Saturday, 08 April 2023 19:56

በሌለ ባሕር

Written by  -ድረስ ጋሹ-
Rate this item
(6 votes)

...ቀስ በቀስ በቃሉ ልቤን አለዘበው። በሌለ ባሕር ለመሻገር ቆረጥኩ። ቤተሰቦቼን የልብ ልብ ሰጠሁ። ከፊታችን ያሉ አዲስ  መንገድ ናፋቂዎችን በደስታ ተቀላቀልኩ። በእውነቱ ትልቅ ሰው ነው። ማዕረግ አለው። ማዕረጉ ሳይገድበው አቀረበን።--”

  አሻግራችኋለሁ አለን፤በሌለ ባሕር። እናቴና እህቴን ግራ ቀኝ ይዤ አተኩሬ አየሁት።ደገመና...አዎ አሻግራችኋለሁ!...ማዕበሉን፣ውሽንፍሩን፣ሁሉን ሁሉን ከፊታችሁ አፀዳለሁ ፤ገነትን ትክሻ የምትለካካ ምድርም እንደርሳለን።የተናገረውን ሁሉ ሰማሁ... ልመነው? ልጠራጠረው? አላውቅም ።እሺ! የሚል መልስ ብቻ ሰጠሁት። ቀይ ነው። ቁመቱ ዘለግ ያለ፣የቃባዥ ዓይን ባለቤት። ድንጋይ የማናገር አቅም አለው አንደበቱ። የሚዋሽም አይመስልም። ፈገግ ሲል ልብ ያቀልጣል።
እናቴን አናገርኳት።
እህቴን በግንባሬ ምልክት ሰጠኋት ።
«እስኪ ጉዱን እንየው»ተባባልን ።
በሌለ ባሕር ለመሻገር አመንን ።
[ አስቀድሜ ፍየል ከገበያ ሲገዛ ለምን ይጎተታል? የሚል ጥያቄ አነሳሁ። እናቴ «ለምን ይሆን» አለችኝ። ቀጠልኩ። አፍሪካዊያን እንደሚሉት፤ ፍየል የውሸት ንጉስ ነበረ። እንስሳት ለእሱ እንዲገብሩ  ያዝዛል። እምቢ ያሉት በገመድ እየተጎተቱ እንዲመጡለት ያደርግ ነበር። እሱ ተሽሮ አይጥ ስትሾም አልገብርም አለ። ይኼኔ  ድሮ እሱ በሚያስጎትትበት ገመድ እየጎተቱ ወሰዱት። ከዛ ወዲህ ያው እምቢ ሲል ሲጎተት ይኖራል...አይ ተረት ብላ ሳቀች እህቲቱ ።]
ጥቂት ጠጠራማ መንገዶችን አብረን ተራምደን ዋርካ አገኘን። የደረሱ ፍሬዎችን ቀጥፎ መብላት አሰኘኝ። ይኼን ሳላደርግ ንቅንቅ አልልም አልኳቸው። ቆመው ጠበቁኝ። ወደ ዋርካው ፍሬዎች...
ድንጋይ ፈልጌ ወረወርኩ...ሳትኩ!
እምቡራቡጭ ወረወርኩ ...ሳትኩ!
እንጨት አጥገመገምኩ ...ፍሬዎች ወረዱልኝ!
አየህ አጀኒ፤ «ስታፈራ ነው ነገሮች ወደ አንተ የሚወረወሩብህ» አለ አሻጋሪው ፤ጎርፉ። ንግግሩ ደንታዬ አልነበረም፤ግን መልካምና የበሰለ ሰው መሆኑን ሊነግረኝ እንደሆነ አላጣሁትም ። አንድ ሦሥት የዋርካ ፍሬዎችን ሰልቅጬ እናዝግም አልኳቸው።
የመጣንበት መንገድ ሰፊ ነበር። ወደፊት በገፋን ቁጥር ሲጠብ ይታወቀኛል። መንገድ ስንጀምር የእናቴ ፊት ነግቶ ነበር። እየራቅን ስንኼድ ታጥፎ አየሁት። እህቴን ልታዘብ ሞከርኩ፤ ፍርኀት ቢጤ ይዟታል። በተፈጥሯቸው ብዙ አያወሩም፤ካወሩም እንደ ትንኩሽት የሚናደፍ ነገር ይጥላሉ። አስጨነቁኝ...ቢሆንም ስሜቴን ለመዋጥ ታገልኩ።100 ሜ. ርቀት ላይ ብዙ ሰዎች ተደርደረዋል። «እኚህ ኹሉ ተሻጋሪዎች ናቸው »ብሎ ራሱን ነቀነቀ ...
