Monday, 24 October 2022 00:00

ካፑችኖ፣ የዮሐንስ ሐሳቦች

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(0 votes)

ክፍል አራት (የመጨረሻ ክፍል)
ፀሊም ለዛ (dark humor)
የሚያሳቅቅ ወይም የሚያሸማቅቅ፣ የሚያስፈራ ወይም የሚያሳዝን ድባብ ውስጥ ሳቅን የሚያጭር ትረካ ነው - “ፀሊም ለዛ”። በአንድ በኩል ኅሊናን ያናውጣል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ሳንወድ በግድ ፈገግ የሚያሰኘን ከንፈርን የሚያስገልጥ አስቂኝ ትረካ ነው። ዮሐንስ፣ “ተጠርጣሪዎቹ” በተሰኘው አጭር ትረካ እንዲህ ጽፏል፤…
ከመካከላችን አንዱን ቦዘኔ አስነስተው ወደሆነ ክፍል ይወስዱታል። ያለ ምንም ማንገራገር ወደ መታረጃችን መሄዳችን፣… የመልካም አስተዳደር ውጤት ያስመዘገበን ቦቅቧቃ ቦዘኔዎች መሆናችንን ማሳያ ሞዴል ነው።
የተወሰደውን ቦዘኔ የመደብ አጋራችንን እያሰብን… የሚያደርጉትን እየገመትን… በታላቅ ስጋትና ዝምታ መዋጥ ነው እጣችን። የፍርድ ቀን ዛሬ ሆኖ… ሁላችን በግራ እንድንቆም የተፈረደብን አይነት ድንጋጤ ላይ ነን።
…ተራዬ ደረሰና ወደሚጠብቀኝ ሲኦላዊ መከራ ያለ ማልጎምጎም ተጎተትኩ።
ገና ከበር ስዘልቅ ወንጭፍ የሆነ ቡጢ ተቀበለኝ… ተመስገን! እስካሁን አለሁ።
“ወስደሀል አይደል?”
“ምኑን?”
“ምኑን ይላል…”
ሌላ ቡጢ።
ጡጫ… እርግጫ።
ጥፊ… መዳፍ ጥፊ… አይበሉባ ጥፊ… ጫማ ጥፊ… (ለካስ ጥፊ እንዲህ ፈርጀ ብዙ ነውና)። አጣናና ፍልጥ… የመጥረጊያ እንጨትም ያለ ሥራ ከሚያንጎላዡ እኔ ላይ እንዲሰባበሩ ተደረገ።
በዚህ መሐል ነበር የቀበሌያችን ሊቀ መንበር፣ የተዛነፈ አስቂኝ አፈጣጠሩን ይዞ የገባው።
ሊቀ መንበር ማለት… ሌላውን መሬት ላይ አስቀምጦ፣ ሌላው ላይ የሚቀመጥ… የቀበሌ እግዚአብሔር ማለት ነው።
ግጥማዊ ማስረጃ…
እሱ ያመጣውን እሱ ይመልሰው
አሰሱም ገሰሱም ይቀልዳል በሰው።
ሊቀ መንበራችን ከወገቡ በላይ የሰውነቱ እጥረት፣ የስንዝሮ አይነት ሲሆን፤… ከወገቡ በታች ያለው አካሉ ደግሞ እንደ ናይል ርዝመት አንደኛ ነው።
የእግሩን መጋጠሚያ ይዘው… ቁልቁል ወደ ቁርጭምጭሚቱ ሲወርዱ (በበቅሎ የሰባት ቀን መንገድ የመሰለ ጉዞ)፣… ‘ይሄ ሰው… ሁለት እግር አለኝ ብሎ ሁለት ዛፍ ላይ ይወጣል… ወላ ሁለት እግሩን ተማምኖ፣ በአንድ ጊዜ ሁለት መንገድ ይኼዳል…’ የሚያስብል አፈጣጠር ነው ያለው።
“አመነ ጓዶች?”
