Monday, 03 July 2023 09:36

የአድዋ መቶኛ ዓመት ዝክረ በዓል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በተቋም ዲሬክተርነቴ ዘመን ብዙ የደከምኩበትና ኋላም ዋጋ ያስከፈለኝ ነገር ቢኖር፣ በ1988 ዓ.ም የተደረገው የአድዋ መቶኛ ዓመት ዝክረ በዓል ነው፡፡ እኔ በዚህ የታሪክ አጋጣሚ የተቋሙ ዲሬክተር መሆኔን እንደ ትልቅ እድል ነበር የቆጠርኩት፡፡ ሙያዬንና የተቋሙን ዝናና እምቅ የመረጃ ሀብት በመጠቀም ይህን የኢትዮጵያን የሃያኛ መቶ ዓመት ዕጣ ፈንታ ከማንኛውም ጉዳይ በበለጠ የወሰነ ክስተት በማይረሳ ሁኔታ ማክበሩን ዐቢይ ተልዕኮዬ አድርሄ ተነሳሁ፡፡ ለዚህም እንዲረዳኝ የተቋሙን የዳበረ ልምድ በመከተል የብሔራዊ ዝግጅት ኮሚቴ አቋቋምኩ፡፡ በኔ ሰብሳቢነት የሚመራው ኮሜቴ አባላት የሚከተሉት ነበሩ፡- ፕሮፌሰር መርዕድ ወልደ አረጋይ፣ ፕሮፌሰር ሺፈራው በቀለ፣ ዶ/ር ካሣዬ በጋሻው ( በወቅቱ በባህል ሚኒስቴር የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዲሬክተር)፣ ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ፣ አቶ አክሊሉ ይልማ (ጸሐፊ)፣ አቶ አቡበከር አብዶሽ (የተቋሙ አስተዳዳሪ)፣ አቶ ደግፌ ገብረ ጻድቅ፣ አቶ ሰሎሞን ወረደ ቃል (ከባህል ሚኒስቴር)፣ አቶ ጸጋዬ አሰፋ (ከዩኒቨርሲቲው ፋይናንስ ክፍል)፣ እና አቶ ይሁን በላይ መንግስቱ፡፡ ኮሚቴው ስራውን የጀመረው ከበዓሉ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ነበር፡፡ ዋና ተግባራት አድርጎ የያዛቸውም ሦስት ነበሩ፡- በአድዋ ድል ላይ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ትልቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤ፣ የአድዋ ጦርነት ከመነሻው እስከ ድምዳሜው ሥዕላዊ በሆነ መንገድ የሚገልጽ ዐውደ ርዕይ እና በአማርኛና በእንግሊዝኛ የተዘጋጀ ዘጋቢ ፊልም (ዶኩሜንታሪ)፡፡
የዝክረ በዓሉ ዝግጀት ሁለት ተፃራሪ የሆኑ ተግዳሮቶች ነበሩበት፡፡ በአንድ በኩል በወቅቱ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ የብሄረሰብ ማንነትን መመሪው አድርጎ የተነሳው መንግስት ይህን የኢትዮጵያዊነት ስሜት የሚቀሰቅስ ዝግጅት የጎሪጥ ማየቱ ነው፡፡ በተለይም ዝግጅቱ የራሴን አቋም ያራምዱልኛል ሊላቸው በማይችላቸው ሰዎች መከናወኑ ሳይጎረብጠው አልቀረም፡፡ ስለሆነም ይመስላል የተቋሙን እንቅስቃሴ ከመደገፍ ይልቅ ብሄራዊ ኮሚቴ ብሎ ሌላ አዘጋጅ አካል ያቋቋመው፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ ድሉ የአንድ ክልል ድል ይመስል በትግራይ ልማት ማህበር ስር አንድ ሌላ ኮሚቴ ደግሞ ተቋቋመ፡፡ ይህም ሆኖ መንግስት ለአዘጋጀው ኮሚቴውም ቢሆን ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ ይህን ያህል የሚያመረቃ አልነበረም፡፡ መጀመሪያ ከተሰጠው የመቶ ሺህ ብር መንቀሳቀሻ ገንዘብ  በላይ ተጨማሪ ስለመሰጠቱ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ታሪክ በምፀት የተመላች ናትና እኔ እስከከማውቀው ድረስ ለዝግጅቱ ከፍተኛውን ገንዘብ ያዋጡት ኢትዮጵያውያን ሳይሆኑ ጣልያኖች ነበሩ፡፡ የአዲስ አበባው ጁቬንቱስ ክበብ አባላት