Saturday, 15 April 2023 21:57

“ና እንጠርጥር” ወግ

Written by  ድረስ ጋሹ
Rate this item
(4 votes)

[ሽንቷ የቀዘቀዘ ላም ፤ሽለ-ሙቅ ጥገት ላም፣ወይፈን፣ጊደር፣ወገዝ እና ጥጃ ]
በረቱ በሬ የለውም ፤ ምናልባትም  አያስፈልግ ይሆናል። ከዋናው ቤት በተቀጠለች አዳፋ ቆርቆሮ ቤት ውስጥ ናቸው። እግራቸው ላይ በአዛባ የተለወሰ ማሰሪያ አለ። በየእግራቸው ልክ ይሰፋል፤በየልካቸው ታብተዋል። አንዷ ላም የዝሆኑን ታሪክ ደግማለች። በእምቦሳነቷ  ትታሰርባት በነበረች ገመድ ላም ሆናም ታስራበታለች። አእምሮዋ በልጅነቷ የሆነውን ብቻ ይስላል ፤ምናልባት ምቾት ሰጥቷት ይሆን?...
ሦስቱ ወደ ምሥራቅ ፤ሦስቱ ወደ ምዕራብ አጎንብሰው ጭድ ሲያነሱ ይታያሉ። ጸጥታ የቤቱ ሕግ ነው። ወይፈኑ ጊደሯን አይመኝም። ሽለ ሙቋም ለወይፈኑ አትቋምጥም። ጭድ በልተው ማሟሻ ብሪንጥ አላቸው። እሷን ክልብሽ አድርገው አእምሯቸውን ያዝናናሉ።
ቁርጤው።
[ ዶሮ በቆጥ ያድራል ፤ከብትም በበረቱ
 ለሰው ልጅ ፍቅር ነው፤ ዞሮ መግቢያ ቤቱ]
እንደልቤን እንደልቡ ያደርጋታል። ጎጃም አበበውን አጣፍቷል። ወደ ቀኝ መሰለኝ። በአናቱ ጎልፋ ያላት ቆብ ደፍቷል። በረባሶ ለእግሩ፣ዱላ ለእጁ ብሏል። የከብቶችን የአመጋገብ ትርዒት ቆሞ ለመከታተል ገባ። ከተዘጋጀችለት የእንጨት ምሥቅል ላይ አረፈ። ከሊቁ ክፍለ ዮሐንስ ቅኔ ተመዝዛ....«ቤትህን አህያ ሞልቶታል» የምትለዋ አቃጨለችበት። እውነትም!..እውነትም!...በረቱ አውራ አጥቷል። ተደነቀ። እንደመነሳት...እንደመቀመጥ...አደረገው። የንብ ክፍለ ጦሮች  ከአለ አውራ ምን ዋጋ አላቸው? ይሰበሰባሉ?...ኦ! የነሱ አውራስ የሚያዘው በቁፍጣን አይደል? አውራ ነኝ ብሎ በሸንበቆ ስንጥር አልገባም ይላል?...ኧረ አይልም...ኦ!ሠናይ ውእቱ አሉ፤ መርጌታ ተከስተ እያለ ተቀመጠ።
ጎዳዋ ላም... ቀንዳሟን ልትወጋት ስትሞክር አየ።
ደሟ የቀዘቀዘችዋ ላም... ሽለ-ሙቋን ላም ስትጎነትላት አየ።
ወገዙ ሊዋጋ... ወደ ወይፈኑ ሲንጠራራ አየ።
ጊደሯ... የወይፈኑን ጉያ ስትማጸን አየ።
     ደነገጠ። አፈረ። አዘነም።
«ይኼንንስ ከማይ ብትገድለኝ አምላኬ» ሲል በልቡ ጮኸ።
ከውጭ ኮቴ ይሰማል።
ወደ ውስጥ እየገባ ነው። የቦት አልያም የቆዳ ጫማ የመሰለ ዓይነት ዳና ነው።
«ከብቶች ቀኑን ሙሉ ታጉረው ለምን ዋሉ? ቁርጢው የለም? እንስሳትም ነፍስ አላቸውኮ፣...አንተ «ሺመክት» »
«ወዬ አባ!...ጠሩኝ እንዴ»
«የለህም ብዬ እንደ እብድ ብቻዬን እያወራሁ ነበር።»
«እ...»
