሉ እንደ ጠላት ይቆጥሩታል።
ስለዚህ ፓለቲካ ማለት ሁሌም ነባሩን የሚታገል የማያቋርጥ የለውጥ አብዮት መሆን አለበት ይላሉ። ይሄ ሃሳባቸው የዘላለም ቋሚ  ሃሳብ ይመስላል? “ነባር” አስተሳሰብ ሆኖ እንዲቀጥል እየነገሩን አይደሉም?
በሁሉም ነገር ላይ ሞጋችና አፍራሽ፣ ገዝጋዥና ስርነቃ የለውጥ አብዮተኛ መሆን አይቻልም። ራስንም ወደ ማፍረስ ያደርሳል። እናም፣ ትርጉም የለሽ የሃሳብ ቅርቃር ውስጥ ተሰንቅረው እንደሚቀሩ መገመት ይቻላል። “ፍልስፍናና ትምህርት እንዲህና እንዲያ መሆን አለበት፣… ፖለቲካና ባህል ደግሞ በዚህና በዚያ መንገድ መሄድ ይኖርበታል” እያሉ ይነግሩናል። እነዚህን ሃሳቦች ማንም እንዲነካባቸው እንዲሞግትባቸውና እንዲለውጥባቸው አይፈልጉም።
ፀረ-ነባር የለውጥ አርበኞች፣… ለምእተዓመታት ለዘላለሙ፣ የነሱ ሃሳብ ቋሚ ሆኖ በነባርነት ተተክሎና ፀንቶ እንዲዘልቅ ይሰብካሉ።
የነባር ባሕል ተቆርቋሪና የነባር ሥርዓት አደራ ጠባቂ ነኝ፣ አክባሪና ተረካቢ ነኝ ብሎ የሚያስብ ሰውስ? አዲስ ነገር አትስሩ፤ የጥንት ልማዶች ሁሉ እፁብ ድንቅ ናቸው የሚል ከሆነ፣ ከራሱ ጋር ይጋጫል። ነባሩንም ባሕል ያረክሳል።… በርካታ ጥበበኛ ሰዎች በዘመናት ቅብብሎሽ የተረከቡትን አክብረውና ጠብቀው እያሻሻሉ፣ በየፊናቸውም የተሻለ ነገር ጨምረው፣ ወደላቀ ከፍታ የሚወስዱ በተራቸው እያስረከቡ  በረዥም ጊዜ የገነቡት ነው - ነባሩ ባሕልና ሥርዓት። ያለ መልካም ለውጥ የመጣ መልካም ባህል የለም።
ትናንት ለዛሬ፣… ዛሬም ለነገ መሰረት ነው የሚባለው ለምን ሆነና? ስንቅ ወይም ሸክም ልንለውም እንችላለን። ሸክሙ ከባድ ይሆናል። ነገር ግን ከሸክሙ የበለጠ ስንቅ ቢኖረው ነው አንድ ስንዝር መራመድ የምንችለው፤ እስከዛሬ ለመድረስ የቻልነው።
ነባር ፀጋዎችን ማክበርና መጠበቅ ያልቻለ ሰው አዲስ መገንባትና ማፅናት አይችልም። አንዲት የጨመረ አንዲት የቀነሰ ወዮለት ብሎ መዝጋት፣ በረዥም ዘመናት በጥበብ እየገነቡና እያነፁ ለኛ ያስረከቡንን የቀድሞ ጀግኖች መዘንጋት ይሆናል።
“ያረጀ፣ ያፈጀ” ብሎ ነባሩን ማጥላላትና የቀድሞ ስርአት ናፋቂዎች እያሉ ማንቋሸሽ ደግሞ፣ ከንቱ እብሪት ነው። “ስር ነቀል ለውጥና አዲስ ፈጠራ ብቻ” እያሉ መፎከር፣ የቆሙበትን ያቆያቸውን መናድ መካድ ይሆናል።
