Saturday, 24 June 2023 20:34

መፍትሄው ከዘረኝነት መውጣት ብቻ ነው!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(8 votes)

 ሥልጣኑም ሃብቱም ለሁላችን ይበቃናል


          የብልፅግና መንግስት ሹማምንቶችና ካድሬዎች በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው  ስለአገሪቱ ልማትና ዕድገት ከልባቸው ቢያወሩንና ቢነግሩን ምንኛ በታደልን ነበር፡፡ (እነሱም ምንኛ በታደሉ ነበር!) የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች (የገዢውም የተቃዋሚውም) የሚሟገቱትና የሚከራከሩት በፖሊሲ፣ በሥራ ፈጠራ፣ በኑሮ ውድነት፣ በድህነት ቀረፋ፣ በኢንቨስትመንት ማስፋፊያ፣ በዲሞክራሲና ሰብአዊ ጉዳዮች…. ላይ ቢሆን ኖሮ ምንኛ በታደልን ነበር፡፡
(ለእነሱም ታላቅ ክብር ነበር!) የባለስልጣኖቻችን ትጋትና ሩጫ የዜጎችን ቤት ማፍረስ ሳይሆን የዜጎችን ቤት መገንባት፤ ማፈናቀል ሳይሆን ማስጠለል ……  ቢሆን ኖሮ ምንኛ በታደልን ነበር፡፡ የወቅቱ ዋነኛ አጀንዳ ከምርም (ፕሮፓጋንዳው ቀርቶ!) ኤክስፖርት ስለሚደረግ የስንዴ ምርት፤(መጀመሪያ እኛ ጠግበን!) ከህዳሴ ግድብ በዶላር ስለምንሸጠው የኤሌክትሪክ ሃይል ቢሆን ኖሮ ምንኛ በታደልን ነበር፡፡ (ኢኮኖሚያችንም በታደለ ነበር!)
የብልፅግና ሹማምንቶችም ሆኑ የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ዘወትር የሚሟገቱት እንዴት ሰላምና አንድነትን እንደሚፈጥሩ፤ እንዴት ኢትዮጵያዊነትን እንደሚያለመልሙ፤ እንዴት በህዝቦች መካከል ፍቅርና ወንድማማችነት እንደሚያሰርፁ ቢሆን ኖሮ ምንኛ በታደልን ነበር፡፡ (እነሱም ውስጣዊ ሰላም ባገኙ ነበር!)
ፉክክራችን እንዴት ራሳችንን አበልፅገን አገራችንን እናበለፅጋለን፤ እንዴት ልማት እናስፋፋለን፤ እንዴት የውጭ ኢንቨስተሮችን በብዛት ወደ አገር እናስገባለን፣ እንዴት ከስንዴ እርዳታ ወጥተን በምግብ ራሳችንን እንችላለን…. በሚለው ላይ ቢሆን ኖሮ ምንኛ በታደልን ነበር፡፡ ሁሉም ከግል ጥቅሙና ከሥልጣን በፊት አገሩን ለማስቀደም ቢተጋ ኖሮ ምንኛ በታደልን ነበር፡፡
በኢትዮጵያ ምድር የተፈጠሩ ዜጎችን ሁሉ በእኩልነት እያየን፤ ያለ እድልዎ በፍትሃዊነት ማስተዳደር ብንችል ምንኛ በታደልን ነበር፡፡ ጭንቃችን ሁሉ ለስደት ወጥተው የባህር ሲሳይ ስለመሆኑ ወገኖቻችን ቢሆን ኖሮ ምንኛ በታደልን ነበር፡፡ ከእጥረት፤ ከድህነት፤ ከፋክክር፤ ከስግብግብነት፤ ከስስት፤ ከጦርነት፤ ከግጭት፤ ወጥተን በበረከት፤ በመትረፍረፍ፤ በብልፅግና፤ በሰላም፤ በበረከት፣  በዕውቀት፣ በፍቅር ላይ ማተኮር ብንችል ምንኛ በታደልን ነበር፡፡ ግን ነገርዬው እንደሚወራው ቀላል አይደለም፡፡
 የአስተሳሰብና አመለካከት ስርነቀል ለውጥ ይፈልጋል፡፡  
የአመለካከት ቀዶ ህክምና ወይም ቴራፒ ይጠይቃል፡፡ የውጭ የሳይካትሪስት የሙያ ድጋፍ ያሻል፡፡ ከሁሉ በፊት ግን ከዘረኝነት መውጣት ይገባል፡፡ ጠባብነት መፀየፍ ያስፈልጋል፡፡ ሁላችንም እንደ ምናውቀው  ኢትዮጵያ የመሬትም፤ የውሃም፤ የሃብትም፤ የምርታማነትም ባጠቃላይ የምንም ችግር የለባትም፡፡ በተፈጥሮ በረከት የተትረፈረፈች ድንቅ አገር ናት፡፡ ችግራችን የአስተሳሰብ ነው፡፡ ችግራችን የእውቀት ነው፡፡ ችግራችን የሥልጣኔ ነው፡፡ ችግራችን የፍቅር እጦት ነው፡፡ ችግራችን የዘረኝነት ነው፡፡ ችግራችን የእኔ ብቻ ልበልፅግ ነው፡፡ ችግራችን ነገን አለማሰብ ነው፡፡
    ሆድ ካገር ይሰፋል በሚል
 ተረት አድገው ለሆድ እየለፉ
ይኸው በየቀኑ ሀገር
ትጠባለች ሆዳሞች ሲለፉ
መሄጃ ላጣ ሰው ሁሉን
 ቻይነቱን መንገሩ ባይከፋም
ተረቱን ቀይሩት
ሀገር ከሆድ እንጂ ሆድ
 ካገር  አይሰፋም። (ታሮስ)




Read 1331 times