Saturday, 15 July 2023 20:46

ጌታው ወንድዬ ዓሊ - በገባን ልክ!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   ‹‹ . . .ወንድዬ ዓሊን በአማርኛ የሥነ ግጥም ባህል ውስጥ ልዩ ያደርጉታል ብዬ ከማምንባቸው ገጽታዎች አንዱ ምስሎቹን የሚጠልቅባቸው ባህሮች አያሌነት ነው። ከጸጋዬ ገብረ መድኅን፣ ከሰሎሞን ዴሬሳና ከዮሐንስ አድማሱ በስተቀር በሌሎች ገጣሚዎቻችን እምብዛም የማይታየውን ዛሬን ከነገ፣ እንዲሁም ዱሮና ዘንድሮን የማተረጓጎም ጥበብ የወንድዬ ሥራዎች ድርና ማግ እየሆኑ የሚመጣባቸው ሥራዎች እጅግ በርካታ ናቸው።--”



         በሥነ-ግጥም ስም እንጀምራለን።
በወሎ ክ/ሐገር በወረኢሉ አዉራጃ፣ ከየወል ተራራ ግርጌ ከከተመች ካቤ ከምትባል ከተማ የተወለደ፣ ራሱ ግጥምን የሆነ ሰው...!! ገጣሚ፣ አርታኢ፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ፀሐፊና ተመራማሪ፣ አዘጋጅ፣ ግለ-ታሪክ ፀሐፊ፣ የመዝሙር ግጥም ደራሲ ....
አብዛኛዉ የእድሜውን ክፍል በሚወደዉ ስራ ውስጥ የኖረ የሥነ-ፅሁፍ ወዛደር...!! ጋሽ ወንድዬን ሳዉቀዉ በሩቅ ነበር። በዝና... ‘በሆነዉ ልክ ማን አወጋለት!’ የሚል መብሰክሰክ ከነበረበት አንድ ገጣሚ ወዳጄ አንደበት...
መጀመሪያ ያነበብኳት ግጥሙም “ውጋት” የምትለዉን ነበር።
“ጣቶቼ:- ጥቅሻ ላይ፣
ሕሊናዬም:- የወግ ብካይ፤
ብራናውም:- ገና ለዛዛ፣
ቀለሙም:- ገና ፈዛዛ፣
መሆኑን ነግሬሽ ምነው!?
ውቃቢሽ የማይለመነው።”
[ወፌ ቆመች ገፅ 14 ]
በለመናትና በተለመነችዉ ዉቃቢ በኩል እንደ ቅዋ በሻትኩት በኩል ዘየረኝ። “እብዷን አብዶ”
ተብሎ በተደረሰበት ጎዳና ... ላይ ቆሜ ሳየዉ ወንድዬ ለራሱ ኖሮ አያዉቅም። በሰው ላይ ያያትን ትንሽ ተስፋ ለማብቀል ራሱን ሲሰጥ የኖረ ሰው መስሎ ታየኝ። መንገዱ ለገጠመለት ሁሉ እጅ ይዞ አድራሽ አይነት...
ያለ ቦታዉ ለተገኘ ደግሞ “ያንተን ነገር ማረቅ አዛባ እንደ መዛቅ ከባድ  ነዉ።” ብሎ ይሸኛል እንጂ ሰውን ያለ መንገዱ ጣት ጠቁሞ እንኳን አያሳይም።
[ወንድዬን በዚህ በኩል አየሁት። ... ወይም ታየልኝ።]
ማንም ባየው ልክ የሚለዉ አያጣም ብዬ ... በእድሜ ታላላቆቼ ከሆኑት ሥነ-ግጥሞች ውስጥ በመንፈሳቸዉ የገራልኝን ለማለት ስነሳ የራሱ ስንኞች አደፋፈሩኝ።
“ማን ይሰማኝ ብዬ!?
ማን አይሰማኝ ብዬ?!”
