Sunday, 09 July 2023 17:22

በፍቅር መንገድ ላይ

Written by  (ከደራሲ ይነገር ጌታቸው “ጠመንጃና ሙዚቃ” የተቀነጨበ)
Rate this item
(0 votes)

 መቼ እንዲህ ያደርጋል ፍቅር ብቻውን
ቢነካኝ ነው እንጂ አስማት  ምናምን
አብዳለች ይሉኛል ከነፈች ይላሉ
እንደኔ በፍቅር ነደው ያልከሰሉ
የፍቅር ምርኮ ናት፡፡ ፍቅር ደጋግሞ ያሰቃያት፡፡ ምናብን የሚያስንቅ ታሪኳም ከዚያው የሚቀዳ ነው፡፡ የጉብዝናዋ ወራት ህይወቷ አለቃ አበበ ይባላል፡፡ ሲያሻት ትዘፍንለታለች፡፡ ደስ ሲላት በእንባ ታጅባ ታንጎራጉርለታለች፡፡ እርሱም ዝም አይላትም፡፡ ስለ ፍቅራቸው ስንኝ ያውሳታል፡፡
“አንተ ስውር ሚስጥር የድብቅ እቃዬ
መቼም አይሰማህ ጭንቀቴ ስቃዬ፡፡” በይ ይላታል፤ ትልለታለች፡፡
የአስናቀች ወርቁ የአፍላነት ዘመን ትውስታ የቱንም ያህል ቢተረክ፣ ፌርማታው አበበ ነው፤ ትዳሩን አስፈትታ ያገባችው አበበ፡፡ ቅዳሜ ለምናው እሁድ ጓዙን ጠቅልሎ ከደጇ የዋለው አበበ፡፡ የአስናቀችን ታሪክ ለሚሰማው ይህ ሰው ገፀባህሪ እንጂ በህይወት ኖሮ ያለፈ አይመስልም፡፡ “ወደድኩት፣ ለመንኩት፣ አገባኝ” ትላለች፡፡ ግን ቅዳሜ አግብታው ቅዳሜ ፈታችው፡፡ የትዳር አጋሩን ፈቶ ከቤቷ የዋለውን ሰው “አስቀየመኝ” ብላ የገዛ ቤቷን ጥላለት ወጣች፡፡ ይሁን እንጂ ከመኖሪያ መንደሯ ነው እንጂ ከአበበ ለመራቅ አልተቻላትም፡፡ እናም የአንድ ቀን ትዳራቸውን አስባ ደብዳቤ ላከችለት፡፡ አበበም የሰው ቤት ይዞ ዝም አላለም፡፡ ከቀናት በኋላ መለሰላት፡፡
አስናቀች የተላከላትን ደብዳቤ ስታነብ መጮህ ጀመረች፡፡ አቤ ብላ ደጋግማ ተጣራች፡፡ ቤተሰቦቿ እብደት ቃጥቷታል ብለው በገመድ አሰሯት፡፡ ፍቅር መሆኑን ተጠራጥረውም ወደ ቤትሽ አሁን አትሄጅም አሏት፡፡ በዚህ አለመግባባት ለ3 ቀና እሱን ካላየሁ አልበላም ብላ ለያዝ ለገናዥ አስቸገረች፡፡ በመጨረሻም ልቀቋት ይለይላት የሚለው ወገን በረከት፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ አስናቀች ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡ አበበ ግን በዚያ አልነበረም፡፡ ግራ ገባት፡፡ ጓደኛዋ ልታማክራት ስትሄድ ከውስጥ ተመለከተችው፡፡ ከአበበ ጋር ዳግም ተወያይተው ፍቅራቸውን አስተካከሉ፡፡