«ማለትስ አለህ ፤የለህም እንጅ»
«ይተው አባ አለሁ።»
«ለምን ከብቶች ከበረት አልወጡም?»
«የበረት ባሕርያቸውን ሜዳ ላይ እንዳያሳዩት አስቤ። አፍሬባቸውም»
 [እኩለ ቀን። ነዲድ የፀሐይ ብርኀን። ሺመክት ልብስ ቀይሮ። ከብቶች ተፈተው መስክ እየጋጡ።]
ከብቶች በጠባብ በረት ታጉረው ስለዋሉ ˙ርቧቸዋል። ያገኙትን ሣር ሲጨረግዱም ይታያሉ። ወገዙ ከወይፈኑ ፊት ይበላል። ጊደሯ መወደጃዋን ወደ ወይፈኑ ታዞራለች። ድራማው ለሺመክት ጤና ነሳው። ከእንስሳት ባሻገር እያሰበ ነገረ ሥራቸው አልተዋጠለትም።ትንሽ ፈቀቅ ሲሉ በጥግምግም ይቀላቸዋል። ሊወጋጉ ሲሞኳከሩ ቀንዳቸውን ያኮልማቸዋል ።እረኝነቱን በብቃት ለመወጣት ቢፈታተኑትም የዋዛ አልሆን አላቸው ፤ «ከፊትህ ብላ!» እሚለው አባቱ ትዝ ስለሚለውም ነው።
ለአፍታ ሽንብራ ቆረጣ ኼደ።
ከብት ከሚያግድበት 100ሜ. ገባ ብሎ የሽንብራ እሸት አለ።«እሸት እና ቆንጆ »ስለማይታለፍ ኼዶ ቀጥፎ ተመለሰ። የሽንብራው ጨው ጨው ማለት ደንታው አልነበረም። በውኃም አልነከረውም። ከየዘለላዋ እየቀነጠበ ወደ አፉ ሲለግት ጌታው ደረሰ።
«አንተ ሺመክት»
«ወዬ አባ »
«ጊደሯ ወይፈኑን ልትሰረው ነው እንዴ የምትታከከው?»
«ና እንጠርጥር»
አብረው ሆነው ጠረጠሩ። ሽንብራውንም ትዝብቱንም።
[ሽንብራ፣ከብት አቆማ፣የሁለቱ ሰዎች ወግ፣ ጠራራ ፀሐይ]
ሁለቱ አለቃ እና ምንዝር ናቸው።ጌታ እና ሎሌ በእነሱ አጠራር። ጌታው የተለየ ክብር፣ ሎሌው የወረደ ክብር አላቸው። ጌታው ሳይበላ ሎሌው እራት አይበላም፣ሎሌ የጌታውን ትራፊ ይበላል፣የሚጠጣውም ቅራሪ ከአለፍ አለፍ ዓይነት ነው።ያም ሆኖ ቅያሜ በመሐላቸው የለም። አዛዥ እና ናዛዥ የወግ ነው።
ቀኑ ለዓይን ያዘ።
ከብቶች ወደ ማደሪያቸው ተመለሱ። ሁሉም እግራቸውን ለማሰሪያ ዳግም ሰጡ። የገመዱን ጭቃነት መቃወም አልቻሉም። ማሰር መፍታቱ በቁርጤው እጅ ነው። የእነሱ ፈንታ እንዳደረጓቸው መደረግ ነው። ከፊታቸው ልማደኛ ጭድ አለ። ፊታቸው ሲሸማቀቅ ፣ሊበሉ ሲደብራቸው ይታወቅባቸዋል። የት ይደርሳሉ?...በረት ውስጥ ያሉትን ከብቶችን « ነፍስ ያላቸው ግዑዛን » ይላቸዋል። ዓይን አላቸው አያዩም ፣ልብ አላቸው ልብ አይሉም ፣አፍ አላቸው ለመብታቸው አይጮኹም ዓይነት...