[ውበት እና ሕይወት _ ገፅ 68 ]
***
የመጀመሪያ የሥነ-ግጥም መድበሉ የሆነችዉ ‘ወፌ ቆመች’፣ በ1984 ዓ.ም በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ታትማ እስከ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና ኮተቤ የመምህራን ኮሌጅ Modern poetry Curriculum ውስጥ ገብታ ለማስተማሪያነት እያገለገለች እንኳን ... እሱ ወረቀቱንና ራሱን አጥብቆ እንደያዘ ነበር።
አጥብቆ የያዛትም ነገር ‘ውበትና ሕይወት’ ሆና በ1998 ዓ.ም ተገለጠች።
(የወፌ ቆመች ቅፅ ፪...)
ወንድዬ ሊፅፍ ሲቀመጥ ዋርካዉን ይፈልጋታል። የፀጥታዉን...፣ የእርጋታዉን...! ሰማይ የተከፈተለት ዕለት መደዴዉ የረገበለት ዕለት ... ኹለንታዉ የእሱ የብቻዉ ሲመስለዉ እንዲህ ይሆንበታል።
“... በጥድፊያ ውሎዬ አክንባሎ ከድኜባቸዉ ያለፍኳቸዉ ዥንጉርጉር ትዝብቶች ... ደግሞ ሆን ብለዉ የሚከተሉኝና የሚጎትቱኝ እንደዚያ ባለዉ ወቅት ነዉ።-- ታዲያም ይህ ኹነት በመጣ - በሄደ ቁጥር በእርቃናቸዉ ያገኘኋቸዉን ትዝብቶች ለመሸፈን እኔዉ - ከ’ኔዉ ጉባኤ እቀመጣለሁ። እናም:- መለሎ ይሁን ጎልዳፋ፣ የቀና ይሁን ቆልማማ ወይም ሸካራ ቢሆን ለስላሳ ... ግን ሌጣ ሬትና ማር የሕይወት ገፅታዎችን ፈርቅጬ፣ ዳምጬ፣ ነድፌና አመልምዬ በፈተልኳቸዉና በሸመንኳቸዉ ማጎናፀፊያዎች ጥበባዊ ልቀት ላላብስ ሁለንታዬን አሰጣለሁ...።”
[ውበትና ሕይወት __ መግቢያ]
እንዲህ ነዉ ወንድዬ። ራሱን የሰጠላት ሥነ-ግጥም መልሳ ራሷን የሰጠችዉ። ወከክ ብላ የታየችለት ...።
ባሳየዉ በኩል ያዩትም እንዲህ ይሉታል፤ “የወንድዬ የገጣሚነት ምናብ ፤ እንደ ቅዱስ ያሬድ ማኅሌት ሥፍራና ጊዜን ከሚያጥፍ ኪናዊ ዘለዓለማዊ ሁለንተናዊነት ይወለዳል። በሌላ አባባል ፣ ገጣሚዉ ስለ ግጥምና ኪነት ሲዘምር፣ በቅኔ ሠረገላ ሰማያትን እያሰሰ፣ ከሰማያት ጉዞ ልምዱ ምስስልና ሕብር እያረቀቀ በመቅረፅ ነዉ።  [መድብለ ጉባኤ፤ ዘመናዊ የአማርኛ ሥነ-ግጥም]
ረዳት ፕሮፌሰር ብርሀኑ ገበየሁ ስለ ወንድዬ ሲገልፁ ...