“ኧረ አላመነም ጌቶች” አለ አንደኛው ገራፊ - እውቀቱ ሁሉ መግረፍ ብቻ የመሰለ።
“እስኪያምን ግረፉት” አለ ሊቀመንበራችን።
“ሌላም ሥራ የለን አለቃ… መለጥለጥ ብቻ!” አለ ቶሎ ባምን የሚናደድ የሚመስለው ሌላኛው ገራፊ።
“አናርከ-ፋሺስት ሁላ የአብዮቱ ፀር ነው። መወገድ አለበት። ጓዶች፣ የኛ ሥራ የአብዮታዊት እናት አገራችንን እጅ ይዘን… ወደፊት መገስገስ ነው” አለና ወጣ።
ለካንስ ሊቀመንበራችንና ጭፍሮቹ፣ እጅና አንገት ለይተው አያውቁም። አብዮታቸውን ለመጠበቅ ዘብ ሲቆሙ፣… እጅ ብለው አንገቷን ይዘው ሲጎትቷት፣… አገራቸውን አንቀው ገደሏት።
“አታወጣም አንተ?” አለ አንዱ ገራፊ።
‘አታወጣም?’… ኤሎሄ ኤሎሄ ብቻ በሆነበት ሰአት… ‘አታወጣም?’ የሚለው ቃል ገናና እና ረቂቅ ሆነብኝ።
አታወጣም…? መታወቂያ ሊሆን ይችላል… ሴት ሊሆን ይችላል… የሆነ የተደበቀ መረጃ ሊሆን ይችላል። የሆነን ቁስ አካልን ከውስጥ ወደ ውጭ ሊሆን ይችላል።… አዬ መከራዬ… ያሳሬ ፅናቱ… ይሄን ሁሉ አማራጭ መልስ ባቀርብ… በፀረ ልማት ወይም አገር በመክዳት አጀንዳ ተፈርጄ መከራዬን ነው የማፀናው።
ተጠርጥረን የተያዝነው የሊቀመንበራችን ሰዓት ስለጠፋ ነበር። ተጠርጥረን ከተያዝነው መቶ ምንምን ቦዘኔዎች፣ ሀምሳ አራታችን በግርፋት ብዛት ታመምን። በተያዝን በሦስተኛው ቀን የሊቀ መንበራችን የቢሮ ስልክ ተንጫረረ። ጓድ ባለቤታቸው ነበረች የደወሉት።
“ሀሎ… ጓድ ሊቀ መንበር?”
“ምን ነበረ… ምን ፈለግሽ?”
“ጓድ ሊቀመንበር… የተከበረ ሰዓትዎ፣ እዚሁ እኛው ባኞ ቤት ውስጥ ተገኝቷል” አሉ የተከበሩ ባለቤታቸው።
እፎይይ…
እኛስ ወዲያው ተለቀቅን።
ባኞ ቤቱ ግን፣ እጅ ከፍንጅ ስለተያዘ፣ ወታደራዊ ቅጣት ይጠብቀዋል።
አስማተ ገሀድ (magic realism)
ተምኔትን ከገሀዳዊ እውነት ጋር በማስተሳሰር የሚጻፍ ልብወለድ ነው - አስማተ ገሀድ ልብወለድ። ዮሐንስ በዚህ የአጻጻፍ ዘይቤ ነው፣ “መንገደ ሰማይ” የተሰኘውን አጭር ትረካ ያቀረበልን። ዮሐንስ እንዲህ ጽፏል፡
የመጠጥ ቤቱ ስም፣ ከገነት ወዲያ - ከሲኦል መለስ።
የሰውን ልጅ፣ ከወይን ወንዝዳር ባየነው ጊዜ፣ ልባችን ወንፊት ሆና፣ ደስታዋን በመላው ምድር ላይ አንዘረዘረች… እንላለን እኛ መናፍስታን…
