Saturday, 17 June 2023 00:00

ከተጠሩት ወይስ ከተመረጡት?

Written by  ድረስ
Rate this item
(1 Vote)

 ”«ብዙዎች ቢጠሩም የተመረጡት ጥቂቶች» ግድግዳዬ ላይ በኮባ ተጽፎ ተሰቅሏል።ደጋግሜ ደጋግሜ አነበዋለሁ ፤ደጋግሜ ደጋግሜ እገረማለሁ። የደጋ ሕዝቦች መሪ ሳይቀር የተጠራ እንጂ ያልተመረጠ ይመስለኝ ያዘ። በየዘርፉ ያሉ ኃላፊዎች የተጠሩ እንጂ የተመረጡ አይደሉም? መመረጥስ ምንድን ነው? እጅ አውጥቶ መሾም ወይስ የመለኮታዊ ኃይል መታከል?....እጠይቃለሁ። የማውቀው ቢኖር የመረጡት ይመርጣል።”
     
        «ሰላሜን»ንፋስ ወስዷታል። ውስጤ በስዉር መንሽ ሲጎሰም ይሰማኛል። እንባዬ ካልታወቀ ምንጭ ይፈልቃል። ሰው መሆን መከራን ማዘል ነው። ለራሴ የምትበቃ ሰላም ነበረችኝ ፤ጎረቤቶቼ አዝነው ባያቸው ለእነሱ አዋጠኋት። እንባ ተበዳድረን...ገንዘብ ተበዳድረን..
አጓጉል ንቃት። እንደዛ ፈላስፋ ሰው መሆኔን በህልሜ እያየሁ፣ ቢራቢሮ መሆኔን፣ ወይም አሁን ቢራቢሮ ሆኜ፣  ሰው መሆኔን ህልም እያየሁ መሆኑን አላውቅም።( Once upon a time, I dreamt I was a butterfly, fluttering hither and thither, to all intents and purposes a butterfly. I was conscious only of my happiness as a butterfly, unaware that I was myself. Soon I awaked, and there I was, veritably myself again. Now I do not know whether I was then a man dreaming I was a butterfly, or whether I am now a butterfly, dreaming I am a man.)
ግማሽ ህልም ግማሽ እውን_ሕይወት። ደሃ የሃብታም ፊት እንጂ ድህነቱ እንዳይከብደው አውቃለሁ። የጎረቤቶቼ ቤታቸው ፈርሶ አየሁ። ማን አፈረሰው? ለምን?...አልተመራመርኩም። መፍረሱ ብቻውን አመመኝ። አሮጊቷ የሙት ልጇን ልጅ ታቅፋ ፣እንባ በስርጉዷ ሞልቶ ስታባሽ አንጀቴ ተላወሰ። አለፍ ብዬ የማውቃቸው የተከበሩ ሸማኔ አስረስ በሰው እጅ መሞታቸውን ሰማሁ። ማን ገደላቸው? ለምን?...አልተመራመርኩም። መሞታቸው ብቻውን አመመኝ።
ሰላማችን የእንቧይ ካብ...
ኑሯችን የእንቧይ ካብ ...
ሥውር እጆች አሉ ከጀርባ። ግርማ ሌሊቱን ጥሰው የሚመዘዙ። መዳፋቸው ስለትና ብረት የያዘ ፣ፊታቸው ከፊት የራቀ ፣ጭካኔ አቡክታ የሰራቻቸው። ሸማኔ አስረስ ሸምነው ባለበሱ፣ እርቃን ገላ በሸፈኑ ሞት ለእሳቸው ? ብረት አቅልጠው ባሳረሱ፣ ሸክላ ጠፍጥፈው ነፍስ አድንን በሰጡ ሞት ለእሳቸው?