‹‹...ወንድዬ ዓሊን በአማርኛ የሥነ ግጥም ባህል ውስጥ ልዩ ያደርጉታል ብዬ ከማምንባቸው ገጽታዎች አንዱ ምስሎቹን የሚጠልቅባቸው ባህሮች አያሌነት ነው። ከጸጋዬ ገብረ መድኅን፣ ከሰሎሞን ዴሬሳና ከዮሐንስ አድማሱ በስተቀር በሌሎች ገጣሚዎቻችን እምብዛም የማይታየውን ዛሬን ከነገ፣ እንዲሁም ዱሮና ዘንድሮን የማተረጓጎም ጥበብ የወንድዬ ሥራዎች ድርና ማግ እየሆኑ የሚመጣባቸው ሥራዎች እጅግ በርካታ ናቸው። ወንድዬ ለምናቡ ጥልቀት፣ ለግጥሙ ትርጓሜ ሁለንተናዊነት የሚያስገኘው ከቅዱሳን መጻህፍት በሚዘርፋቸው ዘመንና ቦታ የሚሻገሩ ምስሎችና ሰብእናዎች፣ እንዲሁም ከአደገበት ቃላት የባህል አውድማ ነው። የገጣሚውን ታላቅነት ለማድነቅ የሚያስገድደን አንድ እውነት የምንጮቹ ብዛት ሳይሆን፣ ከነባርና ዘመን አይሽሬ ውድማዎች የሚስባቸውን ሃሳቦችና ስሜቶች በተራቀቀ የትርጓሜ ስልት ለዘመኑ ሕይወትና እውነት ማሳያነት መገልገሉ፣ በሌላ አባባልም አዲስ ሚት(myth)፣ አዲስ እውነት ለማርቀቅና ለማበጀት መቻሉ ይመስለኛል።...››
ከሁሉም ስለ ወንድዬ ገጣሚነትና ስለ ግጥሞቹ አበክረን እናወጋለን።
ሥነ-ግጥምን የሚያዉቅ ያዉቃታል። ግጥምንም የሚያዉቅ ወንድዬን ያዉቀዋል። እሱ የሥነ-ግጥም አድባር ነዉ። በስራዎቹ ልክ ግን ራሱን ያልገለጠዉ ... ለምን ይሆን? የሚለዉ ጥያቄ ሁልጊዜ የምብከነከንበት ጉዳይ ነበር። እና አንድ ቀን ጠየኩት። “ለምን ግን የአደባባዩን ጉዳይ አልከጀልከዉም?”
“ጊዜ አልነበረኝም። በወቅቱ የነበረዉ የፖለቲካ ሁኔታ ... የሚገትት ነበር። እኔ ደግሞ እሱን አልፈለኩትም። በምንም አይነት ሁኔታ ተሸጉጬ ፍርፋሪ መብላት አልፈልግም። ተጠየፍኩት።”
መልሱ ይሄ ነበር። ይህችኑ ሐሳብ “ውበት እና ሕይወት” ላይ ባለች አንድ ሥነ -ግጥም ብንደግፋትስ ...!!
“ለማላውቃት
ከሕይወት ጥሪ ልስማማ
 ተጨምቄ ተበጥሬ ፤
በነፍሴ ተወራርጄ
የኑሮን ጥሻ መንጥሬ . . .
...
በትናንትና ሠረገላ
 ዘላለማት አምባ ወጥቼ ፣
ከፀሐይ ዙፋን .. ወዲያ .. ማዶ!
ነፍሴን ለንባብ አስጥቼ . . .   (አከራረሙ እነዚህን ስንኞች ይመስላል።... )
[ውበት እና ሕይወት __ ገፅ 3]
***
ግጥም ሥጋ የሚነሳዉ ገጣሚዉ ራሱ በማያዉቀዉ መነካት ውስጥ ሲገባ ፤ በማይረዳዉ ሐይል ሲገፋ፤ ከፍ ባለ አብርሆት ውስጥ ሲገኝ ... ወንድዬም እንደሚላት፤ “ቦግ እልሚቱ” ስትበራ ስትጠፋ ...
“መልካም አፈሳሰስ ... ወድቆ ‘ማይሰበር
ፈሶ ‘ማይደፋ ... ጮሆ ‘ማያሸብር ፤ ...” [ወፌ ቆመች ... ገፅ 1 __ ‘በስንኝ ሲሰክሩ ]
ሐሳብና ስሜትን ...ከጊዜ ስሌት ለማሳለፍ “ትንፋሽን በዋንጫ” እንደ መስፈር ያለን ኹነት ከላይ ከሰደርናቸዉ ስንኞች ተከትሎ ... ወንድዬ በስንኝ መስከርን እንዲህ ይገልፀዋል።
“... በዋርካ ጥላ ሥር፣
ተቀዛቅዞ ባ’የር፤
በዋርካው ጥላ ሥር ... ግራ ቀኝ አማትሮ፣
ውበትን በርብሮ ... ውበትን ቀምሮ፤
...
ከጎን ወደ ግድም ... አግድሙን ተልጎ፣
ከአናት ወደ ግርጌ ... ሸርተቴ ተንዶ፤
...