መጠጥ ቤቱ…
ወለሉ፣ በተቦካና በተላቆጠ የወይን ተረፈ ምርት የተለሰነ ሲሆን፤ ግድግዳው በወይን ግንድ (በቋሚነት፣ በአገድምነት፣ በማገር፣ በሳጋነት)፣ በወይን ልጥና በወይን ሀረግ አልባስነት ትብብር የቆመ ነው።
ጣራው ደግሞ፣ በወይን ግንድ ርብራብ አልጋነት ተመስርቶ፣ በለመለመ የወይን ሀረግ ልብሰ ተክህኖና በጎመራ ፍሬው አስዋቢነት ፍፃሜውን እንዲቀዳጅ የተደረገ ነው።
መጠጥ ቤቱ… ከወይን አፈር ተጠንስሰው፣ በወይን አፈር ላይ ድኸው፣ የወይን ወተት የምታመነጭ እናት ጡት ጠብተው፣ የወይን አፈር አሳምሮ ባበቀለው የወይን እንጀራ አድገው፣ ከወይን ከተሰራ የመጠጥ ዓይነት ተጎንጭተው፣… የስካር ዛርን የሚሳፈሩ እንደ አሸን የፈሉ ጠጪዎች አሉት።
እነዚህን ወይናም ጠጢዎች፣ ጠብ እርግፍ እያሉ፣ እንደየአመላቸው የሚያሽሞነሙኗቸው፣ እየጠጡ ያለስስት የሚያጠጡ አስተናጋጆችም አሉት - መጠጥ ቤቱ።
በአጠቃላይ፣ መጠጥ ቤቱ፣ ጠጪ አለው፣ አጠጪ አለው፣ ስካር አለው፣ ሴት አዳሪዎች፣ ወንድ ዝሙተኞች… የሌለው የለም።
የማርያም ፈረስ፣ ዘላለምን ተሻጋሪ መሳይ እርጋታውን እንደተከናነበ፣ የተለመደ ጥጉን ይዟል። የወይን ጭማቂ (ጁስ)፣ ከወይን ቅርንጫፍ በተሰራ ቀዳዳ ዘንግ (ስትሮ) እየማገ ተቀምጧል። ማለቂያ አልባ የሚመስል እርጋታው ቢወደድለትም እንኳን፣ ፀጋ አልባ፣… ኧረ እንደውም ከነስሙ፣ ጥላቢስ ቀትረ ቀላል ነው ይባላል- (የማሪያም ፈረስ)።
“ለእኔም ቪምቶ አምጣልኝ! ማን ከማን ያንሳል?…”አለ- የሰይጣን ፈረስ ሁሌም እህል ውጠው እሳት የሚተፉ ቀይ ዐይኖቹን… የማርያም ፈረስ ላይ እንደሰካ ነው የሚኖረው።
“ወስኪኮ ነው እየጠጣህ ያለኸው?… አለ አስተናጋጁ በማስገንዘቢያ ቃና። የሰይጣን ፈረስ፣ በምድሪቱ ላይ በአንደኛ መዓረግነት የተቀመጠን ውስኪን ነው እየጠጣ ያለው።
“እና ቢሆንስ? ለነሱ ተደርጎ …” (ብሎ የሰይጣን ፈረስ ሲናገር፣ የማርያም ፈረስ መልካምነትን ይሰብካል - እንዲህ በማለት)።
“አይ ክፋት! ክፋት እኮ ነው! መሸከምህ ካልቀረ፣ ስሪትህ ለማፈናጠጥ መሆኑ ካልተቋጨ፣ ለምን መልካሙን ብቻ አትሸከምም?”