በዚህ ሰሞን ወደ ማዘጋጃ ቲያትር እያቀኑ አፍላ ፍቅራቸውን በሙዚቃና መድረክ ተውኔት አስጌጡ፡፡ ከሷ ጋር ያዩት ሁሉም ለቤተሰብ “ልጃችሁ ከአበበ ጋር ታየች፤ ዳግም ማበዷነው” እያሉ ማሟረት ያዙ፡፡ ያሉት አልቀረም፤ አንድ ምሽት ማዘጋጃ ትያትር አስናቀችና አበበ ሲዝናኑ፣ አበበ የቀድሞ የትዳር አጋሩን በአይኖቹ ሲጠቅስ ተመለከተችው፡፡ የፍቅር ህመሟ ተቀሰቀሰ፤ ቤት እንደደረሱ ካንተ መለየት እፈልጋለሁ አለችው፡፡ ፍቅረኛዋ የሚሰማውን ማመን ተሳነው፡፡ “ጉድ አድርገሽኝማ አትሄጅም” ብሎ ሽጉጡን ከሰገባው ላይ መዘዘ፡፡ አንድ ላንቺ አንድ ለኔ ብሎ ፎከረ፡፡ በቤት ውስጥ ያለውን ዕቃም ሰባበረ፡፡ ያስናቀች የጉብዝና ወራት ፍቅር በጥላቻ እየተተካ ሄደ፡፡
“ከአቤ ፍቅር ምን አተረፍኩ” ብላ እራሷን ጠይቃ
“ስቃይ” ብላ መለሰች፡፡
እናም ያን የልጅነት ፍቅሯን እራቀችው፡፡ እሱም ተስፋ ቆረጠ፡፡ ደግሞ የሌላ ገላ ለመደ፡፡ ከጊዜያት በኋላ የአስናቀች ጎረቤቶች በማለዳ ከቤቷ ተገኝተው፣ ትወደው ታፈቅረው የነበረው አበበ፣ ሰው በመግደሉ በስቅላት ሊቀጣ መሆኑን አረዷት፡፡ እሷ ግን ምንም አልመሰላትም፡፡ እንደማንም ሰው “ምን አድርጎ” ብላ ጠየቀቻቸው፡፡ “ደብረዘይት አንድ የውጭ ሀገር ሰው ገድሎ” አሏት አልደነገጠችም፡፡ ከፍቅሩ ይልቅ ያሰቃያት ትዝ አላት፡፡ ሲሰቀል ለማየት እንሂድ ሲሏት አልሄድም አለች፡፡ አበበ ዳግም ላይመለስ ተሰናበተ፡፡ እሷም በሱ ቦታ ክራርን ተካች፡፡ ጠዋት ማታ እንጉርጉሮ ሆነ፡፡
ከእናቴም ከአባቴም የተጣላሁብህ
የኔ ማህተብ ጠብቋል ያንተ እንዳይላላብህ
ቢመክሩኝ አልሰማ መካሪ ደመኞዬ
የመከራ ውሃ ፈሰሰ በላዬ፡፡
ማለትን አዘወተረች፡፡ የአስናቀች የፍቅር መንገድ መዳረሻውም ሙዚቃ ሆነ፡፡ እኔ አንጎራጓሪ እንጂ ድምፃዊ አይደለሁም ትላለች፡፡ ሰው የሚሰጠኝ ዜማና ግጥምም ለእንጉርጉሮዬ እንጂ ለሙዚቀኝነቴ አይደለም ስትልም ትገልጻለች፡፡ በርግጥም የአስናቀች ወርቁ የዜማ ግጥም ድርሰቶች የግል ትውስታ ትርክቶች ናቸው፡፡ ሃያ አምስት የሚሆኑት በራሷ ክራር የተሰሩ ሙዚቃዎቿም ለዚህ አብነት ይሆናሉ፡፡
አዲስ አበባ ገዳም ሰፈር የተወለደችው አስናቀች ወርቁ፤ የፍቅር ማዕበል ከሙዚቃ ደጃፍ አምጥቶ የጣላት እንጂ፣ መነሻዋ የአብነት ትምህርት ቤት ነው፡፡ በቃል ትምህርት አቀባበሏ ተደናቂ የሆነቸው የያኔዋ ብላቴና፣ በየኔታዋ ተመርጣ ትምህርት ሲጠናቀቅ የመዝጊያ ፀሎት መዝሙር አቅራቢ ነበረች፡፡ በጊዜ ሂደትም በስሙኒ ሳንቲም ክራር ገዝታ ከመንፈሳዊው ዝማሬ ርቃ ስለ ፍቅር ማንጎራጎር ወደደች፡፡ ብርሃኑ ደመቀ ከተባለ የክራር ተጫዋች ጋር እየዋለችም ቅኝት ለማወቅ በቃች፡፡ ፍቅር የሚሉት ምንትስም ከክራር ጋር አጣብቋት እድሜ ዘመኗን በዚያ የዜማ ጅረት ፈሰሰች፡፡