ከዚያ ጎን - እዚያ ጎን ... ድረሱን መሰበቅ
ውስጠ-ውጭ ፍልቀቃ ከሩሕ መተናነቅ፤
እንዲህ ነዉ ምስጢሩ፣
በስንኝ ሲሰክሩ።
[ወፌ ቆመች ... ገፅ 1 __ በስንኝ ሲሰክሩ]
ሥነ-ግጥም በመነካት ስካር ፣ በመከሰት ደስታ ዉስጥ እና ባለመከሰት ትግል (ማጥ) ዉስጥ የሚያቆይበትን የገጣሚዉንና የሁለንታን ትንቅንቅ “ከምኑ ምንጭ ዉበት ልቅዳ” [ወፌ ቆመች - ገፅ 128]  የሚያሰኝበትን መሆን፤ ከላይ ካነሳነዉ የስንኝ መስከር ኹናቴ ጋር ነገሩ ግዘፍ ሳይነሳ ሲቀር “ባላ ‘ደራም ነዉ ባለ እዳ!?” [ገፅ 128] ብሎ የግጥም ባላደራነቱን አሻግሮ የሚከሰትለትን ባለ እዳነት መሸሽ በሚመስል መንገድ የሰደረበት “ቀጠሮ” የምትል ርዕስ የሰጣትን ግጥሙ ዉስጥ ራሱንና ‘ቦግ እልሚት’ የሚላትን ይታዘባል።
“ቀጠሮ
ሰርፆብኝ አንዳች ኹነት ፣
ሕሊናዬ ውጥረት አዝሎ ፣
ይነዝረኛል - እናጣለሁ፤
አልወርድልህ ብሎኝ ቀለም ከብዕሬ ተንከባሎ።
ወደ ልቤ የሚፈሰው
መሆን-አለመሆን ግለቱ፣
ይጨምቀኛል፣
የሕይወት ነፀብራቅ ግዝፈቱ።...
....
ወዲያዉ ቃላት ተዥጎድጉደዉ፣
ብሂል ሆነዉ፣ ብዕሬን አልፈዉ፣
ጠብ ይሉ ብለህ?...
በምን ዕድሌ!
እንዲህ ቢሆን ሁሌ፣
እንዲህ ቢሆን ሁሌ።”
[ወፌ ቆመች - ገፅ 127]
ይህችን ቀጠሮ የምትል ሥነ-ግጥም፣ መስከረም 1978 ዓ.ም ይፃፋት እንጂ ... በገጣሚና በግጥም መካከልም ፤ (በእርሱና በፅሁፉም መሀል) ... መከሰትና አለመከሰት ፣ በፈለጉት ልክ መገለጥና አለመገለጥ ፤ ... ከራሚ ነገር መሆኑን ከ10 አመታት በኋላ የካቲት 1988 ዓ.ም በተፃፈችዉ ሁለተኛ የሥነ-ግጥም መድበሉ ጥራዝ ላይ በሰፈረችዉ “ምጤ የማይገባት” በምትል ግጥሙ ዉስጥ አበክሮ ይፈክራታል።
“ምጤ የማይገባት
..
የዚያ ቀን ብዕሬ፣
ቃላት ምንሽሬ፤
ወለምታ ተመ’ቶ፣
እርሳሱ ተደፍቶ፤
ቀለህ ብቻ ቀለህ - ቀለህ የቀረኝ ‘ለት
ለመፃፍ ስነሣ
አየር ለድልዶብኝ - ጨረሩ ዘንቦብኝ፣
መሬት አነሰችኝ - ሕይወት አፈነችኝ ...
እንዲያ ስንቆራጠጥ :-
ሀሳቤብ ‘ሚገዛ - ቀልቤን እሚሰርቀዉ፣
ለ’ኔ ሥጋ ነስቶ ላ’ንች የተሰወረዉ፤
ምን ብዬ ልንገርሽ ... ?
