Saturday, 29 April 2023 19:15

በመመለስ መንገድ ላይ

Written by  -መኮንን ደፍሮ-
Rate this item
(1 Vote)

 መነሻ ርዕስ፡ ዘሪሁን የትምጌታ፣ በመመለስ መንገድ ላይ፣ 1997 ዘይት ቀለም እና አክሬሊክሸራ ላይ On the Way to Return, 2005 Oil & Acrylic on canvas 62 × 78 cm


       ሳሎን ቤት ሶፋዬ ላይ ተንጋልዬ አንዱን የነገር ሰበዝ እየመዘዝኩ ሌላዉን እየጣልኩ በሐሳብ እባዝናለሁ፡፡ ዛሬ ያለወትሮዬ የሀኒባል ናፍቆት ተቀስቅሶ ክፉኛ ሲያንገላታኝ ዋለ፡፡ ትዝታዉ ከትዉስታዬ ማኅደር በምን ሰበብ እንዳንሰራራ እንጃ፡፡ ከሶፋዬ ሳልወርድ ነዉ ምሽቱ ነጉዶ እኩለ ሌሊት የሆነዉ፡፡ ቅዳሜ ከሌሎች ቀናት ተለይቶ የተለየ ስሜት የሚፈጥርብኝ ቀን ስለሆነ ነዉ መሰል እድሜዉ ያጥርብኛል፡፡ ብዙ ጊዜ ቅዳሜን ከቤቴ ዉጪ ማሳለፍ አልመርጥም፡፡ የዛሬዉን ቅዳሜ ግን ከተማ ስዞር ዋልኩ፡፡ ዉሎዬን አስደሳች ካደረጉት ነገሮች አንዱ ፊት ለፊቴ የማየዉ፣ መሐል ፒያሳ የሚገኝ የሥነ ጥበብ ጋለሪ ጎራ ብዬ ሳለ የገዛሁት የሥዕል ሥራ ነዉ፡፡ ሥዕሉን ይዤ እንደመጣሁ የሰቀልሁት ፎቅ መኝታ ቤቴ ዉስጥ ነበር፡፡ ሥዕሉ የአንድ የአገራችን ታዋቂ ሠዓሊ ሥራ ነዉ፡፡ ርዕሱ በመመለስ መንገድ ላይ ይሰኛል፡፡
 ነፍሱን ይማረዉና አባቴ ሥዕል መሰብሰብ እጅግ ይወድ ነበር፡፡ ይህ ሥዕል ግን ቤቴ ዉስጥ ከተከማቹት የአባቴ ሥዕሎች በበለጠ ስቦኛል፡፡
     ሀኒባል ከወራት በፊት ለምልጃ መሥራያ ቤቴ ድረስ መጥቶ ሳለ እጅግ እንደጠላሁት ቁርጡን ነገሬ ሸኝቼዋለሁ፡፡ ዛሬ ግን ደርሶ ናፈቀኝ፡፡ ጠረኑ ናፈቀኝ፣ ድምፁ ናፈቀኝ፡፡ እንዲህ የናፍቆት ዳይናማይት ኩራትን ያፈራርሳል? ፍቅር ምንድን ነዉ? አሁን ቤቱ ብሄድ ምን ይለኛል? ዉሻ አድርጎ ይቆጥረኝ ይሆናል፤ ወደ ትፋቱ የሚመለስ ዉሻ ነዉና፡፡ ዉሻ ነኝ? እኔ ኤልሳቤጥ ወንዱን ሁላ በተርታ ደጄ የማሰልፍ ልዕልት እንጂ ዉሻ አይደለሁም፡፡ ይኸን እዉነት ሀኒባል ወርቁ ማወቅ አለበት፣ ሁሉም ሰዉ ማወቅ አለበት፡፡ ከራሴ ጋር በብርቱ ስሟገት ብቆይም ናፍቆቱን መቋቋም ተሳነኝ፡፡ ዉሻ መሆንን ወድጄ ዐይኑን ለማየት በእኩለ ሌሊት መኪናዬን አስነስቼ ወደ መኖሪያ መንደሩ ጉለሌ ከነፍኩ፡፡