«ወዴት?» አልኩት፡፡
«የአንድ ላም ወተት፤ የአንድ በሬ እሸት ወደ ሚበቃባት አገር»
«እሷ ደግሞ የት ናት?»
«በእኔ ኃይል ትገለጣለች»
...ቀስ በቀስ በቃሉ ልቤን አለዘበው። በሌለ ባሕር ለመሻገር ቆረጥኩ። ቤተሰቦቼን የልብ ልብ ሰጠሁ። ከፊታችን ያሉ አዲስ  መንገድ ናፋቂዎችን በደስታ ተቀላቀልኩ። በእውነቱ ትልቅ ሰው ነው። ማዕረግ አለው። ማዕረጉ ሳይገድበው አቀረበን።
ወደ ሰዎች በደረስን ሰዓት...
[ እየተንደረደሩ እግሩን ሳሙት፤አንተ አሻግረን አሉት፣የዘመኔ ሙሴን ሁን አሉት፣ትህትናውን አርከፈከፈባቸው።እንደ አደስ፣ እንደ ሱዳን ሽቶ አወዳቸው።]
ወከባውን ጠላሁት። ቤተሰቦቼን ይዤ ፈንጠር ብዬ ቆምኩ። መፈናጠር ደስ ይላል፡፡ እንደ ጉርጥ ፈንጠር...ፈንጠር ፣እንደ ጥንቸል...እንጣጥ እንጣጥ አሪፍ ነው። ሁሌ መራመድ ይሰለቻል። ከሁሉም ሐሳብ ያፈነገጠ ነገር ነበረን። «እውነት ይሁን እስኪ...» የሚል ነው። «ያልጠረጠረ  ተመነጠረ፣ቶሎ መውደድ ቶሎ ለመጥላት» የሚሉት አባባሎች እያቃጨሉብን ይመስላል።
አሻጋሪው ጎርፉ ይባላል (ጎርፍ ሲያሻግር ባይታይም)።ጎርፉ እቅፍ ድግፍ አድርገው ሰዎች ያዙት። የሃይማኖት ቢጤዎቹ፣የአገር ልጆቹ፣የጠጅ ቤት ጓደኞቹ ፣ደስኳሪዎቹ አጀብ ብለው አጀብ አስባሉን። «ምንም እንኳ ከፍ ብዬ ብታይ በሰዎች ትከሻ ላይ ሆኜ ነው» ይሉትን የሚያስብ አልመስልህ አለኝ፡፡ ግን ምናባቴ ላደርግ እችላለሁ? ስሜቴ ተፈራረቀ። በጋ፣ክረምት፣ጥቢ እና በልግ።
ይንዠቀዠቃል ሐሳቤ ...በሰዎች ትከሻ ላይ ቆሞ የማሻገሪያ ስብከቱን ሲናገር ።
ይደርቃል ሐሳቤ...ስጠረጥረው ።
ይለመልማል ሐሳቤ...የመሻገር ፍላጎቴ ጎሸም ሲያደርገኝ ።
ይሰበሰባል ሐሳቤ ...ለውሳኔ ሲዘጋጅ ።
  ከህዝቡ በኋላ ቀረን ።
እኩለ ቀን ነው፤ ዕለቱ ሐሙስ ፣ቦታውም መናገሻ። እንደ ክርስቶስ አደረገው፤  ምናልባት ነገ ዓርብ ነው ይሰቀላል፤ እያልኩ አሰብኩ። በደም ነው  መሻገር የሚኖረው እያልኩም ተፈላሰፍኩ። ከፊቴ ያሉት አጃቢዎች ድለቃውን ከለሉኝ፤ቤተሰቤንም ከለሏቸው።
ትልቁ ደሃ ትንሹን ደሃ አይወደውም ።
«አትከልለኝ፤ትርዒቱን ልይ »አልኩት አንዱን ጠምጣሚ።
«በአንድ ዓይን?»