እቱ
የ’ኔ ገልቱ
የማምጠዉ ምጤ ... ገና የምወልደዉ
የሚገላገለኝ ... የምገላገለዉ ፤
ነበር።”
[ውበት እና ሕይወት - ገፅ 43]
***
ከ1970ዎቹ አጋማሽ እስከ 1980ዎቹ መጀመሪያ ድረስ ተፅፈዉ ወፌ ቆመች ላይ የሰፈሩት ሥነ-ግጥሞች በአብዛኛዉ በሚባል ደረጃ የራስ በራስ ሙግት (ስለ ራስ ፣ ስለ ማንነት፣ ስለ ሞት፣ ስለ ሕይወት ...) የመሳሰሉትን አይነት የመኖር ግዙፍ ጥያቄዎች የሚያነሱ ... በመጠኑም ቢሆን ሐዘን ያረበበባቸዉ ስንኞች ያሉባቸዉ ይመስላሉ።
[ለምሳሌ ያህል :- የእንባ ስርዓቱ (ገፅ 10) ፣ ሽዉ እልም (ገፅ 25) ፣ ምስክር ፍለጋ (ገፅ 54) ፣ መላ (ገፅ 73) ... አይነቴ ግጥሞችን ልብ ይሏል።]
ራስን ስለማመን ባመኑትም ልክ በራስ ስለመተማመን .. ይህ የጎደለ ዕለት የሰው ልጅ የሚሆነዉን “ሽዉ እልም” ይለዋል ጋሽ ወንድዬ...
“ሽዉ እልም
ሽዉ - እልም ፣ ሽዉ እልም ፣
አሁን ወዲያ ቀና - አሁን ወዲያ ዘመም
ነፋስ ወደ ገፋዉ ...፤
...
በቃ:- ልክ እንደዚሁ ነዉ!
በራስ መተማመን ፣ ለሰው ከጎደለዉ።”
[ወፌ ቆመች -- ገፅ 25]
ደግሞ ስለማጣትም ፣ ስለ መነጠቅም ...
“መላ
የሚወዱትን እንዳጡ ÷ በልቅሶ ቢስረቀረቁ፣
ዐመድ - ነስንሰው
ማቅ - ለብሰው
ደረት ገልጠዉ - ቢደቁ ፣
...
ዋይታ ቢያንጎራጉሩ ፤
ዕድሜ እንደሁ - ትንሳኤ የለው፣
ከአለፈ - ያዉ አለፈ ነዉ።”
[ወፌ ቆመች -- ገፅ 73]
ከመኖር፣ ከሕላዌ ... የሚያረካ ምላሽ አጥተዉ የሚቅበዘበዙበትን ... በሀሳብ ፣ በቃልና በድርጊት ሀሰሳ ውስጥ መቆም አቅም  ያጣበትን ጉዳይ ... ሱባኤ ቢገቡ፣ ጥሬ ቢቆረጥሙ ...ራስን ቢያገሉ አልሆን ያለውን ነገር ወንድዬ አልፎት ምስክር ይፈልግለታል።
“ጭዉ - እብስ እንደ ቀልድ
ከሐሳብ ዉጣ ዉረድ፤
ሲጥ - እልፍ ለአንድ’ዜ
ከሕይወት ድንዛዜ፤
እንደሚሻል - የቱ ?
ባወጋልን ሙቱ።”
[ወፌ ቆመች -- ገፅ 54 __ ምስክር ፍለጋ...]
ጊዜን አልፎ የጠየቀበትን ፣ የተሻገረበትን የምናብ ከፍታ ፣ የሞገተበትን ፣ ያደረገዉን ሁሉ ... የሚያዉቀዉንም የማያዉቀዉንም መልሶ ለጊዜ ጉልበት ያስገዛዋል። (ይሄዉ ነዉ። የሰው ልጅ በመለኮትና በአፈር መካከል መሰቀሉ ... በሆነባት ቅፅበት ባደላበት በኩል መገለጡ...)
“የምናዉቀዉ ትዝታ እንኳን
ከእሳቢያችን ተቃቅሮ - ተገይዶ
ፈቃዳችን - የት የለሌ ÷ ከአድማስ ባዶ፤
ስኬታችን ሲሆንብን እዚህ ማዶ፤...
...