በአንድ ምሽት ባደረጉት የገንዘብ መዋጮ ስድስት መቶ ሺ ብር ማሰባሰባቸውን አውቃለሁ፡፡ ከዚህ ውስጥ ለኛ ኮሚቴ ሳንቲም አልደረሰንም፡፡ ይህም ሆኖ እስከተቻለ ድረስ ከሁለቱ ሌሎች ኮሚቴዎች ጋር በትብብር ለመስራት ሞክረናል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የአድዋ ድል በዓል አዲስ አበባ እንጂ አድዋ (ትግራይ) መከበር የለበትም የሚል ጽንፈኛ አመለካከትም ነበር፡፡ የኛ አቋም በዓሉ አዲስ አበባም አድዋም መከበር አለበት የሚል ነው፡፡ ይህን ዓይነቱን ጽንፈኛ አመለካከት በመቃወምም በጦቢያ ጋዜጣ ላይ ሰፋ ያለ ገለጻ ማድረጌን አስታውሳለሁ፡፡ ገና ለገና በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ከትግራይ የበቀለ ነው በማለትና ከርሱ ጋር ያለን ቅራኔ በመመርኮዝ ታሪካዊዋን አድዋ ወደ ጎን ለማድረግ መሞከር ኢ-ታሪካዊ ነበር፡፡ ከሌሎች አገራት ልምድም እንደምንማረው እንዲህ ያሉ ታሪካዊ ክንዋኔዎች ሲዘከሩ ቦታው ድረስ በመሄድ ነው እንጂ እቦታው አልሄድም ብሎ በማደም አይደለም፡፡ ከዚያ በፊትም የዶጋሊ መቶኛ ዓመት ሲከበር ቦታው ድረስ በመሄድ እንደ ነበር ካስገነዘብኩ በኋላ፣ የአድዋ ድልንም በቦታው ተገኝቶ (እነዚያ ታሪካዊ ተራሮች ስር ሆኖ) ማክበር ምን ያህል የመንፈስ እርካታ እንደሚሰጥ በአጽንዖት ገለጽኩ፡፡
በተጻራሪ ወገን የነበረው አዝማሚያ ደግሞ የምኒልክን ሚና የማኮሰስ ነበር፡፡ ይህንንም የተሳሳተ አተረጓጎም ዝርዝር መረጃ በማቅረብ ማክሸፍ ነበረብኝ፡፡ ያቀረብኳቸው ማስረጃዎችም አንደኛ በኢትዮጵያ ታሪክ መቼም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ህዝቡን እንደ አንድ ሰው ለማስተባበር መቻላቸው፤ ሁለተኛ የውስጥ ችግራቸው እስኪፈታ ድረስ (በተለይም ራስ መንገሻ ዮሐንስ እስኪገቡላቸው ድረስ) በትእግስት መጠበቃቸው፤ ሦስተኛ ከኢጣልያ እንኳ ሳይቀር የጦር መሳሪያ በማሰባሰብ ሰራዊታቸውን ማደርጀታቸው፤ አራተኛ ኢጣልያ ከአጋሯ እንግሊዝ ጋር በማበር በኢትዮጵያ ላይ የጣለችውን ዲፕሎማሲያዊ ከበባ በመበጠስ የሩሲያና ፈረንሳይን አጋርነት ለማግኘት መሞከራቸው እና አምስተኛ ደግሞ የመኳንንታቸውን፣ በተለይም የባለቤታቸውን የእቴጌ ጣይቱን፣ ምክር የመስማት ችሎታቸው ነበሩ፡፡
በጉባኤው መክፈቻ ወቅት ባደረግኩት ንግግር ይህንን አላስፈላጊ የሆነ አታካራና የተጣመመ የታሪክ አተረጓጎም አስመልክቼ የሚሰማኝን ለመናገር ተገድጄ ነበር፡፡ እንዲህ ስል፡-
We are grateful to all the individuals and institutions who had confidence in us and in our program. Our appreciation is particularly enhanced when we note that the commemoration of the Adwa victory has otherwise been attended by considerable ambivalence and confusion in some circles. It remains a curious historical irony that the commemoration of such an event as Adwa, which was notable above all for its demonstration of supreme national consensus and single-mindedness, could be attended by doubt and uncertainty.