በዉድቅት ሌሊት፣ በጥር ብርድ እየተንሰፈሰፍኩ ካዛንቺስን አቋርጬ፣ ታላቁን ቤተመንግሥት ዞሬ አራት ኪሎ እንብርት ስደርስ መኪናዬ ተበላሽቶ መሐል አዉራ መንገዱ ላይ ተገተረ፡፡ አልፎ አልፎ እንደ ጀት ባጠገቤ ከሚከንፉ መኪኖች በስተቀር አራት ኪሎ አደባባይ አካባቢ በዐይን የሚታይ የሰው ዘር አልነበረም። ከመኪናዬ ወርጄ የመኪናዬን ጎማዎች ጤንነት ፈተሽኩ፣ ጤናማ ነበሩ። በተገተርኩበት የሚረዳኝ ሰው ፍለጋ በዐይኖቼ ባከንኩ። ፊት ለፊቴ አራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ በር ላይ ሁለት በካፖርት የታጀሉ ሰዎች ተቀምጠዋል፣ እኔ ላይ ያተኮሩ ይመስላል፡፡ ከታች ከጆሊ ባር ሁለት ወንዶች ወጥተዉ ወዳለሁበት መምጣት ጀመሩ፡፡ ወንዶቹ ጎን ለጎን ሆነዉ ሳለ የሚነጋገሩት ግን ድምፃቸዉን አጉልተዉ ነዉ፡፡ ብዙ የጠጡ አይመስሉም፣ ርምጃቸዉ ፈጣን የተሳለጠ ነዉ፡፡ ገርምመዉኝ አልፈዉ በጥድፊያ ሽቅብ አቀኑ፡፡ የእጅ ሰዓቴን ተመለከትኩ፣ ከምሽቱ 6፡34፡፡ መኪናዬ ዉስጥ ገብቼ መስፍን የተባለ መካኒክ ደንበኛዬ በቅርቡ የሰጠኝን አድራሻዉ የሠፈረበት ቢዝነስ ካርድ ፍለጋ የመኪና ኪሱን መበርበር ገባሁ፡፡ ከጥቂት ፍልጋ በኋላ ካርዱን አግኝቼ የመስፍንን የሞባይል ቁጥር መታሁ፡፡ ሞባይሉ ጥቂት እንደ ጠራ መስፍን መለሰ፡
 “ሄሎ?” አለ ጎርናና ድምፅ፡፡   
   “ሄሎ? መስፍን?፡፡”                    
    “አዎ ነኝ፡፡ ማን ልበል?”
“ኤልሳቤጥ ነኝ፡፡ የጋራጃችሁ ደንበኛ …” ንግግሬን ሳልጨርስ፡
“በሰላም ነዉ ኤልሳቤጥ?፡፡”
 “ርዳታህን ፈልጌ ነዉ፡፡ እየነዳሁ መኪናዬ ቀጥ አለ …” አሁንም ንግግሬን ሳልቋጭ፡
 “የት አካባቢ ነሽ?”
 “አራት ኪሎ አደባባዩ ጋ፡፡”
“በቅርብ ሊረዳሽ የሚችል ሰዉ የለም?”
“የለም”፡፡ ብቻዬን ነኝ፡፡”
  “እሽ መጣሁ፡፡” ስልኩ ተዘጋ፡፡
 * *
የሌሊቱን ኃያል ብርድ ለመቋቋም ሲጋራዬን አቀጣጥዬ መኪናዬ ዉስጥ የመስፍንን መምጣት በቋፍ እጠባበቃለሁ፡፡
መንገዱ ላይ የሚከንፉት መኪኖች ቁጥር ከደቂቃዎች በፊት ከነበረዉ ቀንሷል፡፡ ከላይ ቁልቁለቱን እየበረረ የመጣዉ ታክሲ አጠገባችን ደርሶ ሲቆም መስፍን ሊሆን እንደሚችል ጠረጠርኩ፡፡ በእርግጥም ግምቴ ትክክል ነበር፡፡ መስፍንና ታክሲ ሾፌሩ ከታክሲዉ ወርደዉ ጎዳናዉን ተሻግረዉ ወደ እኔ መጡ፡፡ መስፍን በቀኝ እጁ ሳምሶናይት የሚያክል ሳጥን አንጠልጥሏል፡፡ ከመኪናዬ ወርጄ ለሠላምታ ጠበቅኋቸዉ፡፡ መስፍን ቀድሞ አጠገቤ ደርሶ፡
“ሰላም ኤልሳቤጥ?” አለ ቀኝ እጁን ለሰላምታ እየዘረጋ፡፡ እጁን ጨበጥኩ፡፡
“ለገጠመሽ ችግር አዝናለሁ፡፡
“ምንም አይደል፡፡ የሚያጋጥም ችግር ነዉ፡፡”
 “የመኪናዉ ችግር ምንድን ነዉ?”
