Saturday, 15 July 2023 20:34

የስኬት ትርጉም - በሁለቱ ሚሊየነሮች ዕይታ!!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ስኬት አመለካከት ነው፡፡ ስኬት ልማድ ነው። እንደሚቀዳጁት ለሚያምኑና መሻታቸውን ወደ ተግባር ለሚለውጡ ሁሉ፣ ስኬት በቀላሉ የሚገኝ ነው፡፡
ስኬት አንዳችም ምስጢር የለውም።  ስኬትን የተቀዳጁቱ አያሌዎች፤ ስኬታማ ከመሆናቸው በፊት ዓመታትን ለስራቸው፣ ከልባቸው ለሚወዱትና ለህልሞቻቸው መሰዋታቸውን በግልፅ  ይተርካሉ፡፡
በሁሉም ሁኔታ፣ ዋናው ጭብጥ ሁሌም ተመሳሳይ ነው፤ እነዚህ ስኬታሞች ሥራቸውን በፍቅር ይወዱታል፡፡ ስለዚህም ዞሮ ዞሮ፣ ይሄን ሥራቸውን መስራታቸው አይቀርም፡፡ ጥሩ አዱኛ… ወይም ቢያንስ የተወሰነ ደረጃ የገንዘብ ደህንነትና ስኬት… ብዙ ጊዜ የህልማቸው አካል ነው፤ ሃብትና ብልጽግና ግን በህይወታቸው የሚወዱትን በመከተላቸው የሚመጣ ተጓዳኝ ውጤት ነው፡፡ ታዋቂው አሜሪካዊ የፊልም ዳይሬክተር ስቲቨን ስፒልበርግ፣ በቀን አንድ ሚሊዮን ዶላር እየተከፈለው፣ ፊልሞችን የሚጠላ ቢሆን ብለህ አስበኸዋል? ኼነሪ ፎርድ በማሽነሪ ባይማረክስ ኖሮ?...ዶና ካራን አልባሳትን ብትጠላስ ኖሮ?...
የምንወደውን ስንሰራ፤ ሌሎች ላይ ጉዳት ሳናደርስ፣ ስጦታችንንና ተሰጥኦዋችንን ስናቀርብ፤ ለራሳችን፣ በዙሪያችን ላሉና ለፕላኔታችን የላቀ አገልግሎት እየሰጠን ነው፡፡
ስኬት የእጣ-ፈንታ ጉዳይ አይደለም፤ ይልቁንም እጅግ የተወሰኑ መርሆች ሥራዬ ብሎ በመተግበር የሚቀዳጁት ነው፡፡ በዚህ ውስጥ እድል ሚና ሊኖረው ይችላል፡፡ ይኼም የሚሆነው፣ ዝግጁነት ከእድል ጋር ሲገጣጠም፣ በሚለው ብሂል መሰረት ብቻ ነው፡፡
እነዚህ መርሆዎች ባሉበት ሁኔታ፣ እድሜ፣ ትምህርት፣ ገንዘብ፣ የኋላ ታሪክና የልጅነት ተሞክሮ ምንም ቦታ የላቸውም - ለስኬት። የዓለማችን ባለፀጎች፣ ስኬታማ አርቲስቶችና ታዋቂ ተዋናዮች የልጅነት ተሞክሮ  እዚህ ግባ የማይባል ነው፤ ብዙ ጊዜ ደግሞ የድህነት፣ አንዳንዴም ጎስቋላ (አሳዛኝ)፡፡ በትምህርት ረገድም በርካታዎቹ ዘገምተኛ ተማሪዎች ነበሩ፡፡
እንዲያም ሆኖ ግን እያንዳንዳቸው፣ በህይወታቸው ወሳኝ ቅፅበት ላይ እድል ፈንታቸውን በገዛ እጃቸው ለማስገባት በመወሰን፣ ራሳቸውን በመፃህፍት በማንቃትና በማበልፀግ፤ የሌሎችን አርአያነት በመከተል፣ እንዲሁም በተፈጥሯዊ እውቀትና ጥበባቸው ተጠቅመው  ስኬትን ገንዘባቸው ያደረጉ  ናቸው፡፡
በኛ “ፈጣን እርካታ- ወዳድ“ ህብረተሰብ ውስጥ ብዙ ጊዜ የመጨረሻ ውጤቱ ላይ ብቻ ነው የምናተኩረው፡፡ ለምሳሌ፤ የፊልም ኮከብ፣ ሚሊዬነር፣ ተደናቂ አርቲስት ወዘተ የሚለው የመጨረሻ ውጤት ላይ ብቻ፡፡ እናም ነገርየው የአንድ ጀምበር (አዳር) ስኬት ይመስላል፡፡ እነዚህ ስኬታሞች ያለፉበትን የዓመታት ልፋት፣ ቁርጠኝነት፣ ትጋት እንዲሁም ታጋሽነት ፈጽሞ አንመለከትም፡፡ አሜሪካዊው የፊልም ተዋናይ ደስቲን ሆፍማን፣ በአንድ ወቅት፣ “የአንድ ጀምበር(አዳር) ስኬታማ ለመሆን 10 ዓመታት ፈጅቶብኛል” ሲል ቀልዷል፡፡ የማክዶናልድ መስራች ሬይ ክሮክ ደግሞ በግለ-ታሪክ መፅሐፉ፤ “እሺ የአንድ ጀምበር (አዳር) ስኬት ነው እንበል፤ ነገር ግን 30 ዓመት ረጅም፣ በጣም ረጅም ሌሊት (አዳር) ነው” በማለት  ፅፏል፡፡