Those of us who, in the course of the preparations for the Centenary commemoration, have had the opportunity to re-live, however vicariously,  the experience of our sturdy forefathers, are assailed by no doubts. Nor do we harbor any ambivalent feelings about this great event and its commemoration. For, once we manage to rise above the transient political postures of the moment, Adwa strikes us in its eternal and immutable verity -- the right to live in freedom and the duty of closing ranks when the very survival of the nation is at stake.
ይህንን ዝክረ በዓል ስናዘጋጅ ከተለያዩ ወገኖች ለተደረገልን እርዳታ ምስጋናችን እየገለፅን፣ በሌላ ወገን ግን በዓሉ በአያሌ ብዥታና ጥርጣሬ መታጀቡ በእጅጉ ያሳዝነናል፡፡ የላቀ ብሄራዊ አንድነትና ህብረት ተምሳሌት የሆነው የአድዋ ድል በጥርጣሬና ማወላወል መታጀቡ ትልቅ የታሪክ ምፀት ነው፡፡ ዝክረ በዓሉን ስናዘጋጅ በምናብም ቢሆን የአባቶቻችን ገድል እንደገና ለማየት ለቻልነው ግን እንዲህ አይነቱ ጥርጣሬ ሲያልፍም አይነካንም፡፡ ይህን ታላቅ ድል ለመዘከርም አንዳችም ማመንታት አልተሰማንም፡፡ ምክንያቱም አላፊ ከሆኑት የፖለቲካ አቋሞ ከፍ ብለን ማሰብ ከቻልን የአድዋ ቋሚና ዘመን የማይሽረው እውነታው ወለል ብሎ ይታየናል፡- በነፃነት የመኖር መብትና የአገር ህልውና አደጋ ላይ ሲወድቅ ልዩነትን ወደ ጎን አድርጎ፣ ሆ ብሎ በአንድነት መነሳት፡፡
ስለሆነም አለማቀፍ ጉባኤውን ስናዘጋጅ ይህንን ታሳቢ በማድረግ የመጀመሪያዎቹን ሦስት ቀናት አዲስ አበባ ላይ ካደረግን በኋላ ማሳረጊያውን ቀን ደግሞ አድዋ ለማድረግ ቆረጥን፡፡ ከሁሉም በፊት ግን አንገብጋቢው የገንዘብ ጉዳይ  መፈታት ነበረበት፡፡ ከመንግስት ምንም አይነት ድጎማ እንደማናገኝ ካረጋገጥን በኋላ ገንዘብ ለማሰባሰብ የተለያዩ ስልቶችን ቀየስን፡፡ የመጀመሪያው የአገር ቅርስ ማህደር የሆነውንና በህዝቡ ዘንድ እምብዛም የማይታወቀውን ተቋማችንን ማስተዋወቅና እግረ መንገዳችንንም ገንዘብ ማሰባሰብ ነበር፡፡ ለዚህም “የሻይ ግብዣ” በሚል አንድ ምሽት አዘጋጅተን ታዋቂ ሰዎችን (በተለይም ባለሃብቶችን) በመጋበዝ ስለተቋሙ ሰፋ ያለ ገለፃ ካደረግንና ካስጎበኘናቸው በኋላ ለዝክረ በዓሉ ዝግጅት የእርዳታ ቃልኪዳን ሰነድ (IOU) አስፈረምን፡፡ የመጡት ሰዎች በሙሉ ማለት ይቻላል የተለያየ መጠን የገንዘብ እርዳታ ለማድረግ ቃል ገቡ፤ በቃላቸውም መሠረት ከፈሉ፡፡ ከነዚህ መካከል ከፍተኛውን መጠን (ዐስር ሺህ ብር) የከፈሉት ካፕቴን ግዛቸው ወንድይራድና ሚስተር ፓስኳሌ መሆናቸውን ሳልጠቅስ አላልፍም፡፡