የስኬት የክንዉን አዙሪት ፤
የጊዜ ነውና ዳኝነቱ፣
ፍርዱን ለጊዜ ትቶ
ይሻላል መሰል መርሳቱ።”
[ወፌ ቆመች ገፅ 53 ]
***
እና ... የራስስ ነገር? ‘እኔ’ ብለዉ ባመኑትና ባላመኑት ‘ሌላ’ መካከል ... ብቻ ቀርተዉ...፤ በር ዘግተዉ __ ያለ ገላጋይ የተሟገቱበትን ጊዜ ወንድዬ “ወልይ” ይሆንበታል። ቀድሞ ይተነብየዋል። ወደ ፊት ጊዜን ያሰላዋል። ወደ ኋላም ያስታዉሰዋል። በሁለቱ ኹነቶች መገፋት አሁን ላይ ሲረጋ ግን ... የሆነዉም የሚሆነዉም እያደር ይገለጥለታል።
መገለጡን እንደዚህ ይለዋል። ከራሱ  እስከ ሌላዉ ‘ራሱ’ ድረስ...!!
“የእኔና - እኔ ነገር
እኔና ብቻዬ፣
ትንሿ ታዛዬ፣
ኮከብ ... ታዛቢያችን
ብለን:- ቁጭ አልን።
እኔ እና እኔ - እንደ ቀረን፣
ለብቻችን፣
ወደ ኋላም፣ ወደ ፊትም፣ ... ጊዜን አሰላነዉ
ዘመን:- ክፉም ...ደግም ... አለው
.....
የኔና - እኔ ነገር፣
ሁሌ - በክርክር ፣
እንዳለን :-
አለን።
....
እና:-
እኔና እኔም ... ባዳነታችን
እያደር - ተገለጠልን።”
[ወፌ ቆመች - ገፅ 11 ]
***
ወንድዬ ... የሚያዉቀዉን የሥነ-ፅሁፍ ቆሌና የፀሐፊ ነፃነት ጉዳይ እንደሚያብከነክነዉ “ላታዉቁበት” የምትለዉ ለጋሽ ስብሀት ገ/እግዚአብሄር እንደ ማስታወሻ የሰጣት፣ በ1982 ዓ.ም ሰኔ ወር ባ’ንዱ ቀን ፒያሳ ባለች በአንዷ ካፌ [ማኪያቶዉን እየጠጣ ይመስለኛል።] የከተባት ግልጡን ታሳያለች።
መፈለግም፣ መሻትም፣ መለመንም ያለባት ይች ግጥም፣ ጋሽ ስብሀት በልቡ ያለች መብሰክሰኩን ‘ቦግ እልሚቱ’ ለጋሽ ወንድዬ ሹክ ያለችዉ ይመስላል።
“ላታዉቁበት
... ቅጥሩ አይደል ... ከቅጥራችሁ ፣
ዉልዱ አይደል ... ከዉልዳችሁ ፤
ይጥፋ! - ተውት ... እባካችሁ ፣
ይፍዘዝ - ተውት - ባምላካችሁ።
... እሱ ሌላ! ... ብኩን ኬላ፣
ሥራዉ ሌላ! ... ጉም አዘላ፣...”
***
እንደገናም ለሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ማስታወሻ የፃፋት፣ “አስቸግርህ ባጣ” የምትለዉ ሥነ-ግጥሙ ... ለራሷ ለግጥም ፀሎት የማቅረብ ያህል ጉልበታም ነዉ። ራሷን ግጥምን የመካደም ያህል ይልቃል።
“አስቸግርህ ባጣ
በአዬር ... ደንገላሳ፣
በጨረር ... የሣንሳ፤
በነፋስ ትከሻ ... በገሞራ እስትንፋስ ፣
ልመንጠቅ - አንድ’ዜ! ... ስዉር ጥበብ ላስስ።
ትንሽ ... ልፋሰሰው! ... ዛቴን እዚህ ትቸዉ ፣
በሰማያት ጀርባ ... በማይጎረብጠዉ።”
[ወፌ ቆመች -- ገፅ 28]
በአጠቃላይ ግጥሞቹም በታዩልንና በማየታችን ልክ ... ጋሽ ወንድየም በገባን መጠን ይሄንን ብለናል።
“ደኅና እንሁን!!”



Read 828 times