Friday, 23 October 2020 14:30

አለማችን በኮሮና ሳቢያ 28 ትሪሊዮን ዶላር ታጣለች ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 የአለም ባንክ በማደግ ላይ ላሉ አገራት ለኮሮና ክትባት የ12 ቢ. ዶላር ድጋፍ አደረገ


          አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ አለማችን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በመጪዎቹ አምስት አመታት በድምሩ 28 ትሪሊዮን ዶላር ያህል እንደምታጣ ሰሞኑን ባወጣው አለማቀፍ ሪፖርት አመልክቷል፡፡
ተቋሙ ባወጣው መግለጫ እንዳለው፤ ወረርሽኙ በአለማችን ከስራ አጥነት፣ የኢንቨስትመንት መዳከም፣ ከህጻናት ትምህርት ማቋረጥና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ እየፈጠረ የሚገኘው ቀውስ ስር የሰደደና በአመታት የማይሽር ጠባሳ የሚጥል እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
በተያያዘ ዜና፤ የአለም ባንክ አንድ ቢሊዮን ለሚሆኑ በማደግ ላይ ያሉ የአለማችን አገራት ዜጎች፣ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ለማዳረስ የሚውል 12 ቢሊዮን ዶላር መመደቡን ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ የባንኩን ፕሬዚዳንት ዴቪድ ማልፓስን ጠቅሶ  አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው፤ የአለም ባንክ ገንዘቡን የመደበው በማደግ ላይ ያሉ አገራት ፍትሃዊ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ስርጭትና አቅርቦት እንዲኖራቸው እንዲሁም በቂ ምርመራና ክትትል እንዲያደርጉ ለማስቻል ነው፡፡
ይህ የገንዘብ ድጋፍ ባንኩ እ.ኤ.አ እስከ 2021 ድረስ በማደግ ላይ ላሉ የአለማችን አገራት ለመለገስ ቀደም ብሎ ቃል ከገባው 160 ቢሊየን ዶላር ውስጥ የሚካተት መሆኑንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና፣ በተለያዩ የአውሮፓ አገራት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንደገና እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ አገራት የተለያዩ እገዳዎችን መጣል መቀጠላቸውን፤ የአለም የጤና ድርጅት በአንጻሩ ዘግቶ መቀመጥ ብቸኛው መፍትሄ አይደለምና መንግስታት ያስቡበት ማለቱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በአውሮፓ ባለፈው ሳምንት በአንድ ቀን ብቻ 100 ሺህ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ይህም ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በአህጉሪቱ በአንድ ቀን የተመዘገበ ትልቁ ቁጥር እንደሆነና ወረርሽኙ እየተባባሰ ከሚገኝባቸው አገራት መካከልም ቼክ ሪፐብሊክ፣ ፈረንሳይና እንግሊዝ እንደሚገኙባቸው ገልጧል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ባለፈው ሳምንት በ11 በመቶ ያህል ጭማሪ ባሳየባት አሜሪካ፤ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የተባለ ኩባንያ ጀምሮት የነበረውን የኮሮና ቫይረስ ክትባት ምርምር አንድ በጎ ፍቃደኛ መታመሙን ተከትሎ እንዳቋረጠ የተነገረ ሲሆን፣ ለጥንቃቄ ሲባል ሶስተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው የሙከራ ምርምሩ እንቋዲረጥ መደረጉንም ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡
ሮይተርስ በበኩሉ፤ በተለያዩ የአለማችን አገራት ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ በተጣሉ የጉዞ ገደቦችና የድንበር መዝጋት እርምጃዎች ሳቢያ ከ3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ስደተኞች እንዳይንቀሳቀሱ ታግደው በአስከፊና አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ተቋም መግለጹን ዘግቧል፡፡
በርካታ ስደተኞች በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ይገኙባቸዋል ከተባሉት መካከል የመካከለኛው ምስራቅና የሰሜን አፍሪካ አገራት እንደሚገኙበት የጠቆመው ዘገባው፣ በአገራቱ 1.3 ሚሊዮን ያህል ስደተኞች በመሰል ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙም አክሎ ገልጧል፡፡


Read 1777 times