ስለ ማሩ።
ቀርቀሃ ቀፍቅፎ ሰንጥቆ ቀፎ ሰራ_ሽመክት። ንብ ሊያንብ፤ማር ሊቆርጥ። ጌታው የሰጠውን ጥብቅ ትዕዛዝ ፈጽሞ የተሻለ ነገር ለመሥራት ከከብት ጥበቃ ጋር ተሰቃየ። ቀፎ ሰራ፤ሽንጣም ቀፎ። ቀፎ መስራት ብቻውን ሥጋ ያለ ነፍስ ሆነበት። ንቦች ያስፈልጉታል_አዎ ንቦች!
ቅዳሜ ቀን ሠዎች በአያሌው እየጮኹ ሰማ። ንብ እየተከተሉ መሆኑ ነው። የሽመክት ልብ ክፉኛ ለቆመጠ። ከሚጮኹት ጋር ይጮህ፣ይሮጥም ያዘ። ንቦች በአንድ ግራር ላይ ሲያርፉ _አውራው በቁፍጣን ተይዞ ዕጣ ይጣላል።ንቦች ካለ እሱ ምንም የሆኑት ጥሩ መሪ ቢሆን አይደል?  ሺመክት የሮጠለት ንብ ለሌላ መድረሱ ልቡን ሰበረው። የቀፎውን ባዶነት ሲያስብ አዘነ። «እግዜር የከፈተውን ቀፎ ለምን አይከድንም?» እያለ አጉተመተመ።
ጎረቤታቸው ንብ አርቢ ነው።
ሽመክት ልቡ ለስርቆት ሸፈተች። በሌት ተነስቶ ከጎረቤታቸው አውራ ንብ ሰረቀ። ከንብ ጋር ማደጉ ንድፋቱን ቀንሶለታል፤ማሯን እየበሉ ንድፋቷን ቢቀበሉ አይከብድ! በቀላል ጉዳት የሚፈልገውን ወደ ቀፎው አስገባ። ለጌታውም ብስራት ነገረ።
«ሽመክት »
«ወዬ አባ»
«ንብ ሰረቅክ እንዴ?»
«አዎ! በቀልቤ ፋንታ »
ስቆ አለፈው። ጀግናም ምንም አላለውም። ምናልባት «በእንቁላሌ በቀጣሽኝ»ን እንዳይደግመው ፈርቶ ይሆናል።
ወራት አልፈው ለማር ቆረጣ ወጡ። ጌታው ፊቱን ተሸፋፍኗል። በእጁ አስፈላጊ ዕቃዎችን ይዟል። ሽመክት ሊመለከት ቆሟል። ቀፎው የያዘውን ማር ጥርግ አድርጎ አወጣ።
ወደ ቤቱም ይዞ ሲገባ ለሎሌው ቅመስ አላለውም። ሽመክት አዘነ። ለከብቶች አለቃ የሚሆን በሬ ፣ለንቦች አለቃ የሚሆን አውራ ቢያስፈልግ አንሶ ለሰውም አለቃ የሚሆን ሰው? ለዚያውም አይመክሩ አይዘክሩት አለቃ ምን ይሠራል? ይሁን ! ወቅት እጁ ላይ ጥሎኛል ይጫወትብኝ፣ ይቀልድ፣ይሳቅ ይሳለቅብኝ፣...(ተናደደ)።
በነግሕ።
ጌታው ለባብሶ ሲወጣ ተከትሎት ወጣ። በቁጣ አንደበት ...
«አባ!ለመሆኑ ከንብ ቀፎ በምን እለያለሁ?»