 “አላወቅሁም፡፡”
 “ስትነጂዉ የተለዬ ድምፅ ነበረዉ?”   
“አዎ፣ ከታች ዳገቱን ስመጣ የተለዬ ድምፅ ነበረዉ፡፡”                    
 መስፍን ተጎንብሶ መኪናዉን አየና፡
 “ዘይት አፍስሷል፣ ሞተር ነክሷል፡፡” አለ፡፡    
 “ከባድ ብልሽት ነዉ?”
 “አዎ፡፡ ኮሎዉና ብሮንዚናዉ መቀየር አለበት፡፡” የመኪናዉን ኮፈን ከፍቶ መፈተሽ ጀመረ፡፡
 “ለመሠራት ስንት ቀን ይፈጃል?”
  “ሳምንት ይወስዳል፡፡”
የከተማ አዉቶቡስ ተገልጋዮች ማረፊያ ወንበር ላይ ከተኛዉ ሰዉዬ ልሳን የሚፈልቀዉ ወሬ አለንበት ድረስ ይሰማል፡፡      
“ፍቅር እንጂ ገንዘብ መች ጠፋ … ሸርሙጣ ስለሆነች አይገባትም … ለገንዘብ ብሎ ሰዉ ገደለ …”
 ሰዉየዉ ወፈፌ ሳይሆን አይቀርም፡፡                
“መኪናሽ ነገ በተጎታች ጋራጅ ይገባል፡፡” አለ መስፍን የመኪናዉን ኮፈን እየገጠመ፡፡                                      
  “መልካም፡፡”  
 “ቤትሽ እናድርስሽ፡፡” መኪናዉን ለመኪና ጠባቂዎቹ እንሰጠዋለን፡፡” ጆሊ ባር ጋ ወደ ቆሙት ሁለት መኪና ጠባቂዎች አመራ፡፡
የሌሊቱን ቁር የደረብኩት ወፍራም ካፖርት አልመከተልኝም፡፡
 የታክሲ ሾፌሩ ብርዱን ለመቋቋም ሳይሆን አይቀርም አጠገቤ ቁሞ ሲጋራዉን በላይ በላዩ ይምጋል፡፡“በቃ እንሂድ፣ እንዲጠብቁት ነግሬያለሁ፡፡” አለ መስፍን እጁን እያፋተገ መጥቶ፡፡
ተከታትለን ታክሲዉ ዉስጥ ገባን፡፡               
“የት ነዉ ቤትሽ?” ሾፌሩ፡፡
 “ቦሌ፡፡”
 የተሳፈርንበት ታክሲ ቁልቁል ወደ ቤተመንግሥት ከነፈ፡፡  
                   * * *
ታላቁ ቤተመንግሥትን አልፈን ካዛንቺስ ደርሰናል፡፡ መንደሬ ለመድረስ ሩብ ሰዓት ቢወስድ ነዉ፡፡ መስፍን ጎኔ ነዉ የተቀመጠዉ፡፡ የሚያጨሰዉ ሲጋራና የተቀባዉ ሽቶ ጠረን ተዋህዶ በአፍንጫዬ ይሰርጋል፡፡
 አጥንቴ ድረስ ይሰማኝ የነበረዉ ብርድ ተገፎ ሰዉነቴ ተዝናንቷል፡፡ ሾፌሩ አታላይ ናት የተሰኘዉን ዘፈን ከዘፋኙ ዘዉዱ ወርቅነህ ጋር ጮክ ብሎ አብሮ ይዘፍናል፡፡ ግለ ታሪኩ ከዘፈኑ ጋር ቁርኝት ሳይኖረዉ አይቀርም፡፡  “አንተ ቀስ ብለህ ንዳ! ገደል እንዳትከተን፡፡” አለ መስፍን እኔ ላይ አተኩሮ፡፡
 ፈገግ አልኩ፡፡