“አሁን አንተ፣ ክፉ የማትሸከመው ስለፈቀድክ ይመስልሀል? ሐቁ ግን እሱ አይደለም። ልሸከመው ብትልም፣ የሚችል ጫንቃ ስለሌለህ ነው።”
“ይኼ ማምለጫ ነው! ይኼ፣ የለየለት የቀጣፊዎች ማምለጫ… ነው።… እኔ መርጬ እንጂ… -(እያለ ያስረዳል የማሪያም ፈረስ። የሰይጣን ፈረስ እጥፍ ድርብ አብዝቶ ይመልስለታል።)
“…አየህ አፈጣጣርህ ከዓይን አለመግባትን፣ ለዓይን አለመሙላትን፣ አስቀያሚነትን የተሸከመ ስለሆነ፤ ማካካሻህ እርጋታ፣ ቁምነገረኝነት፣ ታማኝነት፣ በጎ ነገርን መስበክ… አይነት ነገር ነው።… በአቋቋምህ፣ በእይታህ፣ በአነጋገርህ፣ ባረማመድህ፣ በሳቅህ መማረክ ስለማትችል፤ ሕይወትን አቅልለህ አትመለከትም። ቀብጠህ አቅብጠህ መኖር አትችልም። በታላቅ መስዋዕትነት (ትንሽነት በወለደው መስዋዕትነት) አንዲት ሴት ታገኝና፣ እሷን ላለማጣት ስለትዳር ክቡርነት፣ ስለትዳር ቅዱስነት፣ ስለመኝታው ፍጹምነት ምናምን እየተረክህ መኖር ብቻ ነው ዕጣ ፈንታህ …” (መንገደ ሰማይ፣ 2009፡ ገጽ 147-150)።
ኤግዚስቴንሻሊስቱ ዮሐንስ
ዮሐንስ የሰው ልጅ የራሱ ምርጫና ውሳኔ ውጤት ነው ብሎ የሚያስብ ኤግዚስቴንሻሊስት ደራሲ ነው። አስተምህሮዎቹን ተከትሎ የዕለት ተዕለት ኑሮው የሚገፋ ደራሲ እንደሆነም በቅርበት ታዝቤአለሁ።
ሰው ረዳት የለሽ ነው
በሌላ አነጋገር፣ እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ምድራዊ የህልውና ፍዳ እና ቀንበር ለመሸከም ራሱ ብቻ (መለኮታዊ አጋዥነትን ሳይማፀን) ኃላፊነቱን መውሰድ አለበት።
ሐዘኑም ደስታውም መዳፉ ላይ ነው። ሰው ምድር ላይ ምርጫውን ተከትሎ መኖር ይችላል። የምድርን ፍስሃ ወደ ጎን ገፍቶ (ለመለኮታዊ አካል ራስን አስገዝቶ መኖር) ተምኔታዊ ሰማያዊ ዓለምን ማለም፤ ለዮሐንስ የባከነ ሕይወት ነው። ተምኔታዊ ዓለም ቅዠት ነው ይለናል ዮሐንስ። በእርግጠኝነት የተጎናፀፍነው ሕይወት በእጃችን ላይ ያለውን ምድራዊ ሕይወት ነው። ዮሐንስ መንገደ ሰማይ በተሰኘ ሥራው እንዲህ ጽፏል፣
በስብከት የሚቆም ትውልድ መጨረሻው አያምርም። የራሱን ሆያሆዬ፣ የነፍሱን አበባ አየሽ ወይ፣ በገዛ ራሱ አቅም መኖር ሲቻለው… ወኔው ስልብ ስለሚሆን በነብር ጣት ዘመኑ… መንፈሱ ላሽቆ ይገረጅፋል።
ተሰብኬ ልንቃ የሚል ስብዕና… ጠፊም አጥፊም ነው። ስብከት የተግባር ማማር የሌለው… ቃል አንደበቱ ብቻ ደም ግባታም የሆነ… እርቃኑን ግርማ … በለስ ነኝ ያለ ኮሽም ነው (ዮሐንስ፣ 2009፡ ገጽ 160)።
የወል እሴቶች ፍፁማዊ አይደሉም
ማኅበረሰብ የሚተዳደርባቸው የግብረገብ (ethical values) እና የሥነ ውበት (aetsthitic values) አንፃራዊ እንጂ ፍፁማዊ እንዳልሆኑ ዮሐንስ ያምናል። ይህ ዮሐንስ አቋም ከኒቼ እና ሳርተር ሐሳብ ጋር የሚስማማ ነው።
ዕጣ ፈንታ ቅዠት ነው
 ዕጣ ፈንታ፣… ቅዠት ወይም ኢሉዥን ነው ይለናል። እንደ ዮሐንስ እሳቤ፣ እያንዳንዱ ሰው በራሱ የታነጸ ሕንጻ ነው (ዮሐንስ፣ 2009፡ ገጽ 150)። የዕጣ ፈንታ እምነትን የሚተቸው ዮሐንስ ብቻ አይደለም። እንደ ሳርተር እሳቤ፣ በዕጣ ፈንታ ማመን ራስን ወደ ቁስነት ማሳነስ ስለሆነ የተወገዘ ነው።