ሌላው የገንዘብ ማሰባሰቢያ መንገድ ደግሞ አዲስ አበባ የሚገኙ ታሪካዊ ስፍራዎችን አድኖ የማግኘት ውድድር (Treasure Hunt) ሲሆን ገንዘቡም የሚሰበሰበው በስፖንሰርሺፕ አማካኝነት ነበር፡፡ ሃሳቡን ያመነጨው ካጠገባችን ያልተለየን ጋዜጠኛና ገጣሚ ሙሃመድ ኢድሪስ ሲሆን ከፍተኛ የሎጂስቲክ እርዳታ ያደረገልን ደግሞ በፕሬዚዳንቱ በሚስተር ግሪጎሪ አማካኝነት የሞተር ብስክሌት ፌዴሬሽን ነበር፡፡  የሙሃመድ ኢድሪስ አስተዋጽኦ በዚህም አላበቃ፡፡ የአፄ ሚኒሊክና የእቴጌ ጣይቱ ድምጽ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀረጸበትን ለእንግሊዟ ንግስት ቪክቶሪያ ያስተላለፉትን የሰላምታ መልእክት ቅጂ በማስመጣትና ከጀርባው ያለውን ኮሽታ ድምጽ በማጥራት የኤግዚቢሽኑ አካል ለማድረግ አብቅቶናል፡፡ ይህ ገንዘብ የማሰባሰብ ጥረት ያልወሰደን ቦታ፣ ያላሳየን ጉድ አልነበረም፡፡
 አንድ የመጣልን ሀሳብ የራት ምሽት በሒልተን ሆቴል በማዘጋጀት አንድ ጥሩ ስእል ለጨረታ አቅርበን ጠቀም ያለ ገንዘብ ማሰባሰብ ነበር፡፡ ለዚህም የመረጥነው በጣም ታዋቂ የሆነውን ኢትዮጵያዊ ሰዓሊ ነበር፡፡
 ስለዚህም ደጅ ለመጥናት አንድ ሦስት ሆነን ወደ ቤቱ አመራን፡፡ ዳቦና ሻይ ከጋበዘንና  ስእሎቹንም እያዞረ ካስጎበኘን በኋላ የመጣንበትን ጉዳይ አስረዳነው፡፡ በነገሩ ጥቂት ካሰበ በኋላ በእንዲህ አይነት ጥያቄዎች ምን ያህል እንደተሰላቸ ገለፀልን፡፡ በተለይም ይህ የአድዋ ዝክረ በዓል ጉዳይ መንግስት በጥርጣሬ አይን የሚያየው በመሆኑ ነገር ውስጥ መግባት እንደማይፈልግ አስረግጦ ነገረን፡፡ ነገሩን የቋጨውም የግል ፍልስፍናውን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ከሽኖ ነው፡-     “When in doubt, don’t “ (“ከተጠራጠርክ አታድርግ”)፡፡ ስለሆነም ዳቦአችንን በልተን፣ የስእል አውደ ርዕዩን አይተን ባዶ እጃችንን ተመለስን፡፡
  እነዚህ እንቅፋቶች ሁሉ በአሉን ከመቼውም በደመቀ ሁኔታ ከማክበር አላገደንም፡፡
ከሁሉም በፊት ማድረግ የፈለግነው 1988 ዓ.ም ሲጠባ የአድዋ ዘመቻን የሚያንጸባርቅ የቀን መቁጠሪያ አሳትመን ማውጣት ነበር፡፡ የፊት ሽፋኑን በኢትዮጵያ ባንዲራ በተከበቡ የአድዋ አርበኞች (ከምኒልክ እስከ ካዎ ጦና፣ ከጣይቱ እስከ አባ ጂፋር) ሲያጌጥ የእያንዳንዱ ወር ገፅ ደግሞ በ1888 ዓ.ም በወሩ የተከሰተ አብይ አድዋ-ነክ ክስተት ስእላዊ መግለጫ ነበረው፡፡
ለምሳሌ በመስከረም የአፄ ምኒልክ የክተት አዋጅ፣ በጥቅምት የውጫሌን ውል የሻረው የአዲስ አበባ ውል፣ በታኃሣሥ የዶጋሊ ጦርነት፣ በጥር የመቀሌ ዕርድ (ምሽግ) ከበባው፣ በየካቲት የአድዋ ጦርነት ወዘተ…፡፡
