Saturday, 17 June 2023 00:00

“እኛን ያስተሳሰረን የኢንዱስትሪውን ተዋናዮች ተጠቃሚ ማድረግ ነው”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 የአገራችንን የመዝናኛ ኢንዱስትሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግና ለማዘመን እየሰራ ያለው ሰዋሰው መልቲ ሚዲያና በላቀ ቴክኖሎጂና በአዳዲስ አሰራሮች የብሮድካስት ኢንዱስትሪውን ተቀላቅሎ በአጭር ጊዜ ውስጥ  ተቀባይነትን እያተረፈ የሚገኘው ናሽናል ሚዲያ አክስዮን ማህበር (NBC Ethiopia) የፈጠራ ኢንዱስትሪውን ወደ ከፍታ ለማራመድ በጋራ ለመስራት ተስማሙ፡፡
የሰዋሰው መልቲ ሚዲያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብቱ ነጋሽ እና የNBC Ethiopia ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ብሩክ ከበደ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የስምምነት ሰነድ ባለፈው ረቡዕ ሰኔ 7 ቀን 2015 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ተፈራርመዋል፡፡  
የሁለቱ ተቋማት ጥምረት የአገራችን ሙዚቃ ዓለማቀፍ ደረጃ እንዲደርስ የሚያስችል ነው ያሉት የNBC Ethiopia ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ብሩክ ከበደ፤ እኛን ያስተሳሰረን የኢንዱስትሪውን ተዋናዮች ተጠቃሚ ማድረግ ነው  ብለዋል፡፡
የሰዋሰው መልቲሚዲያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሃብቱ ነጋሽ በበኩላቸው፤ዓላማቸው ምሳሌ የሚሆኑ ክዋክብትን መፍጠርና ወደ ህዝብ ማድረስ መሆኑን ጠቁመው፣ በተፈጠረው ትሥሥርም በሙዚቃ ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎች ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም የሚያገኙበት ሥርዓት ይዘረጋል ብለዋል፡፡
 የሁለቱ ዘመናዊ ተቋማት ህብረት በሙዚቃው መስክ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆኑ ውጤታማና ባለተሰጥኦ ሙዚቀኞችን ለማፍራት መሰረት ይጥላል የተባለ ሲሆን፤ የሀገራችንን ሙዚቃ ፕሮዳክሽን በሁሉም ረገድ ወደፊት የሚያራምድ ተግባራትን ለመፈፀም እንደሚያስችልም ተገልጧል፡፡
ጥምረቱ፤ ˝በሁሉም መስክ የተሰማሩ የመዝናኛው ኢንዱስትሪ ተሳታፊዎች ድምፃውያን፣የዜማና የግጥም ደራሲዎች፣ አቀናባሪዎች፣ ወዘተ-- ከስራቸው የሚመጥናቸውንና የሚገባቸውን ጥቅም እንዲያገኙ የሚያስችል ታላቅ እርምጃ ነው˝ ተብሏል፡፡
”በዘመናዊው ዓለም የመዝናኛ ኢንዱስትሪው ዋነኛው የተደራሽነት አውታር የብሮድካስት ኢንዱስትሪው ነው፤ መዝናኛውና ብሮድካስቱ በአንድ ጥላ ሥር የሚሰሩና ተጣማሪ ዘርፎች ናቸው፡፡ ዛሬ ሰዋሰው መልቲሚዲያና ናሽናል ሚዲያ አክስዮን ማህበር ለሃገራችን ያስተዋወቁት ይህንን ዘመናዊ ጥምረት ነው፡፡” ብለዋል፤ሁለቱ ተቋማት ባወጡት መግለጫ፡፡

Read 902 times