Saturday, 08 July 2023 00:00

ለጠ/ሚኒስትሩ ጠንከር ያሉ ጥያቄዎች የቀረቡበት የምክር ቤት ውሎ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)


      ጠቅላይ ሚ/ሩ ስልጣን እንዲለቁና ምክር ቤቱን እንዲበተን ተጠይቋል ለጠ/ሚኒስትሩ ከስልጣን ይውረዱ ጥያቄ ሲቀርብላቸው የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው ከኦነግ ሸኔ ጋር ተጀምሮ ስለተቋረጠው ድርድር ጥያቄ ቢነሳም ምላሽ አልተሰጠበትም
   
        የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በተገኙበት ባካሄደው 28ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ጠንከር ያሉ ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ከኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ኦነግ ሸኔ) ጋር ተጀምሮ የተቋረጠው ድርድር በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ አልተሰጠም፡፡
ከምክር ቤቱ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረቡላቸው ዋና ዋና ጥያቄዎች መካከል የሚበዙት በሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ናቸው፡፡ በፌደራል መንግስቱ የተጀመረው የክልል ልዩ ሃይሎን መልሶ የማደራጀት እርምጃ ከምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝና በአማራ ክልል የተፈጠሩ ችግሮችን በምን መልኩ ለመፍታት እንደታሰብ ጥያቄ ቀርቧል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር ውስጥ የተፈፀመውን ከመኖሪያ ቤቶችና የእምነት ተቋማት ማፍረስ ጋር የተያያዙ ችግሮችን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄም፤ ጠ/ሚኒስትሩ ጉዳዩ በዋናነት የሚመለከተው የከተማ አስተዳደሩንና የኦሮሚያ ክልልን ነው ብለዋል፡፡ በሒደቱ የተጎዱ ወገኖች ካሉ ግን ሊካሱ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ አባል የሆኑት የምክር ቤቱ አባል ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፣ ለጠቅላይ ሚ/ሩ ጠንከር ያሉ ጥያቄዎችን ካቀረቡ አባላት መካከል ዋንኛው ናቸው፡፡ ዶ/ር ደሳለኝ በጥያቄያቸው አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ገባችበት ያሉትን ሁለንተናዊ ቀውስ በመግለፅ፣ ለዚህም ተጠያቂው የብልፅግና መንግስት ነው ብለዋል፡፡ ብልፅግና መራሹ መንግስትም ሆነ ፓርላማው አገራችን ከገባችበት የፖለቲካ ቅርቃብ ማውጣት የሚችሉ ባለመሆኑ ጠ/ሚሩ ስልጣንዋን ለጊዜያዊ ሲቪል አስተዳደር ያስረክቡ ብለዋል፡፡ አያይዘውም፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በምክር ቤቱ ፍቃድ ምክር ቤቱን እንዲበትኑና ለአዲስ ምርጫ መንገዱን እንዲጠርጉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቀርበዋል፡፡
“ዜጎች በጠራራ ፀሀይ ይታገታሉ፤ በሚሊዮን ብር ይጠየቅባቸዋል፡፡ ሙሉ አማራ ክልል አዲስ የጦርነት ቀጠና ተደርጓል ከፊል ኦሮሚያ ክልልም የጦርነት ቀጠና ሆኖ ሰንብቷል” ያሉት የምክር ቤት አባሉ፤ ትግራይ አማራና አፋር ፋይዳ ባልነበረው የብልፅግናና የህውሃት የስልጣን ጦርነት ምክንያተ  ደቋል፡፡ ቤንሻንጉል ጋምቤላና አብዛኛው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልም ከሌሎች የተለየ አይደለም ብለዋል፡፡
“ለዚህ ሁሉ ቀውስ ተጠያቂው ብልፅግና መራሹ መንግስትና የጠ/ሚሩ የወደቀ አመራር ነው ያሉት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፤ “አገራዊ መፍትሄ አፈላላጊ ጉባኤ እንዲዘጋጅ አድርገው ሳይረፍድ ለአገራዊ ቀውሱ መላ ቢያበጁ አይሻልም ወይ” ሲሉ ጥያቄአቸውን አቅርበዋል፡፡
ከአብኑ አባል ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ጠ/ሚሩ፤ ከለውጡ ወዲህ ፈተናዎች መብዛታቸውን ገልጸው፣ ፈተናዎቹ ግን እያዳከሙን ሳይሆን እንደወርቅ አጠንክረው እያወጡን ነው ብለዋል፡፡ ጦርነቱ እንደተባለው የህውሃትና የብልፅግና ችግር ከነበረ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ የት ነበራችሁ? ለምን አታስታርቁም ነበር፤ አስታራቂ ሲጠፋ ነው ግጭት የሚበዛው ብለዋል፡፡ ስልጣን እንዲለቁና ፓርላማው እንዲበተን የቀረበውን ጥያቄ፣ ለፊስቡክና ዩቲዩብ እንጂ ለትውልድ አይጠቅምም ብለዋል፡፡ “ፖለቲካው ፅንፍ የያዘ ፖለቲካ ነው፤ እኔ ብቻ ነኝ የምመራው፤ እኔ ካልመራሁ ምርጫ ይፍረስ ፓርላማው ይበተን የሚል ጽንፍ የወጣ አስተሳሰብ ነው” ያሉት ጠ/ሚሩ፤ ተቃዋሚዎች ለ3 ዓመታት እንዲታገሱ ጠይቀዋል፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅሙን እንደሚያውቅም ተናግረዋል፡፡
