Saturday, 17 June 2023 00:00

ታላቅ የመጻሕፍት አውደርዕይና የሚዲያ ኤክስፖ በግዮን ሆቴል ይካሄዳል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ለአምስት ቀናት የሚዘልቅ የመጻሕፍት አውደርዕይና የሚዲያ ኤክስፖ፣ ሰኔ 28 ቀን 2015 ዓ.ም በግዮን ሆቴል እንደሚከፈት የተገለጸ ሲሆን፤መርሃግብሩ  የኪነጥበብ ፌስቲቫልም ነው ተብሏል፡፡
የሃሳቡ ጠንሳሽና  የመርሃግብሩ አዘጋጅ ድርጅት፣ የዩቶጵያ ሚዲያና ኤቨንት ዋና ሥራ አስኪያጅ ዘርይሁን ታየ እንዲሁም በዚህ ፕሮጀክት ላይ ራዕዩን  በመደገፍ አብረውት ለመሥራት የተስማሙት ገጣሚ ኤፍሬም ስዩምና ሰዓሊ ደረጀ የኋላእሸት ከትላንት በስቲያ ሐሙስ፣ ዝግጅቱን አስመልክተው በግዮን ሆቴል አዋሽ አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የመርሃግብሩ ዋና አዘጋጅና የመድረክ መሪ ዘርይሁን ታየ በመግለጫው ላይ እንዳብራሩት፤ በዚህ አውደርዕይና ፌስቲቫል ላይ መገናኛ ብዙሃንን፣ ኪነጥበብን፣ ዕደጥበብን፣ ሥዕልን፣ ትምህርትና ቴክኖሎጂን እንዲሁም የፋሽን ኢንዱስትሪውን ጨምሮ ሰባት ዘርፎች የሚሳተፉበት ሲሆን በአጠቃላይ የ150 ድርጅቶች ድምቀት የሚታይበት ይሆናል ብለዋል፡፡
በዚህ አውደርዕይና የኪነጥበብ ፌስቲቫል ላይ ከ50 ሺ ህዝብ በላይ ይታደምበታል ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ ዘርይሁን ተናግረዋል፡፡
መርሃግብሩ፤ ደራሲያንና ተደራሲያን እርስበርስ የሚተዋወቁበትና ፊትለፊት የሚያወሩበት፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ሥራቸውን የሚያቀርቡበትና እርስ በርስ የሙያ አንድነት የሚፈጥሩበት ይሆናልም ተብሏል፡፡
ዓመታዊ ነው በተባለው በዚህ  የመጻሕፍት አውደርዕይና ፌስቲቫል ላይ አዳዲስ መጻሕፍት የሚመረቁ ሲሆን፤ በዋናነትም የገጣሚ ኤፍሬም ስዩም “ምልኪና ቡና“ የተሰኘ አዲስ የግጥም መጽሐፍ በታላቅ ክብር እንደሚመረቅ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተጨማሪም መርሃግብሩ፤ የጠፉና የማይገኙ መጻሕፍት ለዕይታ እንደሚቀርቡበትና መጻሕፍት ከ30- 50 ፐርሰንት በሚደርስ  የዋጋ ቅናሽ የሚሸጡበት እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡
በዚህ የኪነጥበብ ፌስቲቫልም እንደሆነ በተነገረለት መርሃግብር ላይ፣ የመዝናናትና የመነቃቃት መንፈስ የሚፈጥሩ ግጥሞች፣ ቅኔዎች፣ መነባንቦች፣ ዲስኩሮችና የሙዚቃ ሥራዎች  እንደሚቀርቡም ነው የተነገረው፡፡
መርሃግብሩን ለማዘጋጀት የ2 ሚሊዮን ብር በጀት እንደተመደበለት የገለጹት ዋና አዘጋጁ ዘርይሁን ታየ፤ ይህንን አውደርዕይና ፌስቲቫል ከቀደምቶቹ ዝግጅቶች  አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
የመጻሕፍት አውደርዕይና የሚዲያ ኤክስፖው ሰኔ 26  በብሔራዊ ቴአትር በድምቀት ይከፈታል ያሉት ዋና አዘጋጁ፤ ሰኔ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ደግሞ በግዮን ሆቴል እንደሚከፈት ጠቁመዋል፡፡   

Read 3007 times