Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 14 July 2012 11:09

የእርግብ አሞራ ከሉሲዎች ጋር

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“የጃሉድ ድግስ ሰኔ ሰላሳ” ሰሞኑን በስፋት የሰማነው ማስታወቂያ ነበር፡፡ ቀኑ ደርሶ የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ ፕሮግራሙ ይጀመራል ከተባለበት ከምሽቱ 1 ሰአት ጀምሮ የላፍቶ ሞል አዳራሽ የመግቢያ በሮች መጨናነቅ ጀመሩ፡፡ የድግሱ ዋነኛ አቀንቃኞች ጃሉድ እና ዳዊት መለሰ እስኪመጡ ታዳሚው ከዲጄ በሚለቀቀቁ ዜማዎች ሲዝናና የቆየ ሲሆን በተለይ በኢትዮጵያዊ ዘፋኝ የተቀነቀነው “ሳዋ ሳዋሌ” የተሰኘ የኪሲዋሂሊ ዘፈን እና የቴዲ አፍሮ “ጥቁር ሰው” (አብዛኛውን ታዳሚ ሲወዘውዙ ነበር፡፡

“እንደልቤ አልሆን ደርሶ ፍቅሯ በልቤ ውስጥ ነግሶ” ከሚለው ዘፈኑ ጀምሮ  ሌሎች ተወዳጅ ዜማዎቹን በማስከተል “አባብዬ ልጃችሁን” በሚለው በመሀሙድ ዘፈን ስራውን ያሳረገው ዳዊት መለሰ በብዙዎቹ ታዳሚዎች እንደተናፈቀ ያሳየ ነበር፡፡

ቀለል ባሉ ግጥሞች እንዲሁም ብዙዎች ከልጅነታቸው ጋር በሚያገናኙት ዜማዎች  የተዋዙት የጃሉድ ዘፈኖች በመሀሪ ብራዘርስ ባንድ በተለይ በሊድ ጊታሪስቱ ሮቤል መሀሪ የሙዚቃ ጥበብ ታዳሚውየእርካታ ጣሪያ ላይ ደርሶ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

ከጎልማሳ የእድሜ ክልል በላይ ለሚገኙ ሰዎች “የእርግብ አሞራ” የሚለው የጃሉድ ዘፈን የልጅነት ትዝታን የሚቀሰቅስ ነው፡፡ ጃሉድ ይህን ዘፈን ሲያቀርብ የተደጋጋሚ ድሎች ባለቤት ከሆኑት የሴት የእግር ኳስ ቡድን - ሉሲዎች  ጋር መሆኑ ለኮንሰርቱ ልዩ ውበትና ድምቀት ሰጥቶት ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ሉሲዎቹ አሪፍ ጨፋሪዎችም ናቸው፡፡ “የእርግብ አሞራ” ሲዘፈን አብዛኞቹ ታዳሚዎች ልክ እንደልጅነታቸው ያደረጉትን  ጃኬት ወይም ስካርፍ በማውለብለብ ጨፍረዋል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ደጋፊዎችም ለአስረኛ ጊዜ ላነሱት ዋንጫ የተዘፈነ አስመስለውታል፤ የክለባቸውን አርማ በማውለብለብ፡ “ጉሮወሸባዬ” የሚለውን ዘፈንም ለሉሲዎች ዘፍኗል -ጃሉድ፡፡

የጃሉድ “ሬጌ ዱብዱብ” የሚለው ዘፈኑ ላይ ዱብ ዱብ የምትለው ቃል ታዋቂውን የጅምናስቲክ አሰሪ ግርማ ቸሩን ሳታስታውስ አልቀረችም፡፡ ብዙዎቹ ታዳሚዎች ዱብ ዱብ የምትለዋን ቃል በግርማ ቸሩ ቅላፄ አብረው አቀንቅነዋል፡፡ ታዳሚዎች ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት የዲኬቲ ኮንዶም ዴስክ ላይ እየሄዱ ኮንዶም ሲወስዱ ነበር፡፡ የጃሉድ “ያቺ ነገር” ሲዘፈን ታዲያ በአየር ላይ በመወርወር አዳራሹን ኮንዶም በኮንዶም አድርገውታል -ታዳሚዎች፡፡

ሻሸመኔ በሚለው የጃሉድ ዘፈን

ፈያሞ ሰብኒ ኦሮምቲቻ

ጂርታሞ ቢያ ሻሸመኔ

የሚለው የዘፈኑ ክፍል በአብዛኛው ታዳሚ የተቀነቀነ ሲሆን የኮንሰርቱ ታዳሚ ለነበሩት ራስተፈሪያውያን ደግሞ የአገራቸውን ስም የሚጠቅስ ዘፈን በመሆኑ ሞቅ ያለ ምላሽ ተችሮታል፡፡

በሬጌ ስልት የሚያቀነቅነው ጃሉድ “ዳንሴ ዳንሴ” የሚለውን ለአማርኛ እስክስታ የተመቸ ዘፈኑን ሲያቀርብ አዳራሹ ድብልቅልቁ ወጥቶ ነበር፡፡ በመጀመሪያ የይደገም ጥያቄ ያስተናገደውም ዜማው “ዳንሴ ዳንሴ” ነበር፡፡

ጃሉድ ጃማይካዊ ነው ኢትዮጵያዊ የሚለው ጉዳይ ብዙዎች ሲያነሱት የነበረ ሲሆን በኮንሰርቱ እለት ጥርት ባለ አማርኛና ትህትና በተላበሰ አነጋገር ኢትዮጵያዊ መሆኑን አሳይቷል፡፡

 

 

Read 1560 times Last modified on Saturday, 14 July 2012 11:14