የበዜጎች ግድያና እገታን በተመለከተ ከምክር ቤቱ አባላት የቀረበው ጥያቄም፣ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የመንግስት አመራሮችና የፀጥታ አካላትን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች እንደሚፈፀሙና፤ ንፁሃን ዜጎች በየጊዜው እንደሚገደሉና እንደሚታገቱ በርካቶችም በተለያዩ ጊዜያት ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሆነና ጥቃቶቹም በተቀናጀ መልኩ የሚፈፀም መሆኑን በመግለጽ፤ ዋና ዋና የአገሪቱ መንገዶች የስጋት ቀጠና ስለመሆናቸውና ለዚህ ችግር ስለታሰበው መፍትሄ ጥያቄ ቀርቧል፡፡
ለዚህ ጥያቄ ጠ/ሚር ዐብይ አህመድ በሰጡት ምላሽ ለችግሩ እልባት ለማግኘት መንግስት የህግ ማስከበሩን ዘመቻ እንደሚያስቀጥልና በድርድር የሚፈታ ጉዳይ ካለም በመንግስት በኩል ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ህዝብን እያፈኑና እየገደሉ ህዝብን ነፃ ማውጣት እንደማይቻል የገለጹት ጠ/ሚሩ፤ ከኦሮሞ ነፃት ሰራዊት (ኦነግ ሸኔ) ጋር ተጀምሮ ስለተቋረጠው ድርድር ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ  ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡
 የምክር ቤቱ አባላት ለጠ/ሚሩ ካቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል በሳቸው መሪነት የሚካሄዱትን ፕሮጀክቶች አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጥበትና ፕሮጀክቶቹም ኦዲት እንዲደረጉ ሰኔ 27 ቀን 2015 ዓ.ም በዋለው የምክር ቤት ውሎ ጥያቄ ቀርቦ የነበረ ሲሆን ይኸው ጥያቄ በምክር ቤቱ 28ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይም በድጋሚ ቀርቦ በጠቅላይ ሚ/ሩ ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡ የፕሮጀክቶቹ ጅማሮም ሆነ የገቢ ምንጭ ሰፊ መሆኑን የገለፁት ጠ/ሚሩ፤  ከመፅሃፍ ሽያጭና ከሃብታም ደጋግ ሰዎች ልገሳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 ለምሳሌ ዩኒቲ ፓርክ በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ፕሬዚዳንት ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አማካኝነት በራሳቸው ገንዘብ በራሳቸው ተቋራጭ ኩባንያ መስራቱን የገለፁት ጠ/ሚሩ፤ ገንዘቡን ኦዲት ማድረግ የምትፈልጉ ፕሬዚዳንት ሼክ መሀመድን ጠይቁ ብለዋል፡፡
 የታችኛው ቤተመንግስት እድሳትም በፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት እንዲሁም ፍሬንድሺፕና ሳይንስ ሙዚየም በቻይና ፕሬዚዳንት መሰራታቸውንና ሁለቱም ፕሬሲዳንቶች የራሳቸውን ኩባንያ ቀጥረው እንዳሰሩና ገንዘብ እንዳልተቀበሉ ገልፀዋል፡፡“በተከበረው ምክር ቤት ፊት ለኢትዮጵያ ህዝብ በኩራትና በእምነት የምገልፀው ከዚህ ምስኪን ህዝብ አንድ ብር አንሰርቅም” ብለዋል ጠ/ሚኒስትሩ፡፡ ይህ በምክር ቤቱ አባላት የቀረበው የፕሮጀክቶች ማብራሪያና የኦዲት ጥያቄን በመቃወም የተናገሩት የምክር ቤቱ አባል ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ፤ በፕሮጀክቶቹ አስፈላጊነትና የገንዘብ ምንጭ ላይ ጥያቄ የሚያነሱ አካላት ምን እየፈለጉ እንደሆነ አይገባኝም ብለዋል፡፡ የብዙ አገራት መሪዎች በግላቸው የሚያገኙትን እርዳታና ሽልማት ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው መበልፀጊያ ያደርጋሉ ያሉት ዶ/ር አሸብር፤ ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ግን ለአገርና ለህዝብ ጥቅም እንዲውል በማድረግ ጨዋ ታማኝና ባለአደራ መሆናቸውን አሳይተዋል፤ ይህ ደግሞ ተገቢ የሆነ ዕውቅና እየተሰጠው ነው ብዬ አላምንም ብለዋል፡፡
ምክር ቤቱ በዚህ 28ኛው ጉባኤ ለ2016ዓ.ም የቀረበለትን የ801.65 ቢሊዮን ብር በጀትም አፅድቋል፡፡



Read 2650 times