ካፑችኖ እንደ አገራዊ ማንነት
ዮሐንስ አገሩን ኢትዮጵያን አምላኪ ጸሐፊ ነው። በሦስት ሺህ ዘመን ታሪኩ ይኮራል። የእናት አገሩ የሰው ዘር ምንጭነት ልበ ተራራ ያደረገዋል። የሳላቸው ገጸባሕሪያት የሐበሻን ማንነት የተሸከሙ፣ መንፈሱ የሰፈረባቸው፣ ጠረኑን የሚያውዱ፣ ርእዮቱን እንደ መስታወት የሚያሳዩ ናቸው። ‘አገር ማለት ሰው ነው’ ከሚሉ የእሱ ዘመን ትውልድ ጸሐፍትን ይለያል። የዮሐንስ የማንነት ሐተታ አቋም እጅጉን ይገዳደራቸዋል። እኔ እና የጓደኛዬ ትዕንግርት በተሰኘ ሥራው እንዲህ ጽፏል፡
ሀገር ማለት የነዋሪዎቿ መልክ ነች…
የሀገር ገፅታ ማለት የተወላጆቿ መልክ ነው… ባለሀገር ማለት “ሀገሬ ነች” ብሎ ማውራት የሚችለው - - የሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን… ድንበር በተደነገገለት ወሰነ መሬት ላይ ያለ ባለሕይወቱም ሆነ ግዑዙም ጭምር ነው…
ኢትዮጵያዊ ትንኝ ከካምቦዲያዊ ትንኝ ጋር በዜግነት ምን ያገናኘዋል?
የኢትዮጵያዊው ጉንዳን ቁንጥጫ በትውፊቱም ሆነ በወግ ልማዱ ከጓቲማላው ጉንዳን ጋር ምን ያዛምደዋል?
ኢትዮጵያዊ ድንጋይና ኮሞሮሳዊ ድንጋይ በእምነታቸውም ሆነ በስርአተ አምልኳቸው ፍፁም የተለያዩ አይደሉም እንዴ?
ባለሀገር የሚባለው …
በትምክህቱ ያበጠ - - በትህትናው የተለበጠ… በፍርሃቱ የተናጠ - - በጀግንነቱ የተንቆጠቆጠ… በጥላቻው የሆመጠጠ - - በፍቅሩ የጣፈጠ… በእምነቱ ያጌጠ - - በክህደቱ የሸመጠጠ… የሰው ልጅ ብቻ አይደለም… ከመሬት የሆነ ሁሉ… ለመሬት የተፃፈ ሁሉ… መሬታዊ ነውና ባለሀገር ነው…
የኢራናዊ መልክ ኢራን ነች… የቬትናሙም መልክ ቬትናም… ፊት የተፈጠረው ለውበት ብቻ ሳይሆን… መታወቂያም ጭምር ስለሆነ ነው… ፊት የሌለው ስምም የለውም… (ዮሐንስ፣ 2009፡ ገጽ 279)።
በትረካዎቹ ውስጥ በጉልህ የተሳለችውን ዋና ገጸባሕሪ እዚህ ላይ ማስታወስ አለብን። ሄራን ትባላለች። ውክልናዋ (allegory) ኢትዮጵያ የተባለችውን አገር ነው። ዮሐንስ ሄራን በተሰኘ ትረካው ውስጥ እንዲህ ጽፏል፡
“…አዛውንት የሀገር ስም ናቸው።…የትውልድና የዘመን ክብር ናቸው። የታሪክ ማደሪያ ማህደር፣ ማስረገጫውም ማህተም ናቸው። የመጪ ትውልድ ራዕይ ማፍኪያ ብሩህ ሀቅ ናቸው። አዛውንቶቿን ያላከበረች ሀገር፣ ገመናዋን ገላልጣ፣ በአደባባይ መሐል እርቃኗን እንደ ቆመች ጋለሞታ ትመስላለች…” ያልሺኝን ሳስታውስ ለመንደራችን ምህላ እይዛለሁ።
የአዛውንት ማረፊያ ዋርካዎች፣ መፀለያ ደብሮች፣ ተረት ማውሪያ ካቦች፣ መመካከሪያ አንባዎች… ከመንደራችን ተገርስሰው፣ ፈርሰው፣ ተንደው፣ ተምሰው አልቀዋል።
የጠዋት ፀሐዩን ከሰማዩ ላይ የተነፈገው መንደራችን… የቀትር ጋንኤሎቹ ከቁጥር በዝተው፣- ህፃን አዋቂውን በየእለቱ የሚያጠናፍሩበት መንደራችን፣… የማይለቀው ፅልመት ገዝፎ የተጫነው መንደራችን፣… የምህረት ቀኑን በመናፈቅ ስለራሱ ከማልቀስ ይልቅ፣ በኔ አንቺን ማፍቀር ስላቅ መውለዱ ግን አያስቅም?