«እንኳን አርግዛና ሽል ይዛ በሆዷ
ደብረክ ደብረክ ነው ድሮም አካኼዷ»
ዘፋኙ ስሜቴን ተረድቷል።
ይቺ አገር እንዲያውም እንዲያው ናት እንኳንስ ዘንቦባት። በታሪክ የታጠርን የእንቦይ ካብ ኑሮ ኗሪዎች ነን። ታሪክ ሊለፍፍ የተቃናው ምላስ፣ ጓደኛውን አሳልፎ ለመስጠት ይታጠፋል። በአንዷ የጉንዳን መንገድ የምንተም፣ጉድጓድ ይገድበን ፍጡሮች ነን። እንኳንም ሞት ኖረ።
ተጠርቼ ይሁን ተመርጬ ባላውቅም በረሃ ገባሁ።
ከሰው ሸሽቼ ራቅ ደበቅ ብዬ መኖር ጀመርኩ። በረሃ ውስጥ መለስተኛ ጎጆ ቀለስኩ። ጣሪያዋ በስሱ የተከደነ ሣር ፣በደሬ እንጨት የተውተረተረ ግድግዳ፣ጠፍጣፋ ድንጋይ መደብ ፣አጎዛም ምንጣፌ ነው ።«አጋሙን ግራሩን ጎዝጉዘው ቢተኙ፤መች ይጎረብጣል የልብን ካገኙ?» ሙቀቱ ሲበዛ ከላዬ ላይ የተጣበቀችውን የጎሳዬ ቲሸርት አወልቃለሁ። ቀን ለአደን አወጣጤ ከሆነ ሰው ልጅ ጋር ያመሳስለኛል ፤ብኩርናዬን ባልሸጥም። ሚዳቋዋን፣ቆቋን ..በቀስት ነዳድፌ፣እምብሯቡጭ አጋጭቼ እሳት ፈጥሬ ፣ሥጋ ጥብሴን ብልት። እሳት ሊፈጥሩት አይቸግርም፤በተለይ ለኔ አካባቢ ሰዎች።
በዋሻ ውስጥ የበቀለች ጽጌሬዳን ነኝ። ከዓለም የምወዳቸው ቢኖሩ እንኳ የተከበብኩኝ በአጋም በጋሬጣ ።በረሃ ግማሽ ሰላሜ።ቤተሰብን፣ጎረቤትን በአሰብኩ ሰዓት ባነባም ቀሪውን ጊዜ የአዞን አዋዋል ስቃኝ፣ለጠወለጉ ቅጠሎች ሳዝን፣ለፀሐይ ደረቱን ለሰጠው መሬት ስተክዝ እውላለሁ። የወፎች ድሪሳ፣የዝንጀሮዎች ድሪያ፣የቆቆች ካካታ፣የእባቦችም ሲጥ ድምጽ ተለምዶኛል። ወደ ተፈጥሮ በቀረብኩ ጊዜ መከራ ከአንቀልባው ሹልክ ብሎ ጀርባዬን ይሸሻል። ኀዘን እንደ ውሽማ ፊቱን በግማሽ ሸፍኖ ከትክሻዬ አጥር ሲዘል ይታወቀኛል።
በረሃ ተመላልሰው የሚያዘምሩ ሰዎች የጣመ የላመ ያመጡልኛል።የተቋጠረ ምግብ ወዳጅ ነኝ (ይጥማልም መሰል)። ስለ ሃገሪቷ ኹኔታ በአጭር በአጭሩ ይነግሩኛል።
[ቅዳሜ ዕለት ፣ኹለት አህያ እየነዳ፣አራዳው ጎሽሜ ...
