Saturday, 12 December 2020 00:00

አቶ ልደቱ ከ140 ቀናት በኋላ በ30 ሺ ብር ዋስ ተፈቱ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

“ለምርጫና ለውህደት በዝግጅት ላይ እያለን መፈታታቸው ብርታት ይሰጠናል”
                           
             የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) መስራች እና የምክር ቤት አባል አቶ ልደቱ  አያሌው በ30 ሺ ብር ዋስ እንዲፈቱ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ድ ቤት ምስራቅ ምድብ ችሎት ወሰነ፡፡ በዚሁ ችሎት ላይ አቶ ልደቱ ዋስትና ሊፈቀድልኝ አይገባም በሚል ሰፊ ንግግር እንዳደረጉ የገለፁት አቶ አዳነ፣ ዳኞች በጉዳዩ ላይ አቃቤ ህግ አስተያየት እንዲሰጥበት መጠየቃቸውን ጨምረው ገልፀውልናል። አቃቤ ህግም አቶ ልደቱ በውጭ ሆነው ክሳቸውን ቢከታተሉ ተቃውሞ የለኝም ማለቱን ተከትሎ ነው ፍርድ ቤቱ እንዲፈቱ የወሰነው ብለዋል።
ፍርድ ቤቱ ትላንት ታህሳስ 3 ቀን ጠዋት በዋለው ችሎት፤ አቶ ልደቱ “የፌደራልና የክልል መንግስትን ማፍረስ” በሚል የተከፈተባቸውን ክስ በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ መወሰኑን እና ከእስር መፈታታቸውን የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አዳነ ታደሰ፣ ከቢሾፍቱ ፍርድ ቤት በስልክ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
አቶ ልደቱ ሰኔ 24 ቀን 2012 ዓ.ም  ምሽት የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ “ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት” በሚል በምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከፈተባቸው ክስ በ100 ሺህ ብር ዋስትና ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ቢወሰንላቸውም ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ባለማክበር ሳይለቃቸው በመቆየቱ ከፍተኛ ትችት የቀረበበት መሆኑ አይዘነጋም። ሁለተኛውን “የፌደራልና የክልል መንግስታትን በማፍረስ” የሚለው ክስ የቀረበባቸውም ከእስር ሳይፈቱ ነው።
የኦሮሚያ ፖሊስ፤ ጠቅላይ  ፍርድ ቤቱ ትላንት የሰጠውን ውሳኔ በማክበር አቶ ልደቱን የለቀቃቸው ሲሆን የአርቲስት ሀጫሉ ግድያን ተከትሎ “በቢሾፍቱ የተቀሰቀሰውን የወጣቶች አመፅ አስተባብረሀል በሚል ለእስር ከተዳረጉ 140 ቀናት እንደተቆጠረ ኢዴፓ አስገንዝቧል፡፡
የፓርቲው ስራ አስኪያጅ አቶ አዳነ ታደሰ የአቶ ልደቱን ከእስር መፈታት አስመልክቶ በሰጡን አስተያየት፤ “ ዘንድሮ በሚካሄደው ምርጫ ለመወዳደርና እንደነ ህብር እና ሲሀን እና  ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመዋሃድ አንድ ጠንካራ ፓርቲ ሆነን ለመውጣት ማግስት እየሰራን ባለንበት  የአመራራችን መለቀቅ ትልቅ ብርታትና ጉልበት ይሆነናል ከልምዳቸው ብዙ እንማራለን”  ብለዋል። ለአዲስ አድማስ።  የአቶ ልደቱን የሰውነት ክብደት መቀነስ በፎቶ ተመልክተን ስለጤናቸው ሁኔታ ጥያቄ ያቀረብንላቸው አቶ አዳነ “አቶ ልደቱ” በአሁኑ ሰዓት የልባቸውም ሆነ ሌላ የጤናቸው ጉዳይ አስተማማኝ መሆኑን ላንድ ማርክ ሆስፒታል ማረጋገጡን ገልፀው ለጠቅላላ ጤንነታቸው አብዝተው ስፖርት በመስራታቸው ሸንቅጥ ማለታቸውንም ጨምረው ገልፀዋል።



Read 8079 times