Saturday, 15 July 2023 20:34

ሱዳን በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አስተያየት “ደንግጫለሁ” አለች

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ሰሞኑን  በአዲስ አበባ በተካሄደው የኢጋድ ሰላም አፈላላጊ የመሪዎች ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ የሰጡት አስተያየት በእጅጉ እንዳስደነገጣቸውና ቅር እንዳሰኛቸው  የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ ። 
የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በሱዳን ላይ ” የአየር በረራ እገዳ” እንዲጣልና ተፋላሚዎች “የከባድ ጦር መሳሪያ ትጥቅ እንዲፈቱ” እንዲደረግ ጥሪ አድርገዋል በማለት አገሪቱ  ጥሪው “ሉዓላዊነቴን የጣሰ ነው”  ብላለች ።
ሰሞኑን  በሱዳን “የአመራር ክፍተት ተፈጥሯል” በሚል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ  የሰጡት አስተያየት  ከዚህ ቀደም ለሱዳን ሉዐላዊ ምክር ቤት ሰብሳቢና ለሀገሪቱ ጦር አዛዥ አብዱልፈታ አልቡርሃን በግል ከነገሯቸው አቋም ጋር የሚቃረን መሆኑን የገለፀው የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር  መግለጫ በዚህም አስተያየት ሱዳን መደናገጧን  ገልጿል ።።
በአዲስ አበባው የሰላም አፈላላጊ የአራት ሀገራት መሪዎች ምክክር ላይ ሱዳን ለመሳተፍ ቃል ገብታ የነበረ ቢሆንም በጉባዔው ላይ ሳትገኝ ቀርታለች። የሰላም አፈላላጊ አባል ሀገራቱ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጅቡቲና ኢትዮጵያ ናቸው።  ሱዳን የኢጋድ የሰላም አፈላላጊ ኮሚቴ ሊቀመንበር የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ “ገለልተኛ አይደሉም” በሚል የኢጋድን ሽምግልና  አሻፈረኝ ስትል ቆይታለች።  ሱዳን በግብፅ በተጠራውና በካይሮ ነገ በሚደረገው ለሱዳን ሰላም የማፈላለግ ጉባዔ ላይ  ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኗንም አስታወቃለች።
የኢጋድ ሀገራት የሱዳንን ሉዐላዊነት ጥያቄ ውስጥ በሚከት አቋማቸው ከቀጠሉ “ሱዳን የኢጋድ አባልነቷን ዳግም ለማጤን ትገደዳለች” ብሏል የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር መግለጫ።


Read 3362 times