ሊያልፈኝ ነበር ጠራሁት። አህዮቹን ለሰርዶ ትቶ ወደ እኔ መጣ። እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ያለችዋ አህያ ፖለቲከኛ ነበረች። ለምን? የጎሽሜ አህዮች ሲነቅፉትና ወደ ሌላው ሳር ሲዞሩ ስላየሁ።
«እንደምን ነህ አያ ጺሞ)(ጺሜ ጎፍሮ ስላየ
«ይመስገነው ፣አገር ሰላም ነው?»(ጓጉቻለሁ
አንገቱን ቀረቀረ።በሱማያ ሽመሉ መሬት ፈለሰ። ከተፈለሰው መሬት አሥር ሳንቲም። ሳንቲሟ ዘውድ ነበረች። ዘውድም ድሮ የቀረች። የተቀበረች፤የተተወች። እግር ያለው ኹሉ ሊቆምባት ዝቅ ያለች።
ዓይኔ ዓይኑን ተከተለ። ከነፍሱ እየተማከረ ይመለሳል። ሙሐመድ ቢን ቱግላክ ትዝ አለው። ትዝ ብሎት ትዝ አስባለኝ። እጁ እየተወናጨፈ ፣ግንባሩ እየተኮፋተረ ቀጠለ...
«ሙሐመድ ቢን ቱግላክ ትዝ አለህ? የተማረ፣ሃይማኖተኛና ፍልስፍናም የማያጣው ሰው ነበር። የፋርስ ግጥሞች፣ሥነ-ፈለክም ይማርከዋል። አስደሳች ከሚባሉት ሰው ይመደባል። አዋቂነቱ ይበል ነበረ።ይኼን ያዩ የህንድ ነዋሪዎች እርሱ በነገሠ ጊዜ ብዙ  ነገር ይጠብቁ ያዙ።
ተሾመ።
ይህ ሰው ትክክለኛ ውሳኔዎችን ያውቃል፤ትክክለኛ መተግበሪያ ወቅቶችን ግን አያውቅም።«አስተዋዩ ሞኝ» እያሉ የሚጠሩት ዓይነት ነው። ሙከራዎቹ በቂ ዝግጅት ያልተደረገባቸው፣ሥራዎቹ ጥናት የሚያንሳቸው ናቸው።ዕውቀቱ ግን ይበል ነው። እናልህ የግዛቱን ዋና ከተማ መቀየር ፈለገ (ሌሎችን ክፍሎች ለመቆጣጠር እንዲያመቸው)። አወጀ። ሕዝቡ ወደ አዲሷ ከተማ ሲፈልስ በመሐል በድካም ብዙ ሰው ሞተ። 2 ዓመት ሳይሞላው ወዲያው ወደ ቀድሞዋ ከተማ ምርጫው መዞሩን አበሰረ _ግርምት። ሌላም ጊዜ ቶክን ከረንሲን(ምንዛሬን) አስተዋወቀ። በነጋዴዎችና በተራ ሰዎች መካከል ውዥንብር ፈጠረ። የተሰራው መገበያያ የጥራት ችግር ስለነበረበት ፎርጅድ ገበያውን አጥለቀለቀው ፤ከቆይታ በኋላ ወደ ቀድሞው መገበያያ ተመለሰ_ግርምት። አይገርምህም?..ይኼን የኢኮኖሚ ስብራት ለመጠገን በተወሰኑ የህንድ አካባቢዎች ግብር ጨመረ።ግብሩ ያስመረራቸው ኗሪዎች በሌብነት ተሰማሩ_ግርምት። ገባህ ጺሞ?»
«ገብቶኛል ጎሽሜ ...ጥሩ እህል ውኃም ሆኖ ታይቶኛል...» ተሰነባበትን።
[ የማቴዎስ ወንጌል ፣ እኔ ፣ደሳሳዋ ጎጆ...]