“ሙዚቃዉን ደግሞ ቀንሰዉ!” በተቃራኒዉ ሾፌሩ የሙዚቃዉን ድምፅ ከፍ አደረገዉ፡፡ እኔና መስፍን በግርምት ፈገን ተያየን፡፡
“የእናንተ ሰፈር የት ነዉ?” ወደ መስፍን ዞሬ፡፡  
“ሽሮሜዳ፡፡”
ሾፌሩ ዘፈኑን ተከትሎ መዝፈኑን አላቋረጠም፡፡
አታላይ ነች ሆድዬ አታላይ ነች
አታላይ ነች ሆድዬ አታላይ ነች
መስላ ገብታ ከሆዴ ቤቷን ሠራች
 ላታዛልቅ ላታዋጣኝ ጥላኝ ጠፋች፡፡  
     መኖሪያ መንደሬ ደርሰን ቤቴ ፊት ለፊት ቆመናል፡፡ ምሽቱ ጠፍ ጨረቃ ነዉ፡፡ ጠፈር ሰሌዳ ላይ የፈሰሱት ከዋክብት ድምቀት አጀብ ነዉ፡፡           
“ፊት ለፊት የምታዩት ነዉ ቤቴ፡፡” አልኩ በአመልካች ጣቴ ቤቴን እየጠቆምሁ፡፡
  “ደህና እደሪ፡፡” አለ ሾፌሩ፡፡
“ደህና እደሩ፡፡” ከመኪና ወረድሁ፡፡ መስፍንም በእሱ በኩል የነበረዉን በር ከፍቶ ተከትሎኝ ወረደ፡፡
 “የመኪናሽን ቁልፍ ስጪኝ? በእዚህ ሳምንት ተሠርቶ ትረከቢያለሽ፡፡”
 “መልካም፡፡” ቁልፉን ሰጠሁት፡፡
 “ደህና እደሪ፡፡”
“ደህና እደር፡፡”
ግቢዬን በር ከፍቼ እንደ ገባሁ እነ መስፍን መኪናቸዉን አስነስተዉ ከነፉ፡፡ ፍቅሩን ለመግለፅ እላዬ ላይ የሚዘለዉን ዉሻዬን አንበስን አባርሬ መኝታ ቤቴ ዘለቅሁ፡፡
     በእኩለ ሌሊቱ ገጠመኝ ከአእምሮዬ ተደምስሶ የነበረዉ ሀኒባል እንደገና ነፍስ ዘርቶ ተንሰራፋ፡፡ ወደ ልብስ ቁምሳጥኑ አምርቼ ቤቴ ዉስጥ የቀረዉን ብቸኛ የግል ቁሱን ስካርፑን አንገቴ ላይ ጠምጥሜ አልጋዬ ዉስጥ ገባሁ፡፡
                       * * *  
አርብ ረፋድ፡፡ መኪናዬ ጋራጅ በገባ በሳምንቱ፡፡ በብዙ አይነት ትዕይንት የተሞላ ህልሜን እየኮመኮምኩ እንቅልፌን እለጥጣለሁ፡፡ እንዲህ እንደ ሬሳ ወድቄ ሳለ ነዉ ለዕዝኔ እንግዳ ያልነበረ የደወል ድምፅ ቀስቅሶ ያነቃኝ፡፡ የደወሉ መደጋገም ፈጠኜ ከመኝታዬ እንድነሳ አስገድዶኝ እየተጣደፍኩ ፎቁን ወረድኩና ሳሎኑን አቋርጬ ወደ አጥሩ በር ገሰገስኩ፡፡ በሩን ስከፍት መስፍን ተገትሯል፣ መኪናዬን መንገዱ ዳር አቁሞ፡፡
ታዲያስ መስፍን?፡፡”
ለሰላምታ የዘረጋሁለትን እጄን ጨብጦ እንደያዘ ጉንጩን ሰጠኝ፡፡ ጉንጭ ለጉንጭ ተሳሳምን፡፡
 “መኪናዬ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ይሠራል ብዬ አላሰብኩም ነበር፡፡ በጣም አመሰግናለሁ፡፡”