ሌላ በበአሉ መዳረሻ ያደረግነው ዝግጅት የግጥም ውድድር ነበር፡፡ ለዚህም ብዙ ተወዳዳሪዎች ቀርበው በእኛ ግምት ከሁሉም የላቀ ሆኖ ያገኘነውን ረዘም ያለ የተሻገር ሺፈራው ግጥም በአንደኝነት መርጠን በኋላም ለበአሉ በተዘጋጀው ልዩ መፅሄት ታትሞ ለንባብ በቃ፡፡
ቀደም ሲል እንደተገለፀው፣ ዋናው ዝግጅታችን በሦስት አበይት ጉዳዮች ላይ ያጠነጠነ ነበር፡፡ የመጀመሪያው በአድዋ ጦርነት (መነሾ፣ ሂደቱና ውጤቱ) ዙሪያ አለማቀፍ ጉባኤ ማሰናዳት ነበር፡፡ ለዚህም በመላ ዓለም ለናኘው የኢትዮጵያ ጥናት ማኅበረሰብ፣ ጥሪ  አድርገን አበረታች መልስ አገኘን፡፡ የጥንታዊ ፅሁፎቹን ብዛት (ስድሳ ያህል) በማጤንም፣ ጉባኤው ሰኞ የካቲት 19 ቀን አዲስ አበባ ተጀምሮ ማሳረጊያው የካቲት 22 ቀን አድዋ ላይ እንዲሆን አድርገን መርሃ ግብሩን አዘጋጀን፡፡
የአዲስ አበባው ክፍል ያለ እንከን የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የአድዋው ግን አንዳንድ እክሎች ነበሩበት፡፡ በተለይም ፕ/ር መርዕድ ጽሁፉን በሚያቀርብበት ሰአት በተቀነባበረ መልክ በእሱ ላይ የመዝመት ሁኔታ ይታይ ነበር፡፡
መርዕድ ሁልጊዜ ከትግራዋይነቱ በፊት ኢትዮጵያዊነቱን የሚያስቀድም ስለነበር ለአክራሪ ብሄርተኞች አይጥማቸውም፡፡  እንደ አጋጣሚ ውይይቱን የምመራው እኔ ስለነበርኩ፣ የዘመቻውን መሪ አደብ እንዲገዛ አድርጌ ውይይቱ በሰላም ሊጠናቀቅ ቻለ፡፡
ይህ እንግዲህ በእለቱ ያጋጠመን ሳንካ መቅድም መሆኑ ነበር፡፡ የሻይ እረፍ ሰዓት ሲደርስ በስብሰባ ወግ የትግራዩ ኮሚቴ የደገሰልንን ለማወቅ ተወካያቸውን ሻይ የተዘጋጀልን የት እንደሆነ ስጠይቀው “ከተማው ሁሉ ሻይ ቤት ነው” ብሎ ፈጽሞ ያልጠበኩትን መልስ ሰጠኝና ሻይ ታስቦ ታለፈ፡፡
ሰውየው በአጼው ዘመን የዩኒቨርሲቲው አንጋፋ መምህርና ባለስልጣን እንደመሆኑ መጠን የአካዳሚክ ጉባኤ ስነ ስርዓትን ያጣዋል ብዬ አልገመትኩም ነበር፡፡ በሌላ በኩልም በእንግዳ ተቀባይነታቸው በሚታወቁት በትግራዋያን ምድር ይህን አይነት መልስ ማግኘቴ በጣም ገረመኝ፡፡ ምሳ ሰዓት  ሲደርስም እንዲሁ ምንም የተደረገልን ዝግጅት ስላልነበረ ምሳ ፍለጋ በከተማው ተሰማራን፡፡
ለተንኮሉ ደግሞ በአሉን ለማክበር ከተማይቱ ከተለያዩ የትግራይ ከተሞች በመጡ እንግዶች ተጥለቅልቃ ስለነበር በየደረስንበት ምግብ አልቆ ጠበቀን፡፡
በመጨረሻ በነፍስ የደረሱልን ቅቅል እንቁላል እያዞሩ የሚሸጡ ልጆች ነበር፡፡ የአጋጣሚው ምፀታዊ አንድምታ ወዲያው ነው የመታኝ፡፡
 “ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ፤ ግብሩ እንቁላል ነበር ይኼን ጊዜ አበሻ” እያልን እየዘመርን ነበር ያደግነው፡፡ በእለቱ አድዋ ግን እንቁላል ባይደርስልን ኖሮ በጠኔ አልቀን ነበር!
***
(ከባህሩ ዘውዴ “ኅብር ሕይወቴ ግለ ታሪክ“ መጽሐፍ የተቀነጨበ)

Read 770 times