Saturday, 31 July 2021 00:00

በጦርነቱ 3 ሺህ ሰዎች ከአማራ ክልል ተፈናቅለው ወደ ሱዳን ተሰደዋል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 በአፋር ከ70 ሺ በላይ ሰዎች በግጭቱ ተፈናቅለዋል
         
              በአማራና ትግራይ ክልል ድንበር አካባቢ በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት ባሳለፍነው ሳምንት 3ሺ የሚደርሱ ሰዎች  ወደ ሱዳን መሰደዳቸውን አለማቀፉ የስደተኞች ተቋም (IOM) አስታውቋል።
ስደተኞቹ ከአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ መሆናቸውን ያመለከተው ተቋሙ፤ ከስደተኞቹ መካከል የተወሰኑት በሱዳንና በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ እንደ አዲስ በተቀሰቀሰው ግጭት የተፈናቀሉ እንደሆኑም ጠቁሟል።
ባሳለፍነው ሳምንት ከአማራ ክልል ተፈናቅለው ወደ ሱዳን ከተሰደዱ 3ሺህ ያህል ስደተኞች መካከል አብዛኞቹ ሴቶች፣ ህፃናትና አቅመ ደካማ አዛውንቶች እንደሆኑ የተቋሙ መረጃ ያመለክታል፡፡
በተመሳሳይ የህወኃት ሃይሎች፣ የአፋር ክልል ከትግራይና ከአማራ ክልሎች ጋርየሚዋሰንበትን አካባቢ ጥሶ በመግባት የፈጠሩትን ግጭት ተከትሎ፣ ከሰባ ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስታውቋል፡፡
ነዋሪዎቹ የተፈናቀሉት ከቅዳሜ ሐምሌ 10 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ ዞን አራት፣ ፋንቲረሱ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ግጭት በመፈጠሩ መሆኑን የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን ባለፈው ሳምንት ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ሃላፊው በወቅቱ በነበራቸው መረጃ መሠረት፤ ከጎሊና፣ አውራ እንዲሁም ኡወና ቴሩ ከሚባሉ ወረዳዎች ከ70 ሺ በላይ ነዋሪዎች ሰዎች መፈናቀላቸውን ነው የጠቆሙት፡፡  
እስካሁንም ባልተቋጨው የትግራይ ቀውስ ሳቢያ ባለፉት 8 ወራት በአጠቃላይ ከ65 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ሱዳን መሰደዳቸውንና በአራት የተለያዩ ካምፖች ተጠልለው እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡
በአሁኑ ወቅት በዚህ ግጭት ምክንያት ስደተኞችን ጨምሮ ከ5.2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መደበኛ ህይወታቸው ተናግቶ በሰብአዊ ቀውስ ውስጥ ይገኛሉ ተብሏል። ጦርነቱ በአፋጣኝ መፍትሄ የማይበጅለት ከሆነ ግጭቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተስፋፍቶ የከፋ ሰብአዊ ቀውስ እንዳያስከትል አለማቀፍ የረድኤት ተቋማት ስጋታቸውን እየገለፁ ነው።


Read 669 times