Sunday, 31 October 2021 16:14

በጎንደርና አፋር አካባቢዎች በህወሃት 482 ንፁሃን መገደላቸው፤ 109 ሴቶች መደፈራቸው ይፋ ሆነ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ህወኃት በወረራ ይዟቸው በነበሩ የሰሜን ጎንደርና ደቡብ ጎንደር ዞኖች እንዲሁም በአፋር ክልል በሚገኙ ወረዳዎች በንፁሀን ዜጎች ላይ የፈፀማቸውን ጥቃቶች አስመልክቶ የፍትህ ሚኒስቴር ሲያካሂድ የነበረውን ምርመራ ሪፖርት ትናንትና ይፋ አድርጓል፡፡
በዚህ ምርመራ በተገኘው ውጤት መሰረት፤ በሰሜን ጎንደር ዞን የህወኃት ታጣቂዎች 96 ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸውን፣ በ53 ሰዎች ላይ አካላዊ ጉዳት ማድረሳቸውን፣29 ሴቶችን አስገድደው መድፈራቸው 6 የእገታ ድርጊት መፈጸማቸውን ሪፖርቱ ይጠቁማል።
በተጨማሪም በመንግስት የግልና የሃይማኖት ተቋማት ላይ ዘረፋና ውድመት መፈፀማቸውም ተመልክቷል፡፡
በደቡብ ጎንደር ዞን ባሉ አምስት ወረዳዎች ደግሞ 129 ሰዎች በታጣቂዎቹ መገደላቸውን በ54 ያህሉ ላይ አካላዊ ጉዳቶች መድረሱን እንዲሁም በንፋስ መውጫ ከተማ ብቻ 73 ሴቶች ላይ የአስገድዶ መደፈር ወንጀል መፈፀሙን  ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በአፋር ክልል ደግሞ ነሐሴ 29 ቀን 2013 በጋሊኮማ ቀበሌ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ በነበሩ ተፈናቃዮች ላይ በተፈፀመ ጥቃት 24 ንጹሀን መገደላቸውን፣ 42 ያህል መቁሰላቸውን፣በሌሎች ወረዳዎች 17 ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም 17 መቁሰላቸውንና 7 ሴቶች የአስገድዶ መደፈር ጥቃት እንደደረሰባቸው በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡
በሁለቱም ክልሎች የህወኃት ታጣቂዎች በፈፀሙት ጥቃት በድምሩ 482 ሰዎች መገደላቸውን፣ 165 ሰዎች መቁሰላቸውን እንዲሁም 109 የአስገድዶ መደፈር ድርጊት መፈጸሙን በፍትህ ሚኒስቴር ሪፖርት ተመልክቷል፡፡





 

Read 11551 times