ይኼኔ ተናደድኩበት። ታልሞ የሚተኮስ በአንድ ዓይን አይደል? ተሳሳትኩ? ለሃገሬ የከፈልኳት ዓይን ላይ ስድብ ትለጥፋለህ? ትንሽ ተጨቃጭቀን_ተሻገርን  (ከፀብ)።
መንገዱ የነጭ ጉንዳን ሰልፈኛ በመሰለ ሰው ደምቋል። ምናልባትም ታቦት የምናነግሥ እንመሥላለን። አሻጋሪውም ታቦት ይመስላል። በሰዎች እራስ ላይ ነው የተቀመጠው። ልዩነቱ፣ ታቦት የሚሸከሙ ቀሳውስት ጾመው ጸልየው ፣በኋላም ከእህል ከውኃ ታቅበው ነው። ይኼን አሻጋሪ የተሸከሙት ሰዎች ግን አፋቸው ለሰከንድ ዝም ሲል አይታይም።ቢያፍኗቸው በቂጣቸው ይተነፍሱ ይሆን?..ይሆናል ።
መሻገሪያ እግር፣መሻገሪያ ሐሳብ ይዘን ሰው እንዲያሻግረን መጠበቃችንን ጠላሁት ። ወደ እናቴ ዞሬ...እንቅር አልኳት። የልጇን ቃል ታከብራለችና «ካንተ ጋር ምን አለኝ» አለች።
ወደ ኋላ አፈገፈግን። እህቴን ብርክ ይዟታል። ከፊት ያለው ሰልፈኛ ጋር መቀላቀል የወደደች ትመስላለች። ወኔዋ ከዳት...
«ለብቻችን?..ኧረ ወደ ጎርፉ እንኺድ »(ተማጸነችኝ)
«ጎርፉ እንደስሙ ነው። በስተኋላ ሊያጥረገርገን ይችላል» (አደፋፈርኳት)
«እባክህ ወንድሜ» (ስሜቷ ተመሰቃቀለ)
«አይ! እንግዲህ..»
ወደ ኋላ ብዙ ተራምደን ትንሽ ቦታ ተጓዝን። ወደ ኋላ ሲሄዱ መንገዱ አይፈጥንም? ትዝታም እንዲሁ ተጠልቆ የማያልቅ የሆነው ለዚህ ነው? (ለራሴ ጠየቅኩ፤ገረመኝ)
ኑ! አትፍሩ። በጎርፉ ከምንሻገር ወደ መጣንበት እንመለስ።
ወደ ዓለም ስንመጣ ዓይናችን ያይ ነበር?
ወደ ዓለም ስንመጣ ብቻችንን አልነበርን?
ወደ ዓለም ስንመጣ ደካሞች አልነበርን?
ወደ ዓለም ስንመጣ በሆነ ሰው እጅ ታጥበን አልነበር?
እኮ! በቃ ወደ ዓለም እንደመጣን አስቡት። ይችን የአሁኗን ኑሮ እንደ ውልደት ቁጠሯት። አስቡት፤ ሁሉም አዲሳችሁ ነው። አዋቂ እና ህጻን ከተግባሩ እንደሚማር አክሉ። ኑ! ደፈር በሉ። መቼም...እንደ አመጣጣችን ሁሉ አሟሟታችን ለብቻ፣ዓይን ገብቦ ፣ድክምክም ብሎ እና በሌላ ሰው እጅ ታጥቦ ነው። አመጣጥን አካሄድ ይደግመዋል፤ተፈላሰፍኩ? (የማስረዳችሁ የሚሉትን ሰምቼ ነው። ) ያው ብርኀንም፣ጉልበትም፣ሌላም ሌላም በአሻጋሪ አይሰጥም፤ሙሴም አይደገምም ልል ፈልጌ እኮ ነው (ሳቁብኝ)።
«ልጄ፣ራስን ማድመጥ ብቸኝነት ነው?»
