Saturday, 22 April 2023 20:03

የወደድኩት የግጥም መድበል

Written by  ሙላት አማረ
Rate this item
(1 Vote)

ደበበ ሰይፉና ታገል ሰይፉ (ወንድማማቾች አይደሉም)፡: በኢትዮጵያ ስነጽሑፍ ታሪክ በወጣትነታቸው በርካታ ዘመን አይሽሬ ግጥሞችን የደረሱ ጸሐፊያን ናቸው። (ቢረሳ ቢረሳ የደበበ ሰይፉን «ልጅቱ— የዘመነችቱ»ን እና የታገል ሰይፉን «ሃምሳ አለቃ ገብሩ» ማን ይረሳል?)
በእኛ ዘመን ደግሞ አያሌ ወጣቶች (በሃያዎቹ መጀመሪያና በሃያዎቹ አጋማሽ የሚገኙ ወጣቶች) መጽሐፍ የማሳተም እድሉ አላቸው። ከእነዚህ ወጣቶች መካከል ጌራወርቅ ጥላዬ አንዱ ነው። በቅርቡ “እናርጅና እናውጋ” የተሰኘ የግጥም መድበል አሳትሟል። አንብቤ የወደድኳቸውን መጻሕፍት መጠቆም ደስ ይለኛል። አንድ ልሙጥ ወረቀት ሶስት ብር በሚሸጥበት ዘመን ደፍረው መጽሐፍ የሚያሳትሙ ወጣቶች ሊበረታቱ ይገባል። “ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም” እንዲል መጽሐፍ፣ ከግጥምና ቅኔ የሚገኘውንም ደስታም ልንቋደስ ይገባል።
በመድበሏ ውስጥ ከስልሳ ያላነሱ ግጥሞች የተካተቱ ሲሆን— “ሕይወት አደይ መሳይ”፣ “ነበረ”፣ “ና አብረን እናልቅስ”፣ “የእድሜ ዘላለሜ” እና “እኔስ ባንቺ ቀናሁ” አንብቤ የወደድኳቸው ግጥሞች ናቸው።
ቁጥብ—ያልተንዛዛ—ምጣኔ ያለውና መልዕክት አዘል ግጥም ይማርከኛል።
“ነበረ” የሚለውን ግጥም አብዝቼ የምወደው ለዚህ ይመስለኛል።
“ነበረ”
ስልጣን ብይዝ?
ሁሉን ቀልበስ፣ ሁሉን ጎንበስ።
ነዋይ ባገኝ?
ምን ፈለኩኝ?
ሁሉን ሰገድ፣ ሁሉን ፈንደድ።
እግዜሩ ቢያደርገኝ እግዜሬ
እግዜሩን አሽቀንጥሬ
ሰማይ ለኔ፣ ምድር የኔ
ነበረ ሐሳቤ፣ ነበረ ምኞቴ
እግዜሩ ግን ፍርሐቱ፣
የፍርሐት ደግነቱ
ሁሉን ነፍጎኝ ማስመኘቱ።
ጌራወርቅ (2015፣ 30) (ሰረዝ የኔ)
  እኒህ ስንኞች ያስደምሙኛል፤ እኔ ባዩ ገጸባህሪ “እግዜሩ  ቢያደርገኝ እግዜሬ...እግዜሩን አሽቀንጥሬ...እግዜሩ ግን ፍርሐቱ...ሁሉን ነፍጎኝ ማስመኘቱ።” ይለናል። የሰውን እውነተኛ ጠባይና ተፈጥሮ ይነግረናል። የሰው ልጅ፣ ለስልጣንና ነዋይ ስግብግብ ነው። ገጣሚው ሊነግረን የፈለገው ይህንን ይመስለኛል። “የእድሜ ዘላለሜ” ለጎንደር ከተማ የተደረሰ ሲሆን፣ የደበበ ሰይፉን “ይርጋለም” ያስታውሰኛል። በሁለቱ ግጥሞች መካከል የአምሳ ዓመት ልዩነት ቢኖርም መንፈሳቸው ግን ተመሳሳይነት አለው። ሁለቱ ገጣሚያን ቀድሞ ከነበሩበት የክብርና ዝና እርከን የወረዱ ከተሞቻቸውን እያነሱ ይቆዝማሉ፤ “ምነው? ምን ነካብን?” ይላሉ።
ደበበ ለይርጋለም፦
“አባውራው እንደሞተበት
ወራሽ እንዳልለማበት
ገፊ ቤት፣
ሲያይ ስትዘነጣጠይ
እሚጠግንሽ ጠፋ ወይ?
ሰዎችሽ ሸሹን፣ ሄዱን?
ወደ ደራበት አመሩን?
እንደ አሮጌ ጨርቅ ሲጥሉሽ
ማን ይጠቃቅምሽ አሉሽ?
በቅሬታ ታዘብኩሽ።
አንቺ ብቻ የማትቀልጪ
በላብ በወዝሽ የማትበልጪ፣
ለምን?
ድጅኖ መዶሻ አካፋ
ጠረኑ ካንቺ የጠፋ፣
ለምን?
ባጥቢያሽ የገደል ማሚቶ መተኛቷ
በቦዘን ምክንያት መደፋቷ፣
ለምን?...እኮ ለምን?”
ደበበ (1964)

ጌራ ወርቅ ለጎንደር፦
“ወይዘሪት እምዬ! መሆንሽ ምነውሳ...?
ቀባሪ እንዳጣ ሬሳ፣ በሰው እንደተረሳ፣
ዳዋ እንደወረሰው እንደገበሬ ማሳ፤
ምላሱ ከላንቃው እንደተጣበቀ፣
ገላው እንደልብሱ በላዩ እንዳለቀ፣
በውንጭፍ ድንጋይ ምት እንደተሰበረ እንደበኩር እሸት፣
ሞት እንደተጸየፋት፤ ኑሮ እንዳቀለላት፣ ደካማ አሮጊት፣
ጎታታ፣ ዳተኛ፣ እንደ ጉፋያ ከብት፣
በሚታየኝ ሁነት፣ ይሁን ያንቺ ሕይወት?
ጎንደር! የልቤ ከተማ፤ እንዳልነበርሽ ያገር አምባ!
ምነው ዛሬ ሳይሽ እኔ፣ ውብ ዐይኖቼ አነቡ እምባ?”
ጌራወርቅ (2015፣ 21)

Read 706 times