ህፃናት የማይገላበጡ (እሳቱ በማይጠፋ ምድጃ ላይ፣ እንደሰማይ የተዘረጋ ብረት ምጣድ ላይ ተጋግረው) ቂጣዎች ይመስላሉ - በመንደራችን። ለቅሷቸው፣ የማያባራ እርር ክስል ያለ ሆኗል። ገፃቸው (የህፃን ላህዩን ተገፍፎ) ከሚንቋቋ ቁርበት ብሶ ተጨረማምቷል - በመንደራችን።
“…ህፃናት የነገ ስም ናቸው። የሕይወት ውበት ናቸው። የሀገር ብልፅግና ክንፍ፣ የመልካም ነገር ሁሉ ስረ መሠረቱ ናቸው። ህፃናቶቿን ያልተንከባከበች፣ ለነጋቸው የሚሆን ብሩህ ቀን ፀንሳ ያልቆመች ሀገር ወዮውላት…!” ያልሽኝን ሳስታውስ፣ ፀጉሬን እየነጨሁ፣ መጎናፀፊያዬን ቀዳድጄ ማቅ በመልበስ ወየው እላለሁ።
ሴት ልጅ ክብሯን ጥላ፣ በየጥሻው ካገኘችው ጋር ተኝታ ትነሳለች - በመንደራችን። መማገጥ ጌጥ ሆኗል - በቀያችን። ጡት፣ መቀመጫና ሀፍረት፣ እንደ ፊት እንደ ዓይን እንደ አፍንጫ… ባደባባይ የሚታዩ ተራ ነገሮች ሆነዋል።
“…ሴት ክብሯን ከጣለች፣ መላዋን ከሳተች፣ ብልሃቷን ከዘነጋች፣ ወግ ማዕረጓን ካረከሰች… እናትነት ጉድ ፈላበት። ሴት እኮ የመኖር ሁሉ ማዕረጉ፣ የዘር ሁሉ ጉልላቱ ነች። ውበት ከሴት ሲመነጭና ሲፈስስ እኮ ነው፤ ሁሉ ምሉዕ በኩልዔ የሚሆነው…” አልነበረም የምትይኝ?
አየሽ፣… እኔ ግን እዚህ ሁሉ መአት ውስጥ ቆሜ፣ አንቺን አፈቅራለሁ። እዚህ ሁሉ ክፋት ውስጥ ሆኜ፣ ደገኛ ስምሽን የፅናቴ ማግዘፊያ አድርጌዋለሁ። እዚህ ሁሉ ሰዶም ውስጥ እያለሁ፣ የኖህ መርከብ ስምሽን እጠባበቃለሁ። ስምሽ ይመጣል። አይቀርም። (ዮሐንስ፣ 2009፡ ገጽ 5-6)።
ዮሐንስ ካፑችኖ በተሰኘው ትረካው ኢትዮጵያዊያን ቀደምት ህዝቦች ሲሆኑ ሌላው የዓለም ህዝብ ኋላ መጥ ነው ይለናል። ካፑችኖ የኢትዮጵያዊያን ጥንተ መልክ ወካይ ነው። ወተት ደግሞ ፈረንጆችን (the white)። ቡና ውክልናው ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ሌሎች ጥቁር ህዝቦችን ነው።
መኮንን ደፍሮ (Telegram: @ MekonnenDefro77)

Read 9532 times