የጎበጠች ግመል ማየት ልማዴ ነው።በረሃውን ተቋቁማ ፣ስንቅ ለነጂዋ ተሸክማ ታልፋለች። ከተቀመጥኩባት የቁጥቋጦ ጥላ ሥር ሆኜ ላይዋ ላይ የሚያርፈውን የፀሐይ ብርታት አያለሁ። ጀርባዋ ስለ ሰው ልጆች መጉበጡን አስባለኹ። ሰሪዋ፣ውኃ ጥም እንዳያጠቃት ባያደርግ  ምን ይፈጠር? ከበደኝ። ሲገፉን ወድቀን ፤ወድቀን መነሳት ባንችል ፣አንዱ ሲጠላን አንዱ ባይወደን ምን ይውጠን? ለነገሩ፣የማንም ሰው አንገት ወደ እኔ አይዞርም።ቢያዩኝ አሳፍራለሁ ወይ ለመታየት አልበቃሁም ወይ ደግሞ እንድታያቸው አልተፈቀደላቸውም።
ፀጉሬ ጎፍሮ ፣ለምድን ገላዬ ለምዶ። ድንጋይ አፋጭቼ እሳት አወጣለኹ፣ የፈረደባትን ሚዳቋ አድናለኹ ፣ጠባብሼ እመገባታለኹ።ኑሮዬ ግለኝነት ይውረሰው እንጅ ሰፊ ዓለም ነው። ከሰው ልጅ የቀረብኝ «አሉባልታ» ነው። ሰው አዋዋሉን ካላሳመረ የሚቃርመው ወሬ፣የሚመርጠው መንገድ ዙሪያው ገደል ነው። አብሮ የሚንር ሰው የዋርካ ጥላ ሳይበቃው፣እኔ በቁጥቋጦ ጥላ ደስታዬን ማግኘቴ ይደንቀኛል።አዳም ብቻውን ይኾን ዘንድ ሴትን የሰራ አምላክ፣ እኔም ብቻዬን እንድደሰት የቁጥቋጦን ጥላ ሰጥቶኛል።
በረሃ ውስጥ ታሪክ አለ።
በየዋሻው ፣በየድንጋዩ የተቀረጸ ጥበብ።
ቢያዩት የሚያጠግብ ልዩ የአእምሮ ምግብ።
ሥጋዬን በሚዳቋ ሥጋ ብደልለውም፣ ጉልበቴ በዳገት አይደክምም። ከነብር ጋር ታግዬ ጉርምቦውን አንቄ አውቃለሁ። ሥጋ በል ከሆንኩበት ጊዜ አንስቶ አካሌ ፈርጥሟል።«እኒያ የደጋ ኑዋሪ ወገኖቼ ምን ውጧቸው ይሆን?» እላለኹ ዘወትር።
እግሬ መራመድን ይሻል ፤ልራመድበትስ አይደል የተሰጠኝ? ነበር። እነሳለኹ ኧፈፍ ብዬ ፣ መንገዴ ግን ጓያ ይበዘዋል። በእሸትነት ዕድሜው የማያራምድ (ጠላፊ)፣በአዋቂነት ዘመኑ መስበርን የለመደ።
ከጢሻው ውስጥ ጉምን ልሆን ብታደል እላለሁ። ሹልክልክ..እጥፍጥፍ ብዬ ከምፈልገው ድርስ።
ክረምት ጥቢን፣ ሌላውም ሌላውን ወቅት ጠራ።
መጠራት።
የገለጥኩት መጽሐፍ ትዝ አለኝ።ስለ መጠራት...ስለ መመረጥ።
በአምላካቸው ፊት ያለነቀፋ የሚኖሩት የዘካሪያስ እና የኤልሳቤጥ ልጅ _ዮሐንስ። በአንድ ጎኑ እኔን ይመስላል _በረሃ በመኖራችን። ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የቆለፈ፣ ሲወለድ የፈታ ተአምረኛ ነው። እኔ የእሱን ተአምር አንባቢ። ሄሮድስ ሰይፉን ወደዚህ ተአምረኛ ህጻን ቢያዞር ቤተሰቦቹ ተጨነቁ። አባቱን ገደሉ ፤እናቱ ይዛው ወደ በረሃ፤በዛው አረፈች። ማርያም ልጇን «እንውሰደው ይሆን ?»ብላ ስታማክረው«ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ» አላት። የግመል ጠጉር ለብሶ፣ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ «ሒድ የልጄን ጎዳና ጥረግ»ተብሎ እስኪመረጥ ድረስ። ሰማይን ከነግሱ፣ ምድርን ከነልብሱ የያዘ ፈጣሪ «አጥምቀኝ »አለው፤አጠመቀውም_መጥምቀ መለኮት።
መጠራት_መመረጥ።
[አራዳው ጎሽሜ ፣ወደ ደጋ ሲወጣ፣ከወገብ በላይ  እርቃን ሆኜ ፀሐይ እየሞቅኩ...
