Saturday, 04 July 2020 00:00

ኮሮና የከፋ ደረጃ ላይ ከደረሰ 50 ሚ. ህዝብ ለጽኑ ችግር ይጋለጣል ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)


          እስካሁን ድረስ 6ሺ አንድ መቶ ስልሳ ሰዎችን አጥቅቶ፣ 103 ያህሉን ለሞት የዳረገው የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ተፅዕኖ የከፋ ደረጃ ላይ ከደረሰ 50 ሚሊዮን ሰዎች በጽኑ ችግር ውስጥ ሊወድቁ እንደሚችሉ የኢትዮጵያ ስራ ፈጠራ ኮሚሽን የሰራው አንድ ጥናት አመለከተ፡፡
ጥናቱ እንደጠቆመው፤ ቫይረሱ ለስድስት ወራት የሚቆይ ከሆነ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ 60 በመቶ ሰዎች ስራቸውን ሊያጡ ይችላሉ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በአገልግሎት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ 74 በመቶዎቹ ሥራ አጥ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተሰማርተውበታል በሚባለው የአገልግሎት ዘርፍ ብቻ 3 ሚሊዮን ሰዎች ስራቸውን ሊያጡ እንደሚችሉም ጥናቱ አመልክቷል፡፡
ቫይረሱ በህብረተሰቡ ውስጥ በስፋት ከተስፋፋ አደጋው የከፋ ሊሆን እንደሚችል የጠቆመው ጥናቱ፤ የቫይረሱ ተፅዕኖ የከፋ ደረጃ ላይ ከደረሰ በአጠቃላይ 50 ሚሊዮን የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ለከፋ ችግር ይጋለጣሉ ብሏል፡፡
አለም አቀፉ የሥራ ድርጅት አይኤልኦ በቅርቡ ይፋ ያደረገው አንድ መረጃ በበኩሉ፤ ምንም እንኳን ቫይረሱ በእድሜ የገፉና ቀደም ሲል የተለያዩ የጤና ችግሮች ያሉባቸውን ሰዎች በስፋት የሚያጠቃ ቢሆንም ወረርሽኙ የሚያስከትለው የሥራ አጥነት ቀውስ ወጣቱ ክፍል ላይ ይበረታል ብሏል፡፡ በአገልግሎት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ሴቶች፣ ዋስትና አልባ ስራ የሚሰሩ ሰዎች እንዲሁም ስደተኛ ሰራተኞች ክፉኛ የስራ አጥነት ችግር ሊገጥማቸው ይችላል ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚስቶች ማህበር ያሳተመው አንድ ጥናቱ፤ ቫይረሱ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ከሆነ በርካቶች ሥራ አጥ ሊሆኑ እንደሚችሉ አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር በቅርቡ ይፋ ያደረገውን የአራት ባለሙያዎች ምልከታ ዋቢ አድርጐ ቢቢሲ እንደዘገበው፤ ወረርሽኙ የሚፈጥረው የምጣኔ ሃብት ጉዳት የአገልግሎት ዘርፉን በተለይም የቱሪዝምንና የመስተንግዶ ኢንዱስትሪውን፣ የውጪ ንግዱንና የመጓጓዣ ዘርፉን በእጅጉ ሊጐዳ ይችላል ይላል፡፡ የግብርናው ዘርፍም ቢሆን በኮሮና ወረርሽኙ ሳቢያ ከሚደርሰው የምጣኔ ሃብት ጉዳት ማምለጥ የማይችል መሆኑን ያመለከተው መረጃው፤ በተለይ በቀላሉ የሚበላሹ ምርቶች አብቃዮችንና አከፋፋዮችን ለጉዳት እንደሚዳርጋቸው አመልክቷል፡፡ ወረርሽኙ የአቅርቦት ሰንሰለትን ያውካል፤ የስራ መቀዛቀዝ በሚፈጥረው የገቢ እጥረት የንግድ ተቋማት የመንቀሳቀሻ ገንዘብ እጥረት እንዲያጋጥማቸውና እዳ መክፈል እንዳይችሉ ሊያደርጋቸውም ይችላል ተብሏል፡፡
ከኢትዮጵያ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ሰላሳ ዘጠኝ በመቶውን ድርሻ የሚይዘው የአገልግሎት ዘርፍ በወረርሽኙ ከሌሎች ዘርፎች በበለጠ ሊጐዳ እንደሚችልና ሰላሳ ሶስት በመቶውን ድርሻ የሚይዘው ግብርና ግን በአንፃራዊነት ያነሰ ጉዳት ያገኘዋል ተብሏል፡፡
የኢኮኖሚ ባለሙያዎቹ ጥናት እንደሚያመለክተው፤ ወረርሽኙ አነስ ባለ የጉዳት መጠን ለሶስት ወራት ከቆየ ምጣኔ ሃብቱ እስከ 44 ቢሊየን ብር የሚደርስ ኪሳራ የሚደርስበት ሲሆን ወረርሽኙ ለስድስት ወራት የሚቆይና የጉዳት መጠኑም ከፍተኛ ከሆነ የኪሳራው መጠን ከሁለት መቶ ቢሉዮን ብር የሚበልጥ እንደሚሆን አመልክቷል፡፡

Read 1854 times