እንኳን በእጃችን በአጠገባችን ያሉ ነባር ፀጋዎች፣ … በሩቅ አገር የተገነቡ፣ ከብዙ ዘመናት በፊት የተፈለሰፉ የጥበብ ሃሳቦችና እውቀቶችም እንደ ፀጋ ልንቆጥራቸው ይገባል።
አማርኛን ብቻ ሳይሆን እንግሊዝኛንም በፀጋ እንጠቀምበታለን።
ብንችልና እንግሊዝኛን ከምድረገፅ ብናጠፋ ምን እናተርፍበታለን? ኢላማ የምናነጣጥርበት ሌላ ቋንቋ ለማግኘትና በጥላቻ ለመብገን ነው? ምን በወጣን! እንግሊሊኛን የዓለም ቋንቋ ለማድረግ የመድከም የመልፋት እዳ የለብንም። እንደ ፀጋ የመጠቀም ዕድል ግን በእጃችን ነው። አማርኛን ደግሞ እንደልባችን።
አዲስ ለመገንባት የተዘጋጀ ሰው፣ ዋና አላማው ነባሩን ማፍረስ አይደለም። የሆኑ የሆኑ ቦታዎች ላይ፣ ብዙ ያገለገሉ ግንባታዎች መፍረስ ቢኖርባቸውም ቢያረጁም እንኳ፣ በጥላቻ ሳይሆን፣ የቀድሞ ሙያተኞችን በማውገዝ ሳይሆን፣… በክብር በምስጋና መንፈስ መሆን አለበት። ቢያንስ ቢያንስ፣ የአቅማቸው ያህል መገንባታቸው በአርአያነት እና በበጎ ገፅታ የሚጠቀስ እንደሆነ ማመን ያስፈልጋል።
የአክሱም ሃውልቶችን ወይም የግብፅ ፒራሚዶችን እንደ ምሳሌ ልናነሳቸው እንችላለን። አዲስ ሐውልት ያቆሙት የቀድሞ ሐውልቶችን በማፍረስ አይደለም።
ከዝነኞቹ ሶስት ፒራሚዶች በፊት ሌሎች አነስተኛ ፒራሚዶች ተሰርተዋል። በአሰራር ጥራት፣ በጠንቃቃ ዲዛይን እና በግንባታ ጥበብ እንዲሁም በግዙፍነት ግን፣ ሶስቱ ፒራሚዶች  ይበልጣሉ። ነገር ግን፣ የቀድሞዎቹን በአርአያነት አክብረው ነው አዲስና የላቀ ቅርስ የገነቡት።
ሀይማኖቶችንም መመልከት ትችላላችሁ። የአይሁድ እምነት ቀደምት የስልጣኔ ማእከላትን ገሸሽ አድርጎ አላለፈም። ለመሰፖታሚያና ለግብፅ ስልጣኔዎች ሰፊ የትረካ ቦታ በመስጠት ነው ወደ ሙሴ የሚደርሰው። ሙሴ ዋና ዋና የሀይማኖት መርሆችንና ስርአቶችን ያዋቀረ ምሶሶ ነው ማለት ይቻላል።
እስከ ሙሴ ድረስ ያለው የበርካታ ሺ አመታት ትረካ ግን፣ በአብዛኛው ከምድረ ባቢሎን፣ ከዚያም ከግብፅ ጋር የተዛመደ ነው። በተወሰነ ደረጃም የእየሩሳሌም አካባቢንና ኢትዮጵያን የሚጠቅስ ነው። እየሩሳሌምን በተመለከተ መልከ ጼዴቅን፣ ከኢትዮጵያ ጋር የተቀራረበ ደግሞ የሙሴ አማት እና አማካሪ ዮቶርን ማስታወስ ይቻላል።
የክርስትና እንዲሁም የእስልምና ሃይማኖቶችም በተራቸው፣ ለነባር የአይሁድ መጻሕፍትና ትረካዎች ክብር በመስጠት ነው የተስፋፉት።

Read 1152 times