Saturday, 17 June 2023 00:00

“ፈንድቃ፤ ታሪክ ባህልና ጥበብ እንጂ ቤት ብቻ አይደለም” አርቲስት መላኩ በላይ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ባለ 20 ወለል ህንፃ ለመገንባት ዲዛይን ማሰራቱን ተናግሯል ቦታውን ወደ ሊዝ አዙሮ ለ90 ዓመት መፈራረሙንና የ30 ዓመት ቀድሞ       መክፈሉን ገልጿል


       ከ35 ዓመታት በላይ ታሪክ ያለው ፈንድቃ ፈርሶ ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ሊሰራበት ለባለሀብት መሰጠቱ በአገር ባህልና ጥበብ ላይ ጥፋት ማድረስ ነው ሲል የፈንድቃ የባህል ማእከል ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ አርቲስት መላኩ በላይ ተናገረ ፡፡ አርቲስት መላኩ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት 25 ዓመታት በዚህ ማእከል ኢትዮ ከለር ባንድን አቋቁሞ፤ የበፊቱን የአሁኑንና መጪውን ትውልድ በማገናኘት፤ ባህልና ጥበብ ከምንጩ እንዲቀዳ ሲሰራ መቆየቱን ባለፈው ረቡዕ በፈንድቃ ባህል ማእከል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አብራርቷል፡፡
ማዕከሉ ቤት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት ከእነወዙ የሚታይበት፣ የህፃናት ቤተመፃሀፍትና የጫወታ መርሃግብር፣ ሰዓሊያን ያለ ክፍያ ስራዎቻቸውን ለእይታ የሚያቀርቡበት የስእል ጋለሪ፣ “ግጥማዊ ቅዳሜ” የተሰኘ የኪነጥበብ ዝግጅት የሚካሄድበት፣ እንደነ ሄኖክ ተመስገን ያሉ አንጋፋ የጃዝ ሙዚቀኞች የጃዝ ሙዚቃ የሚያቀርቡበትና በርካታ የባህልና የኪነጥበብ ክዋኔዎች ትልቅ ማእከል መሆኑንም አርቲስ መላኩ አብራርቷል፡፡
“ማዕከሉ ከነዚህ ሁሉ ስራዎች በተጨማሪ ከወጪው ዓለም አርቲስቶች ጋር በመተባበር 5 የሙዚቃ ሸክላ ያሳተመ ሲሆን ለዚህ ሁሉ ስራው የበጎ ሰው ሽልማትን ጨምሮ የቴድፌሎው 2022 ተሸላሚ፣ የፈረንሳይና የጣሊያን መንግስታት ለተመረጡና በሀገራቸው መልካም ለሚሰሩ ሰዎች የሚሸልሟቸውን የክብር ሽልማቶች ማግኘት የቻለ ሆኖ ሳለ ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ለመገንባት ሲባል ይህን የኢትዮጵያን ጥበብና ባህል የያዘ ማእከል ማፍረስ ከታሪክ ተጠያቂነት አያድንም” ሲል ነው፤ አርቲስት መላኩ ቅሬታውን የገለፀው፡
“ልማት አይልማ የሚል አመለካከት የለኝም” ያለው አርቲስቱ፤ ፈንድቃን ከእነቀለሙና ተግባሩ የሚይዝ ባለ 20 ወለል ህንፃ ለመገንባት አርክቴክቸራል ዲዛይን ማሰራቱን ገልፆ፤ ቦታውንም ቢሆን ወደ ሊዝ አዙሮ ለ90 ዓመት መፈራረሙንና የ30 ዓመት ቀድሞ ከፍሎ ይህንኑ የሚገልፅ ሰርተፍኬት ከሚመለከተው የመንግስት አካል ማግኘቱን በዋቢነት ጠቅሷል፡፡
“ግንቦት 25 ቀን 2015 ዓ.ም ለውይይት ተብለን ተጠርተን እንኳን ልንወያይ ውሳኔያቸውን ነው ያሳወቁን” ያለው አርቲስ መላኩ፤ “43 ቋሚ ሰራተኞች የሚያስተዳድር፣ በመላው ዓለም ቅርንጫፍ ሊከፍት የተዘጋጀ፤ በዓመት ከ20 ሺህ በላይ የውጪ ዜጋ የሚጎበኘው፣ የወደቁና የተረሱ የሀገር ባለውለታ አንጋፋ አርቲስቶች ሰርተው የሚኖሩበት ቤት እንደ ቀላል ይፍረስ መባሉ በእጅጉ ቅስም ሰባሪ ነው” ብሏል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኘችውና ከፅዳት ሰራተኝነት ተነስታ ድምፃዊና ተወዛዋዥ ለመሆን የበቃችው አርቲስት እመቤት፤ ከፈንድቃ ጋር አለምን ዞራ ብዙ ልምድና ማንነት ያገኘችበት ቤት ይፍረስ መባሉን ከሰማች በኋላ እንቅልፍ እንዳልተኛች በእንባ ታጅባ ተናግራለች፡፡
 ከአስተናጋጅነት ተነስቶ ብዙ የሙዚቃ መሳሪያዎችን እስከ መጫዎት ፕሮፌሽናል ተወሳዋዥና ሳውንድ ኢንጂነር እስከ መሆን የደረሰበት ለ16 ዓመት ያደገበት ቤቱ ሊፈርስ መሆኑን ሲያውቅ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንደገባ የተናገረው ደግሞ አርቲስ መሳይ አበባዬ ነው፡፡
መሳይ ከነዚህ ሁሉ እድገቶቹ በተጨማሪ በፈንድቃ ከኢትዮ ከለር ባንድና ከሌሎችም በፈንድቃ ከሚሰሩ ባንዶች ጋር የሚሰራ “ጉንጉን” የተሰኘ የራሱን ባንድ መመስረቱን ገልጾ ይህ ማዕከል ሲፈርስ ወዴት እንደሚሄድና ምን እንደሚሰራ ግራ እንደገባው ተናግሯል፡፡
አርቲስት ናርዶስን ጨምሮ የፈንድቃ ሰራተኞች፤ የሚመለከተው አካል የፈንድቃን ጉዳይ በድጋሚ እንዲፈትሽና እንዲያጤነው ተማፅነዋል፡፡
“ፈንድቃ ከፈረሰ ደግሜ የትም ቦታ ይህን መንፈስ ላመጣው ስለማልችል መንግስት ለባህል፣ ለጥበብና ለእሴት እቆረቆራሁ ካለ ፈንድቃን ከማፍረስ ይልቅ በቦታው ላይ የማልማት እቅዴን ፈትሾ እንዲፈቅድልኝና ባህልና ጥበብን ከማፍረስ እንዲቆጠብ እጠይቃለሁ” ብሏል አርቲስቱ በመግለጫው፡፡


Read 618 times