አጭር ከዘራውን ያወራጫታል። ሲሄዱ ባዶ የነበሩት አህዮች ሲመለሱ ተጭነዋል። ጭነት በሰውም ይኸው ነው። አንዱ ሸክማችንን ሲያራግፍ ሌላው ሸክም ይሰጠናል። ጎሽሜ አህያ ይወዳል። ከደጋ ሕዝቦች መሪ ይልቅ አህያ ትበልጣለች ይላል። ለምን? ቢሉት በአንዴ ፊቷንም ኋለዋንም ታያለች ነው መልሱ።
ፊትንም ኋላንም ማየት።
የደጋ ሕዝቦች መሪ ሌላኛው ቱግላክ መሰል ነው። የሚተገብራቸው ሥራዎች ሁሉ የተጠኑ የማይመስሉ ።ፊቱን እንጅ ኋላውን ያላገናዘቡ ናቸው።ጎሽሜ በዚህ መሪ መማረሩን የማውቀው «አንተማ ታድለህ»ሲለኝ ነው።
አራት ወቅት ፤አራት ወንጌል።
ከአራቱ ወቅት ጥቢን እመርጣለኹ። መስከረም (ክረምት የሚመሽባትን)፣ጥቅምት (ጠቃሚዋን ጊዜ)፣ ኅዳር (ገበሬ ሰብሉን ከአራዊት ሊከላከል ውጭ የሚያድርባትን)። ከወንጌል ለማቴዎስ አደላለሁ። ስለ መመረጥ ስለ መጠራትም ስለሚነግረኝ። ጎሽሜ አልኩት..
«ወዬ! አንተ የበረሃ ሰው»
«መንግሥት ምን ቢሆን ይሻላል? ማለቴ..በዕውቀት፣ስዩመ እግዚአብሔር፣በምርጫ...ወይስ በምን?»
«ዕውቀት ለቱግላክ መች አነሰ? ሌላውስ ለሌላው መች ጠበበ...?»
እየጠየኩት ይጠይቀኛል። የደጋው መሪ ያደግኩበትን ሰፈር እንድለቅ ሰበቤ ነው። የደጋ ነዋሪዎች ግን ከአፋቸው ሞልቅቀው አጉርሰው አሳድገውኛል።ስለ እነሱ እጨነቃለኹ።
የጎሽሜ ብሶት ሲንፈቀፈቅ ባየውም በቃል ማዋለድ አልቻለም። ድርጊት ቃልን ሲበልጠው አየሁ። አፉ ደጋግሞ «ነገራችን ኹሉ የእንቧይ ካብ» እያለ ወደ ሚፈራው ወ ወደ ሚጠላው ኼደ።
ወደ ጎጆዬ ገባሁ።
«ብዙዎች ቢጠሩም የተመረጡት ጥቂቶች» ግድግዳዬ ላይ በኮባ ተጽፎ ተሰቅሏል።ደጋግሜ ደጋግሜ አነበዋለሁ ፤ደጋግሜ ደጋግሜ እገረማለሁ። የደጋ ሕዝቦች መሪ ሳይቀር የተጠራ እንጂ ያልተመረጠ ይመስለኝ ያዘ። በየዘርፉ ያሉ ኃላፊዎች የተጠሩ እንጂ የተመረጡ አይደሉም? መመረጥስ ምንድን ነው? እጅ አውጥቶ መሾም ወይስ የመለኮታዊ ኃይል መታከል?....እጠይቃለሁ። የማውቀው ቢኖር የመረጡት ይመርጣል።
ብዙ ስሜቶች ወደ እኔ ተጠሩ።
ከተጠሩት ውስጥ መረጥኩ። የመረጥኩት መረጠኝ።
ዝምታ ነበር ዋናው።


Read 811 times