«የሚቆረጥህ ማር ሳይሆን አ* በመሆኑ»
ክው አለ። ነገሮቹ ኹሉ ትዝ አሉት። ለራሱ “እኔማ የንብ ቀፎ ነኝ” እያለ በአጽንዖት አረዳ። የማመርተውን የማልበላ፣የጠቀለልኩትን የማልጎርስ ፣ያበሰልኩትን የማልልስ _የንብ ቀፎ።
«ሽመክት?»
«ጠሩኝ አባ!»
«ንብ የሰረቅካቸው ሰዎች ስሞታ እየላኩብኝ ነው»
«ምነዋ ማር የተሰረቁትስ አይልኩ?»
የነገር እሰጥ-አገባቸው እየመረረ ይጥማል። ሎሌው ወደ ቤቱ ሊመለስ የመጋቢትን ወር እየጠበቀ ነው (ሰው ሊሆን!..ከተገዢነት ሊወጣ)። መጋቢት 5 በየቤቱ የገቡ ሎሌዎች ወደየቤታቸው ይመለሳሉ። ደመወዛቸውን ይዘው። እንደውላቸው ከጥሬውም ከጤፉም ይዘው። ጫማ ይቀይራሉ፤ይለብሳሉ፤ስልክ ይገዛሉ።
ገላ ሸጠው የሚያድሩት ሴቶች  ይችን ወር በተለየ ይወዷታል። ታጥበው ታጥነው ሸበላውን ቁርጤ ይጠብቃሉ። ጥሪቱን ወደቤተሰቡ ከመውሰዱ በፊት ለሽቶ እንዲጀባቸው ይፈልጋሉ ።ሎሌውም ከልጓም የወጣ ፈረስ የሚሆን በዚህ ወቅት ነው። ሽመክት መሰነዳዳት ጀምሯል።
ከጌታው ጋር የነበረውን የሎሌነት ቆይታ ሊያጠናቅቅ ቀናት ናቸው የቀሩት። ሁሉን በአዲስ ቀይሯል። ለእጁ ስልክ አበጅቷል። ማንነቷ ከማትታወቅ ሴት ጋር ሃሎ መባባሉን የሰማ ጌታው ...
«ልጅ ሽመክት »
«ወዬ አባ »
«ወይፈኖች አማራቸው መሰለኝ »
«አባ!አምሮት በጊደሮችም አይጠፋ»
ስለተግባቡ ተሳሳቁ።
«ታዲያ አምሮት በምን ይከላል? (ይወገዳል ማለቱ ነው)”
«አለቃን በመርሳት፤...»
የመሰናበቻ ቀናቸው ላይ ደርሰዋል። የለፋበት እህል ከየዓይነቱ ተሰፍሮ ተደረገለት። ምርቃት ቢጤም ተሰነዘረለት። አስከፍተንህ ከነበርስ ንገረን እንጅ አሉት ...
«መከፋት ደስ አይበለው አልተከፋሁም። በቆይታዬ ከብቶች ማሰሪያ ወዳድ መሆናቸውን አውቂያለሁ። የንብ ቀፎ እና መልአከ ሞት ምንም እንደማይጠቀሙ ገብቶኛል። የንብ ቀፎ ማር አፍርቶ ለበሊታ፣መልአከ-ሞትም ገድሎ ለኮነኝ አጽዳቂ ይሰጣሉ፤ሎሌም ለጌታው ይኸው ነው።
«በል ደህና ሰንብት ሽመክት። ጥሩው ይግጠምህ።»
«ዕድሜ ይስጥዖ ገጥሞኝም ያያሉ...ያው
ምንዝር ደልቶት ቢዘረዝር ፤
አለቃ ከፍሬው ይጠረጥር ።»
«ይጠርጥር አባክ!..ለመሆኑ ለቀጣይ ከ’ኔ ቤት ትከርማለህ?»
«የንብ አውራን ከሆኑ ምን ግዴ፤ አይሆኑም እንጅ»
ተጨባብጠው ተለያዩ (ለመለያየት ነው የተገናኙትም)። ተሸኛኙ (ይገናኙም አይገናኙም ይሆናል)..እንጠርጥር!

Read 851 times