 “ምንም አይደል፡፡” የመኪና ቁልፌን ሰጠኝ፡፡
“እባክህ ቤት ግባ?” ወደ ቤቴ እንዲዘልቅ በዐይኖቼ እየተማጠንኩ፡፡ አልተግደረደረም፣ ወደ ዉስጥ ዘለቀ፡፡
 “ዋዉ! ግቢሽ በጣም ዉብ ነዉ፡፡”
 “አመሰግናለሁ፡፡”
 መስፍን ሳሎን ሶፋ ላይ ተቀምጦ የቤቴን ቁስ በዐይኑ ያስሳል፡፡ እጅግ ሸበላ ነዉ፣ ቁመተ ሎጋ፡፡   
“ሠዓሊ ነሽ እንዴ?፡፡” ዐይኖቹን ግድግዳ ላይ የተሠቀሉት ሥዕሎች ላይ እንደተከለ፡፡
“ሥዕል እወዳለሁ እንጂ ሠዓሊስ አይደለሁም፡፡”
  “ብዙ ሥዕል ሰብስበሻል፡፡” ዐይኖቹ ገላዬ ላይ ሲንከራተቱ እጅ ከፍንጅ ያዝኳቸዉ፡፡ በዐይኑ እንደ ሙዳ ሥጋ ሊጎርሰኝ ምንም አልቀረዉ፡፡
 “ብዙዎቹ የአባቴ ስብስቦች ናቸዉ፡፡”
 የለበስኩት ፒጃማ ስስነት ገላ አጋልጦ ሚያሳይ ስለነበር ምቾት ነስቶኛል፡፡ ይኸን ፒጃማ ለብሼ ማንም አይቶኝ አያዉቅም፣ ከሀኒባል በቀር፡፡ ከመስፍን ፊት እስክሰወር ተጣደፍኩ፡፡ መስፍንን እንዲያጫዉት በሚል ቴሌቪዥን ከፍቼ ወደ መኝታ ቤቴ ዘለቅሁ፡፡
መኝታ ቤቴ ስገባ አንገቴ ላይ ያደረዉ የሀኒባል ስካርፕ ወለል ላይ ወድቋል፡፡ አንስቼ ልብስ ቁምሳጥኑ ዉስጥ አኖርኩና ስስ ፒጃማዬን አዉልቄ መስፍን የፈዘዘበትን ርቃን ገላዬን በቁም መስታወቱ ዉስጥ መገምገም ጀመርኩ፡፡
ጠይም ፊቴ የወዛ ነዉ፡፡ ፀጉሬ በረጅም አንገቴ ዙሪያ ተዘናፍሏል፡፡ ከንፈሮቼ በሲጋራ ፍም ቢጠለሹም ዉበታቸዉ አልደበዘዘም፡፡ ከንፈሬን አሽሽቼ ጥርሶቼን አጠናሁ፣ በረዶ ይመስላሉ፡፡ አንገቴ ላይ ሦስት ክርክራቶች አሉ፡፡ ጡቶቼ እንደ በረሃ ተራራ ደረቴ ላይ ጉብ ብለዋል፡፡ ከጡቶቼ ዝቅ ብሎ ያለዉ አካሌ እህል በልቶ የሚያድር አይመስልም፡፡
 የአፍረቴ ጭገር ጎፍሯል፡፡ ቁመናዬ ዛሬም ቅርጹ አልተዛባም፡፡
መለመላዬን ሆኜ ራሴን በመስታወት ተመልክቼ አላዉቅም፡፡ መስታወት ላይ ማፍጠጡን ትቼ ጅንስ ሱሪ በቲሸርት ለበስኩና ቁርስ ለመሥራት ማብሰያ ቤት ገባሁ፡፡ ከመስፍን ጋር ትሪ ከበን የሠራሁትን ቁርስ በጋራ በመመገብ ላይ ነን፡፡
 “ጣፋጭ ምግብ ነዉ የሠራሽዉ፡፡ ባለሙያ ነሽ፡፡”
 “ታዲያ መች በላህ?” ባዶ ብርጭቆዉ ላይ ዉስኪ ቀዳሁለት፡፡
 “ብዙ በላሁ፡፡” ያዘጋጀዉን ሦስተኛ ጉርሻ ሊያጎርሰኝ እጁን ወደ አፌ ሰደደ፡፡ ጉርሻዉን ጎረስኩ፡፡
 “አግብተሽ ነዉ የምትኖሪዉ ኤልሳቤጥ?”