የስኬታማ ሰዎች የጋራ መገለጫ፣ ሁሉም ውድቀቶችን (ሽንፈቶችን) ማስተናገዳቸው ነው፤ አንዳንዴም ብዙ ውድቀቶችን ወይም ሽንፈቶችን! አብዛኞቹ ሰዎች  ስኬት ላይ ፈፅሞ አይደርሱም፤ ምክንያቱም ከአንድ ወይም ሁለት እንቅፋቶች በኋላ ተስፋ ቆርጠው የጀመሩትን ከእነ አካቴው ይተውታል - ከጉዟቸው ይገታሉ።
በአዲሱ ሚሊኒየም ስኬት አዲስ ትርጓሜ ተሰጥቶታል፡፡ የሚሊዮን ዶላሮች ህልምን ለማሳካት ሲሉ፤ ጤናቸውንና የቤተሰብ ህይወታቸውን መስዋዕት በማድረግ፣ በሥራ ሱስ ተጠምደው ለመቀጠል የሚሹ  እጅግ ጥቂት እየሆኑ መጥተዋል፡፡ አሁን ስኬትና ብልፅግና በእርግጠኝነት ሚዛናዊ ህይወትን የሚያካትት ሆኗል፡-በአንድ በኩል አጥጋቢ ሥራን መከወን፤ በሌላ በኩል ጤናንና የአካል ብቃትን እየጠበቁ፣ የፍቅር ግንኙነትና ደስተኛ ቤተሰብ ባለቤት ሆኖ፣ በማህበራዊ እንቅስቃሴዎች እየተሳተፉ እንዲሁም፣ ውስጣዊ ሰላምንና እርካታን እየተቀዳጁ ህይወትን መምራት፡፡
ኒውዮርክ ታይምስ  በሰራው ፖል፣ አብዛኞቹ የጥናቱ ተሳታፊዎች፣ ዋና ጉዳያችን ነው ያሉት፣  በዝግታ መጓዝንና ጥቂት መስራትን ነው፡፡ በተጨማሪም የበለጠ ክብርና ሃብትን ከማሳደድ ይልቅ የበለጠ ጊዜያቸውን ከወዳጆችና ቤተሰብ ጋር ማሳለፍን ትኩረት እንደሚሰጡትም ተናግረዋል፡፡
እውነተኛ ስኬት ይሄን ሁሉ ሊያካትት ይችላል፡፡ በፍቅር የምንወደውን ስራ ለዓለም ማቅረብ፣ በዙሪያችን ላሉ ሁሉ ድንቅ አገልግሎት ነው፡፡
ውብ ግንኙነቶችን መመስረትና እነሱንም ለማጣጣምና ለመጠቀም ጊዜ ማግኘት ሁላችንም ማሳካት የምንችለው ብርቱ ፍላጎት ነው፤ ከወደድን ማለት ነው፡፡ በቅጡ የታሰበበትና የታቀደ የስራ ልማድ፤… በተለይ የአዕምሮ ልማድ… የገንዘብ ደህንነትና ብልፅግና ሊያቀዳጅ ይችላል፡፡ በቂ ሃብት ሲኖረን፤ ከልባችን የምንወደውንና ደስታ የሚያጎናጽፈንን ያለ ጭንቀት ለመሥራት፣ እንዲሁም ለዓለም መልሰን ለመስጠትና ሌሎችንም ለመርዳት ትልቅ ነፃነት እንጎናፀፋለን፡፡
አንድ ጥንታዊ የቻይና ምሳሌያዊ አባባል፣ የአንድ ሺ ኪሎ.ሜትር ጉዞ፣ በአንድ እርምጃ ይጀመራል ይላል፡፡ ይህን መፅሐፍ ለማንበብ በመወሰንህ፣ ወደ ስኬትና ህልም ጉዞህ የሚያደርስህን የመጀመሪያ እርምጃ ወስደሃል። በህይወት ውስጥ ሁሉም ነገር የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ የዚህ መፅሐፍ አላማ፣ አንተ የምር የምትፈልጋቸውን (ህልሞችና ግቦችህን) ማወቅ እንድትችል የቀረቡልህን አማራጮች ግልፅ ማድረግ ብቻ አይደለም፤ እነዚያን ግቦች ታሳካም ዘንድ ማገዝም ጭምር እንጂ፡፡
- ሳምንት ይቀጥላል -
(ምንጭ፡- በሁለቱ ሚሊየነሮች ማርክ ፊሸርና ማርክ አለን አጋርነት ከተፃፈው “How to Think Like a Millionaire”  መፅሐፍ መግቢያ ላይ ስለ ስኬት ከቀረበው ሰፊ ሃተታ የተወሰደ)

Read 1279 times