አስናቀች የሙዚቃ ሰው ብቻ ሳትሆን የመድረክም ፈርጥ ነበረች፡፡ “የፍቅር ጮራ” የተሰኘውን ትያትር ለመድረክ ለማብቃት ደፋ ቀና በማለት ላይ የነበሩት ጌታቸው ደባልቄና ጓደኞቼ ለተዋናይነት የከጀሏት ያኔ ነው፡፡ በገዳም ሰፈር ሲያልፉ ተመለከቷት፡፡ ወንዶች የሴትን ገፀ ባህሪ ተላብሰው በሚተውኑበት በዚያን ወቅት፣ በርግጥ እንደዚህ አይነት ቀልጣፋና አይነ ግብ ሴት ለትወና ማግኘት የሚታሰብ አልነበረም፡፡ ግን መጠየቁ ነውርነት የለውም ብለው ቀርበው አወሯት፡፡ አላንገራገረችም፡፡ በ1945 ጥበብን በሞያነት አወቀቻት፡፡ “የፍቅር ጮራ” ትያትርም በሷ ልክ የተሰፋ መሰለ፡፡
ይህ ብቃቷን ያዩ ሰዎች ቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ ትያትር ሲጀምር ለተመልካች በበቃው “ዳዊትና ኦሪዮን” ተውኔት ላይ እንድትሳተፍ ለመጋበዝ አላመነቱም፡፡ እሷም ለመድረክ መፈጠሯን ለማሳየት እንደዛው፡፡ በንጉሱም የዘወድ በአል ላይ ተሳታፊ የነበሩት የውጭ ሀገር እንግዶች፣ የመክፈቻ ትርኢቱን ከተመለከቱ በኋላ አስናቀችን የየት ሀገር ዜጋ ናት እስከማለት ደረሱ፡፡
የፍቅር ማዕበል ከጥበብ ደጃፍ የጣላት ያቺ ወጣት ግን የተመልካችን አፍ በአንድ የመድረክ ስራዋ ብቻ ያስያዘች አልሆነችም፡፡ እናም ዘመናት መጥተው ዘመናት ሲተኩ በሷ የተከፈተውን መድረክ ተራቀቀችበት፡፡ ከ3 ዓመት በኋላ ለማ ገብረህይወትና ማሞ መንግስቴ የቀዳማዊ ሀይለስላሴ ቲያትርን የሀገረ ሰብ የሙዚቃ ቡድን ሲያቋቁሙ አስናቀችም የመድረክ ሙዚቀኝነቷን በይፋ አወጀት፡፡ በ1955 የአፍርካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት ከቀዳማዊ ሃይለስላሴ ኦርኬስትራ ጋር በመሆን “አማረች አዲስ አማረች ለአፍሪካ ህብረተ መሰረት ሆነች” በማለት የድርጅቱን ምስረታ አበሰረች፡፡
አስናቀች ለቲያትር ቤቱ የመጀመሪያ አመታት፣ በኦርኬስትራው በመታጀብ ዜማዎቿን ማቅረብ የቀጠለች ሲሆን፣ “ስራ በእውነት ያሻል” የተባለው ሙዚቃዋ ለዚህ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ተወዳጁዋ የጥበብ ንግስት፣ ከኦርኬስትራ ይቅ የግል ቁዘማዋ ውጤት በሆነው የክራር ስራዋ እራሷን ማጀብ መረጠች፡፡ የትውስታዋን ማህደር እየገለጠች በክራሯ ከትዝታዋ ጋር አብራ ነጎደች፡፡ በህይወት መንገድ ላይ ሰባት አስርት አመታትን ተሻግራ ስምንተኛው ደጃፏ ላይ ግን ክንዷ ዛለ፡፡ በ2004 ትዝታዋን ለቀሪው ነዋሪ አጋብታ ላትመለስ አሸለበች፡፡



Read 655 times