 “አላገባሁም፡፡ ላጤ ነኝ እስካሁን፡፡”
“እንዴት ሳታገቢ? ትዳርን ከሚፈሩት ነሽ መሰል? ትዳር እኮ ጥሩ ነዉ፡፡”
 “እኔ ትዳርን ከሚፈሩት አይደለሁም፡፡ ሂ ሂ ሂ፡፡ ትዳር ምኑ ያስፈራል?”
“አለ አይደል፣ ነፃነትን ስለሚገድብ፡፡ እስርን ፍራቻ፡፡”
 “እንዲህ የሚስቡት ሌሎች ናቸዉ፡፡”
 “አግብተሃል አንተ?”
“አላገባሁም፡፡” ብርጭቆዉን አንስቶ ተጎነጬ፡፡” “እኔ ያላገባሁት ዕድሌ ሳላልተቃና ነዉ፡፡ ዉሃ አጣጬን ስላላገኘሁ፡፡” ብዙ ዝርዝር ታሪኮችን ሳንሱር አድርጌ ግለ ታሪኬን በአጭሩ አወጋሁት፡፡
ሕይወት ትንግርቱ ብዙ ነዉ፡፡
ወደ ከዳኝ፣ ወደ በደለኝ ሀኒባል ወርቁ በመመለስ መንገድ ላይ (ዉሻ ነኝና) መስፍንን አገኘሁ፡፡    
                  * * *
     ምድር ጥቂት በጎ ሰዎችን ነዉ በጉያዋ የያዘችዉ፡፡ መስፍን ከእነዚህ በጎ ሰዎች አንዱ ነዉ፡፡ በጎነቱ ገዝቶኛል፡፡  
                 * * *
ሀኒባል በክህደት ልቤን ሰብሮ ከተለየሁት በኋላ ለእርቅ በሬን እንድከፍት ተማፅኖዉን አላቆመም፡፡ ልቤ ግን በጄ አልል አለኝ፡፡ ወደ ጎዱን ሰዎች መመለስ እጅግ ከባድ ነዉ፡፡ ልቤ ሁዳድ ላይ ጥላቻ በቅሏል፡፡ ለምን ልቤ አለት ሆነ? ሌላ ገላ ስለለመድኩ? ሀኒባልን አመልከዉ አልነበረምን? ልክ እንደ ሸማ ፍቅር ያልቃል? መስፍንን መተዋወቄ የሕይወትን አዲስ ገጽ እንድገነዘብ አድርጎኛል፡፡ ዛሬ፣ ሰንካላ እድልን ከመርገም ታቅቦ እልፍ ብሎ ፍቅርን የመዝገን ዕድል እንዳለ አዉቄያለሁ፡፡     አሁን አሁን በሀኒባል የሰርክ ተመሃልሎ መመረር ጀምሬያለሁ፡፡
 አንድ ሰሞን የሀኒባልን ምልጃ በጄ ለማለት አመንትቼ ነበር፡፡ ልቤ እየዋለለ፡፡ ግን ቆረጥሁ፡፡ ሀኒባልን ከልቤ ፅላት ላይ ፋቅሁ፡፡ መስፍንን የመሰለ በጎ ሰዉ ገፍቼ ወደ ሀኒባል ብመለስ ደግሞ እንደማይከዳኝ ዋስትና ስላልነበረኝ፡፡ በሕይወት ዉስጥ ዋስትና የለም፣ ሕይወት ቁማር ነዉ፡፡ የቁማር ጨዋታ መርሁ ልብን መክሮ ቁርጥ ዉሳኔ ማሳለፍ ነዉ፡፡ መስፍን ምርጫዬ ነዉ፡፡ በልቤ ነግሷል፡፡

Read 707 times