«ኧረ አይደለም!...ምነው እማ»
«አይ ምንም»
ነገር በሆዷ ገብቷል። የመፍራት ዓይነት ስሜት ተዋርሷት አየሁ። መመለስ ፈልጋ ይሆን? በጎርፉ መሻገርን የመጨረሻ አማራጭ አድርጋ አሰበችው እንዴ?...ተብሰለሰልኩ።
ጉድቤል ።
በዚህ ውስጥ የመሸጉ ሦሥት ሰዎች። ነፍሰጡር የመሰሉ ወንዶች ፣ ሆዳቸው ሸክም የሆናቸው ሰዎች። አስጠሉኝ። እናቴን እና እህቴን አቅፌ እንዳላየ ለመሆን ጣርኩ። አንገታቸው ቀና ፣ጸጉራቸው ቆም ቆም ሲል ይታወቀኛል። ከአሁን አሁን ጠሩን ስል ..ቀጭን ፉጨት አፏጩ።
ሦስታችንም ዞርን ።
ሦስታቸውም በጣታቸው ኑ አሉን።
እምቢተኝነት ተጣብቶኝ በቸልታ ወደፊት ገፋሁ። ለአፍታ ብዞር ያነጣጠሩትን ጥይት ተመለከትኩ። ሽንፈትን ይኼኔ አወቅኋት። እጄን ወደ ላይ አውጥቼ ተማረኩ። እናት እና እህቴን ይዤ ወደ እነሱ ተጠጋሁ። የቤተሰቦቼን ነፍስ ለማትረፍ ከዚህ የተሻለ ምርጫ አልነበረኝም።
ከፊታቸው ቆምን። ደም በጎረሰ ዓይናቸው አጎረጡብን። ብትንቀሳቀሱ ኖሮ ቀንድሸን እንጥላችሁ ነበር አሉን። ዛቻ እና ፉከራቸውን ሰማን። አከታትለውም ይጠይቁን ያዙ...
«ለምን ከአሻጋሪው ጎርፉ ጋር አልሄዳችሀም?»
«አልወደድንም፤እኛ ለራሳችን እንበቃለን። ለማንደርሰው ትናንት ፣ለማንጨብጠው ነገ ብዙም አንጓጓም ።አሁንን ኗሪዎች ነን»
«ቀና ቀናውን መልስ!..አትሻገሩም?»
«ከየት ወዴት ?»
«ከአሁን ወደ ነገዋ...»
«አልገባህም እንዴ?፤አንፈልግም!። በሌለ ባሕር ሰው ይሻገራል?»
አበሳጨሁት መሰለኝ፤ እጁን ጨብጦ ከጉድቤሉ ወጣ። ጣቶቹ ወደ መዳፉ ሲታጠፉ አጥንቱ ፈጠጠ። ሊያኮልመኝ ይሆን?..አልዋሽም ጨነቀኝ።
 «ማነው ስምህ?»
«አጀኒ»
«ቀጥ ብላችሁ ወደ ሰልፉ ተቀላቀሉ። አይ ካላችሁ የእሳት ቀለብ ነው የምትሆኑት። እዚህ የተቀመጥነው የማንን ጎፈሬ ልናበጥር መሰለህ? እንደ እናንተ ጎርፉን አንከተልም የሚሉትን ለመኮርኮም መስሎኝ..»
 «ጎርፍ ይብላችሁ» እያልን...እየተራገምን ...ተመልሰን ጎርፉን ተቀላቀልን። ጎርፉ አደረሰው ሊያደርሰን..!
ይኼኔ እናቴ.፤ «መጪው ጊዜ ይከብዳል ልጅም ከእናቱ ይወልዳል» የሚል ቃል ወጣት።
ደገመችና...
«ሞት የሌለበት አገር እንኼድ ብለን ፤ በጎርፉ ግፊት ከአይቀበሩበት እንዳንደርስ »
ሰለሰችና...
«የማን ግፍ ጎርፍ ሆኖ መጣ? ግን» አለች፡
   ድንገት!..ቁርስ ደርሷል ተባልኩ። ህልም እልም እያልኩ ተነሳሁ...


Read 839 times